የአብክመ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች ዳኞች እና ዐቃቢያን ህግ ድምፅ.""".

  • Home
  • Ethiopia
  • Bahrdar Giyorgis
  • የአብክመ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች ዳኞች እና ዐቃቢያን ህግ ድምፅ.""".

የአብክመ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች ዳኞች እና ዐቃቢያን ህግ ድምፅ.""". Justice : the quality of being just, impartial, or fair.

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች ውይይት ተካሄደባሕርዳር ፣ ነሐሴ 05/2018(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)የአማራ...
11/08/2026

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች ውይይት ተካሄደ

ባሕርዳር ፣ ነሐሴ 05/2018(የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች፣ ዳኞች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁሉም ምድብ ችሎቶች አስተባባሪዎችና ዳኞች በተገኙበት የክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የማጠቃለያ መድረክ እና የቀጣይ በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ፣ የ2018 ዓ/ም የፍርድ ቤቶች እቅድ አፈጻጸም፣ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ እና የ2019 ዓ/ ም የትኩረት አቅጣጫዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ ፣ ግልጽ፣ ፈጣን እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑ በቀረበው ሪፖርት የተገለጸ ሲሆን፣ በሶስት ዙር ትግበራ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ዲጂታላይዝ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ትግበራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በሁሉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በ27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና በሁለት የማረሚያ ቤቶች መተግበር የተቻለ መሆኑ ተገልጿል።

የመረጃ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የፍርድ ቤት ኔት ወርክ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑም ተገልጿል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት በቢሯቸው ሆነው የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የወረዳ ፍርድ ቤቶችን አሰራር መከታተል የሚችሉበት ስርዓት የተዘረጋ መሆኑም በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል።

የስማርት ኮርት፣ ኢ- ፋይሊንግ፣ ትራንስክሪፕሽን፣ የሞባይል መተግበሪያ እና ድረ ገጽን ጨምሮ ዲጅታል ፊርማ፣ ዲጅታል አንድ ማዕከል እና የጥሪ ማዕከል አገልግሎቶች ከተተገበሩት እና ሥራ ላይ ከዋሉት የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫዎች መካከል ተጠቅሰዋል።

በ2018 ዓ.ም በነበረው እቅድ አፈጻጸም የዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና ከመቸውም ጊዜ በላይ ማሻሻል የተቻለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የክልሉ ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን አመላካች ነው።

የተለያዩ ቅጾችን በማዘጋጀት እና ለባለጉዳዮች በነጻ በማቅረብ ከ209 ሚሊየን ብር በላይ ባለጉዳዮች ሊያወጡ የሚችሉትን ወጪ ማዳን መቻሉም ተገልጿል።

ከቀረቡት የአፈጻጸም እና የቀጣይ ዓመት መነሻ እቅዶች በመነሳት አመራሮች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች፣ የምድብ ችሎት አስተባባሪዎችና ዳኞች በበጀት ዓመቱ አፈጻጸም፣ በቀጣይ ዓመት የትኩረት መስኮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የላቀ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ ማእከል ለማድረግ መወሰድ ባለባቸው የቀጣይ አመት ተግባራት ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸው እና በየደረጃው ባሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተተገበሩ ሥራዎች የሚታዩ እና ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች፣ ሊሻሻሉ ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ የዳኞችን አቅም ለመገንባት እየተካሄዱ ያሉ መደበኛ የዳኞች ውይይቶች፣ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች፣ የልምድ ልውውጦች እና ሌሎችም አሰራሮች የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገባቸው አጋዥ መሆናቸውን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፣ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያይቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፣ የተጀመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ በችግርነት የተነሱት ደግሞ በሂደት እንደሚፈቱ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ፣ መንግስትና ሕገ መንግስቱ የሰጠንን ሀላፊነት እና አደራ በአግባቡ በመወጣት በአገልግሎት አሰጣጣቸው አርአያ የሆኑ ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት የያዝነውን እቅድ እውን በማድረግ ተገልጋዩ የሚተማመንባቸው የዳኝነት ተቋማትን መገንባት አለብን ብለዋል። © የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region

