03/10/2022
በተለያየ ዘመንና ሥፍራ ሀገርን የመሩ ሦስት ሰዎችን አደንቃለሁ፡፡ አንዱ ቋረኛው ንጉሥ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ለምን? እነሆ ከብዙ ሦስት ምክንያቶች፡-
***
በግልፅ እና በዝርዝር ከሚታወቀው ልጀምር፡፡ በፖለቲካ ታሪካችን ሥልጣንን እና ባለሥልጣንን የሚያገናኘው ትጋት ወይም ብቃት አይደለም፡፡ አጋጣሚ ነው፡፡ አጋጣሚው ለዙፋን “ከተመረጠ” የዘር ሀረግ መወለድ ሊሆን ይችላል፡፡ አጋጣሚው የፖለቲካ ሥልጣን የያዘ ስብስብ አባል ሆኖ መገኘት ሊሆን ይችላል፡፡ ከጥንት እስከ አሁን፣ መሪዎቻችን በአጋጣሚ በተገኙበት የሥልጣን ወለል ላይ የበቀሉ ናቸው፡፡ ቴዎድሮስ በአጋጣሚ በተገኘበት የሥልጣን ወለል ላይ የበቀለ መሪ አይደለም፡፡ ሥልጣኑ የትጋት - የብቃት ውጤት ናት፡፡ የቴዎድሮስን የንግሥና ዘመን ስኬት እና ፍጻሜ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጻሕፍ በጥሩ ገልጾታል፡-
“ያ ቋረኛ ንጉሥ ተበጣጥሰው የነበሩትን ያበሻን መንግሥት ክፍሎች በሰላው ጎራዴው ቀጥቅጦ አዋደደ፡፡ ሕዝቡንም ከካህናትና ከሹሞች ቀምበር አርነት ሊያወጣ አገር በጄ ብሎ አወጀ ትምህርትንም ሊከፍት ተከራከረ፡፡ አንባቢ ሆይ በዚህ ጥረቱ ምን ተጠቀመ ይመስልሃል፡፡ በመላው ሕዝብ በካህናትና በሹሞች ተመክሮ ተነሳበት አሳበደውም፡፡ በመጨረሻም ለባዕድ አሳልፎ ሰጠው በገዛ እጁም ሞተ፡፡”
***
ዳግማዊ ቴዎድሮስ እና አብርሃም ሊንከን በተለያየ ሥፍራ በተመሳሳይ ጊዜ የተለያዩ ሕዝቦችን መርተዋል፡፡ የቴዎድሮስ ሰሞነ-ፍስሐ (heydays) ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት (American Civil War) ጋር የተገጣጠመ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የዚህ ጦርነት ውጤት የዓለምን የፖለቲካ ሥርዓት እንደሚወስን የተረዳው ገና በጦርነቱ ጅማሬ ነው፡፡ የፖለቲካ እርምጃዎቹን ከዚህ ጦርነት ውጤት ጋር ለማስማማት፣ ስለጦርነቱ መረጃዎችን ያሰባስብ እንደነበር ተጽፎ አንብበናል፡፡ ለማሳያ በአጼ ቴዎድሮስ ተይዘው ከታሰሩት እንግሊዛውያን መካከል አንዱ የነበረው ዶክተር ሔንሪ ብላንክ የጻፈውን እንጥቀስ፡-
“The following day, during the march, Theodore sent Samuel backwards and forwards with questions,--such as: ‘Is the American war over? How many were killed? How many soldiers had they? Did the English fight with the Ashantees? Did they conquer them? Is their country unhealthy? Is it like this?’ …”
***
ዳግማዊ ቴዎድሮስ ቋንቋ ሲጠብ መግባቢያ ሲሰፋ የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑን የተረዳ መሪ ነው፡፡ በዘመኑ የኢትዮጵያ ግዛት ለሚገኝበት ንፍቀ-ዓለም የአረብኛ ቋንቋ ዕውቀት ቁልፍ የፖለቲካ መሳሪያ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ይህን በመገንዘብ አረብኛ ለመማር ሞክሯል፡፡ ዶክተር ሔንሪ ብላንክን በድጋሚ እንጥቀስ፡-
“… Mr. Rassam, having complimented his Majesty on his great work, added, that before long he hoped that our people would have the same pleasure of admiring it as we did. Samuel, who translated on that occasion, turned quite pale, but as … Emperor [Theodore] understood a little Arabic he was obliged to render the sentence, though he evidently did not like it.”
(የተያያዘው ምስል “THE END OF KING THEODORE” ከሚል መግለጫ ጋር የተገኘው ሔንሪ ስታንሊ በግሪጎሪያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1896 ‹‹Magdala: The Story of the Abyssinian Campaign of 1866-7›› በሚል ርዕስ ካሳተመው መጻሕፍ ነው፡፡)