23/07/2024
የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ዛሬ ወደ ፓሪስ ይሸኛል
| በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሽኝት ይደረግለታል።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተሳታፊ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተውጣጡ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ በውሃ ዋና እና በቦክስ ስፖርቶች ትሳተፋለች።
የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደቆየ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተያያዘ ዜና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፉ አትሌቶችን ዛሬ ማለዳ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሯ በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን የምታስጠሩ አትሌቶች በዘንድሮው ኦሊምፒክም በአሸናፊነትና በጀግንነት ታሪክ ሀገራችሁን እንደምታስጠሩ እምነቴ ነው ብለዋል።
አትሌቶቹ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የቡድን ስራና ስፖርታዊ ጨዋነት ውጤት ለማምጣት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችም ስለ ቅድመ ዝግጅታቸውና ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ በመግለፅ ከሚኒስትሯ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።