>> የስልጣን ጥማት
11/08/2026

>> የስልጣን ጥማት

>> ተቋማዊ እምነት መኖር
05/08/2026

>> ተቋማዊ እምነት መኖር

የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥለባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና ሽማግሌዎች የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና ዘለቄታዊ ጥቅሞቹየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ (CRS) እ...
03/08/2026

የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥለባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና ሽማግሌዎች የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና ዘለቄታዊ ጥቅሞቹ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ (CRS) እና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባሕር ዳር–ደሴ ሀገረ ስብከት (CCE-BD) ጋር በመተባበር ለባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ አሰልጣኞችና ሽማግሌዎች የሚሰጥ የስድስት ቀናት አገር አቀፍ ተጽዕኖ ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ ጀምሯል።

በክልሉ ውስጥ ለ15 የባሕል አለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች እውቅና በመስጠትና በ1,377 ቀበሌዎች የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማደራጀት የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ ይገኛል።

1️⃣ የሥልጠናው ዋና ዋና ትኩረቶችና የተሸፈኑ ርዕሶች

• የባሕል ፍትሕ ሥርዓትና የሕግ ብዝኃነት (Legal Pluralism)።
• የዳኝነት ነፃነት፣ የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ሚናና ኃላፊነት።
• የሰብአዊ መብቶች፣ የጾታ እኩልነት፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ጥበቃ።
• የባሕል ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር ያላቸው ሕጋዊ ግንኙነትና አሠራር።

2️⃣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ የፍትሕ አገልግሎት ማረጋገጥ

የባሕል ፍርድ ቤቶች ማኅበረሰቡ ባሉበት አካባቢ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ተከራካሪ ወገኖች ወደ ከተማ በመመላለስ የሚያወጡትን የትራንስፖርትና የእንግልት ወጪ በመቀነስ ፈጣን ውሳኔ እንዲያገኙ ያደርጋሉ።

3️⃣ የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የፋይል ክምችት (Case Backlog) መቀነስ

አነስተኛና ማኅበራዊ አለመግባባቶችን በባሕል ፍርድ ቤቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የፋይል ጫና በመቀነስ የፍትሕ ሥርዓቱን ቀልጣፋ ያደርገዋል።

4️⃣ ዘላቂ ሰላምና ማኅበራዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር 🕊️

በመደበኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አንደኛው ወገን አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሲሆን፣ በባሕል ፍርድ ቤቶች ግን በእርቅና በስምምነት (Win-Win Approach) ስለሚወሰን የኅብረተሰቡን አብሮ የመኖር እሴትና ሰላም ያጠናክራል።

5️⃣ የሰብአዊ መብቶችና የሕግ መርሆዎች መከበር

የሚሰጡት ሥልጠናዎች የባሕል ፍርድ ቤቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የጸዱ እንዲሆኑ፣ የሴቶችንና የሕፃናትን መብት እንዲያስከብሩና በሕጉ ማዕቀፍ (በአዋጁ) መሠረት ብቻ እንዲዳኙ ያደርጋል።

6️⃣ ባሕላዊ እሴቶችን ከዘመናዊ ሕግ ጋር ማጣጣም

የአካባቢን በጎ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ከዘመናዊ የህግ ፍልስፍናዎች ጋር በማቀናጀት፣ ለማኅበረሰቡ ቅርብና ተቀባይነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት እንዲገነባ ያስችላል።

የባሕል ፍርድ ቤቶችን ማጠናከር የፍትሕ ተደራሽነትን ማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው።

ስለ ባሕል ፍርድ ቤቶች ሚና እና አሠራር ያለዎትን አስተያየት በኮመንት ያጋነው።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 01/ 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ይሆናሉ።በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ በፍርድ ቤቶቻችን የሚስተናገዱ ጉዳዮችን ከስር በተ...
03/08/2026

የክልሉ ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 01/ 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ይሆናሉ።

በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ በፍርድ ቤቶቻችን የሚስተናገዱ ጉዳዮችን ከስር በተያያዘው ደብዳቤ ይመልከቱ 👇

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ቋሚ ምድብ ችሎት የ2018 ዓ.ም  ስራ አፈፃፀሙን ገመገመ ።================//========​ ሀምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ሀይቅ፣  የአማራ ...
03/08/2026

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ቋሚ ምድብ ችሎት የ2018 ዓ.ም ስራ አፈፃፀሙን ገመገመ ።
================//========
​ ሀምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ሀይቅ፣

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ችሎት የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ መድረክ የምድብ ችሎቱ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች በተገኙበት በሎጎ ሀይቅ ሪዞርት ተካሂዷል።

​የግምገማ መድረኩን የምድብ ችሎቱ አስተባባሪ አቶ አሻግሬ አድማሱ በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እቅድ እና በጀት ዝግጅት ባለሙያ አቶ መሀመድ ሰይድ የምድብ ችሎቱን አመታዊ ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከታቀዱት ግቦች አንጻር በዝርዝር አቅርበዋል።
​📊 ከሪፖርቱ የተገኙ ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች እና የተመዘገቡ ውጤቶች፡
​የመዛግብት እልባት እና አፈፃፀም፡
​ እስከ ታህሳስ 13/2018 ዓ.ም በሰበር ሰሚ ችሎት ከቀረቡት 1395 መዛግብቶች ለ1,116 መዛግብት ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ 1,392 (99.7%) መዛግብት እልባት አግኝተዋል። የመዛግብት ማጣራት አቅም (Clearance rate) 150.3% ደርሷል።
​በመደበኛ ችሎት 2165 መዝገቦች ቀርበው ለ1,732 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 1,905 (87.9%) ውሳኔ አግኝተዋል። የመዛግብት ማጣራት አቅም (Clearance rate) 103% ሆኗል።
​በአጠቃላይ፡ በሁለቱም ችሎቶች ከቀረቡት 3,560 መዛግብት ውስጥ 3,297 (92.6%) መዛግብት እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል።
​የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ስማርት ኮርት (Smart Court)፡
​በስማርት ኮርት በቪዲዮ ኮንፈረንስ 309 መዛግብት (108 ወንጀል እና 201 ፍታብሔር) የታዩ ሲሆን፣ 1,233 ተገልጋዮች አገልግሎት በማግኘታቸው ያወጡት የነበረውን የገንዘብ፣ የጉልበት እና የጊዜ ወጪ ማስቀረት ተችሏል።
​የርቀት ሙግት (የቪዲዮ ኮንፈንስ) እና የኢ-ፋይሊንግ (E-filing) አገልግሎት በማስጀመር ዳኞች የውሳኔ ፅሁፎችን የእጅ ፅሁፍን በማስቀረት የውሳኔ ጽሁፎችን በኮምቲውተር እንዲጽፉ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። ወደ ባህር ዳር ሰበር ከ370 በላይ መዛግብት በኢ-ፋይሊንግ ተልከዋል።
​የፍትህ ተደራሽነት እና አጠቃላይ አገልግሎት፡
​ተከላካይ ጠበቃ ማቆም ለተሳናቸው ተከሳሾች ጥበቃ በመስጠት 29 መዛግብት ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ 47 ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።
​በበጀት ዓመቱ 1,438 ሴቶች፣ 143 አካል ጉዳተኞች እና 2,490 አረጋውያን የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽ ተደርጎላቸዋል።
በመደበኛ እርቅ እና ድርድር እንድሁም በፍርድ ቤት መር አስማሚ ችሎት አማካኝነት ስራዎች ለመስራት ጥረት የተደረገ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ከመሆኑ አንፃር አመርቂ ስራ ባይሰራም በመደበኛው እርቅ እና ድርድር ስርአት 12 መዝገቦች መስራት ተችሏል፡፡

​ከተመደበው 6,689,142 ብር በጀት ውስጥ 6,689,112.84 ብር (100%) ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ከቅጣት እና ከዳኝነት 2,528,224.42 ብር ገቢ ተሰብስቦ ለመንግስት ፈሰስ ተደርጓል።
​🔍 የታዩ ጥንካሬዎች እና በቀጣይ የሚስተካከሉ ድክመቶች
​በመድረኩ ላይ ለአዲሱ ቴክኖሎጂ የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች መሰጠታቸው፣ እድሜ ያስቆጠሩ (ከለር ኮድ የተሰጣቸው) መዛግብት ቅድሚያ አግኝተው መሰራታቸው እና ተጋላጭ ወገኖች ቅድሚያ ማግኘታቸው በጥንካሬ ተነስተዋል።
​በሌላ በኩል የሰዓት አከባበር ክፍተቶች፣ በኢ-ፋይሊንግ ወቅት የሚታዩ የቴክኒክ እና የቁጥር አሰጣጥ ችግሮች፣ እና የነዳጅና የኑሮ ውድነት ያሳደሩት ጫና በችግርነት የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ በቅንጅትና በክትትል እንደሚፈቱ ተገልጿል።
በቀረበው ሪፖርት መሰረትም ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ውይይቱን የመሩት የምድብ ችሎቱ አስተባባሪ አቶ አሻግሬ አድማሱ እና የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ከግምገማ መድረኩ በማስከተል የምድብ ችሎቱ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች የለጎ ሀይቅ ሪዞርትን መናፈሻዎች እን ልዩ ልዩ ክፍሎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

​ #ፍትህ

📌 የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2018 ዓ.ም የስራ አፈፃጸም እና የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ግምገማ መድረክ በሀይቅ ከተማ አካሄደ። ​ ሀምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ...
01/08/2026

📌 የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2018 ዓ.ም የስራ አፈፃጸም እና የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ግምገማ መድረክ በሀይቅ ከተማ አካሄደ። ​

ሀምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም | ሀይቅ

​የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁሉም ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች በተገኙበት በሀይቅ ከተማ የ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት የስራ አፈፃጸምና የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡
​የመድረኩን መከፈት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ትዕግስት ዳኛቸው በንግግራቸው ያበሰሩ ሲሆን፤ የበጀት ዓመቱ የስራ አፈጻፀም ሪፖርት በእቅድ ዝግጅት፣ በጀትና ክትትል ባለሙያው አቶ መሀመድ ሰይድ እንዲሁም የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ መኮንን ሲሳይ አማካኝነት በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የበጀት ዓመቱ ዋና ዋና አፈጻጸሞች በቁጥር፡
​⚖️ የመዝገቦች አፈጻጸም፡ በበጀት ዓመቱ ውስጥ 6,811 የፍትሃብሔር እና የወንጀል ጉዳዮች ቀርበው 5,686 ጉዳዮች እልባት አግኝተዋል (83.5% አፈጻጸም)።
​🛡️ የተከላካይ ጠበቃ አገልግሎት፡ ጠበቃ ማቆም ለማይችሉና በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ 338 ተገልጋዮች (320 ወንድ፣ 18 ሴት) አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ 67 ተከሳሾች (20%) በተከላካይ ጠበቆች አማካኝነት ነፃ ተብለዋል።

የበጀት አጠቃቀምና ገቢ፡ ከተመደበው 9,623,363 ብር የመስሪያ በጀት ውስጥ 100% ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ከዳኝነትና መቀጫ 14,478,730.55 ብር ገቢ ተደርጓል።

የባህል ፍርድ ቤቶች፡ በ255 ቀበሌዎች 1,326 የሀገር ሽማግሌ ዳኞች (1,224 ወንድ፣ 102 ሴት) ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል። በዚህም 866 የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት አግኝተው ሊወጣ የነበረ 11,049,585 ብር ከወጪ እንዲድኑ ተደርጓል።

የፍርድ ምርመራና አስተዳደር፡ 1,602 የመደበኛ ፍርድ እና 54 የድንገተኛ ፍርድ (100%) መዝገቦች ተመርምረዋል። በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በኩል የተከሰሱ 10 ዳኞችና ተሿሚዎች ጉዳይም ታይቶ አስፈላጊው ውሳኔ ተሰጥቷል።

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በፕሬዚዳንት ወ/ሮ ትዕግስት ዳኛቸው፣ በምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ምትኬ ወርቁ እና በጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አላዩ አስፋው ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል።

የአብሮነትና የመዝናኛ መርሃ-ግብር፡
ከግምገማው በኋላ የፍርድ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች በዕሪኩም ሎጂ የአብሮነት የምሳ ፕሮግራም ያካሄዱ ሲሆን፣ በመጨረሻም በገበታ ለሀገር ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረው አዲሱ የሎጎ ሀይቅ ሪዞርት በመገኘት ጉብኝት በማድረግ ያማረ ጊዜ አሳልፈዋል።
​ #ደቡብወሎ #ከፍተኛፍርድቤት #ሀይቅ #የስራአፈጻጸም #ሎጎሀይቅ #ሪፖርትግምገማ

የደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት  የ2018 ጀት  ዓመት አመታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ ፡፡======++======++=======++=====++=======++========            ...
01/08/2026

የደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የ2018 ጀት ዓመት አመታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ ፡፡
======++======++=======++=====++=======++========
ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም
⏩ የደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት በአመቱ የተከናወኑ ስራዎችን ሪፖርት በፍ/ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አድስ በማቅረብ ዉይይት አደረገ፡፡
⏩ የደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኞች ፤የጉባኤ ተሿሜዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች በዉይይቱ የተሳተፎ ሲሆን የእለቱን ፕሮግራም የመክፍቻ ንግግር የፍ/ቤቱ ፕሪዝዳንት አቶ ሽመል አድስ አደድርገው በመቀጠልም የ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ ስራዎችን በእቅድ ባለሙያዎች የተዘጋጀዉን ሪፖርት ፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል፡፡
✅ በዚህም መሰረት በወንጀልና በፍታብሂር ጉዳዩች የመዝገብ አፈፃጸም በተመለከተ፡-
👉ከላፈዉ የተላለፈ-583
👉አደስ የቀረበ--9801
👉ከመ-ቤት የተንቀሳቀሰ--1533
👉ድምር አቅርቦት--11917
👉እቅድ--11321
👉ክንዉን--11164
👉ክንዉን ከአቅርቦት በፕርስንት 93.6 ሲሆን በይግባኝ በሂዱ መዝገቦች ላይ የመሻር፣ የመሻሻል፣የመጽናት ሆኔታን በሪፖርቱ በአሃዝና በዝርዝር ተገልጸዋል፡፡
✅በሽሪዓ፣በአስማሚ ችሎትና በተከላካይ ጠበቃ እንዲሆም ለበሌሎች ሄደቶች የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
✅የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ በበጀት አመቱ የተመደበ የስራ መስኪጃና የደመወዝ አጠቃቀሙን ገላጭ በሆነ ሪፖርት ቀርቧል፣በየቀበሌዉ 10 የባህል ፍርድ ቤቶችን አቋቁመናል፡፡
⏩በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በ12 ወሩ የታዩ ጠንካራ አፈፃጸሞችና፣በ12 ወሩ የታዩ ክፍተቶችን የገጠሙን ችግሮችና የተሰጠ መፍትሄ በስፋት በሪፖርቱ ቀርበዉ ተወያይተዉባቸዋል፡፡
⏩ ተወያዩችም በቀረበዉ ሪፖርት ላይ ጥያቂና አስተያየቶች በመስጠት ሁለቱ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪዎች አወያይ በመሆን የዉይይቱ ሀሳብ እንዲዳብር በመደረጉ በክፍተት የታዩትን መፍትሄ በመስጠት ለቀጣይ እንሰራለን ሲሉ ተወያዩቹ ገልጸዋል ፡፡
⏩ በመጨረሻም በበጀት አመቱ የሰራነዉ ስራ ጥሩ ነዉ ምክንያቱም ካለዉ የስራ ብዛትና የቤሮ ጥበት አንፃር ጠንክረን መስራታችንን ያሳያል ለቀጣዩ ችግሮችን እየፈታን የበለጠ በመስራት የተሸለ የስራ አፃጸም እንደምናመጣ አምናለሁ በማለት የእለቱን ዉይይት በስኬት ተጠናቋዋል፡፡
የደሴ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ህዝብ ግንኙነት

የደቡብ ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ በወንጀልና ፍትሐብሔር ክርክሮች ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት አስመለሰየደቡብ ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት ...
01/08/2026

የደቡብ ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ በወንጀልና ፍትሐብሔር ክርክሮች ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት አስመለሰ
የደቡብ ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታወቀ።

በመምሪያው የፍትሐብሔር የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብዱ ሙሳ በ2018 በጀት ዓመት የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የባከኑ ሀብቶችን ለማስመለስ በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን ገልፅዋል።

አስተባባሪው እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ቀድሞ የመከላከል አሠራርን በመከተልና ከሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብቶች እንዳይባክኑ ተደርጓል።

የወንጀል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ምናለ ደርሶልኝ በበኩላቸው በሙስና ወንጀል ረገድ የተመዘገበው ውጤት የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በበጀት ዓመቱ የቀረቡ 274 የሙስና መዝገቦች ተመርምረው ሙሉ በሙለ ውሳኔ አግኝተዋል።

በጥሬ ገንዘብ 170 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ 10,130 ካሬ ሜትር በሙስና የተመዘበረ መሬት ተወርሶ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ተደርጓል።

የደቡብ ወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም ሞላ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከልና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በፍትሐብሔር የሕግ ክርክር፣ በድርድርና በአፈጻጸም ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ (ከባለፈው ዓመት 37 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር እድገት ያሳየ) ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ተችሏል።በተጨማሪም በፍትሐብሔር በተከሳሽነት በኩል አላግባብ የቀረቡ ክሶችን በመሞገትና ምላሽ በመስጠት ከ347 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ገንዘብ ከወጪና ከኪሳራ ማዳን ተችሏል ብለዋል አቶ አብርሃም።
በሙስና ወንጀል ሥራ ሂደት ብቻ በወንጀል የተገኘና የባከነ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ተመልሶ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል።በወንጀል ኤግዚቢቶች፣ በዋስትናዎችና በልዩ ልዩ ገቢዎች ከ437 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተደርጓል።

በጥቅሉ በወንጀልና ፍትሐብሔር ክርክሮች ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት መምሪያው ማስመለስ እንደቻለም ተብራርቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ107 ሺህ በላይ ማህበረሰብ በ20 ደቂቃ የሚለካ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ከ237 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ አቶ አብርሃም አክለዋል።

ከዞን እስከ ወረዳ የቀረቡ ከ1ሽህ700 በላይ መዝገቦች ሙሉ በሙሉ ምላሽና ውሳኔ አግኝተዋል።በተጨማሪም የቀረቡ ከ4 ሽህ በላይ የወንጀል መዝገቦች መቶ በመቶ ተጣርተው የተጠናቀቁ ሲሆን፣ አቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት ተከራክሮ የማሸነፍ አቅሙን 94.97 በመቶ በማድረስ ከእቅዱ (90.5%) በላይ ማከናወን ችሏል።

መምሪያው ለአረጋውያን፣ ሕፃናት፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ነጻ የሕግ ድጋፍ በመስጠት የመሬትና የንብረት ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረጉን የገለጹት አቶ አብርሃም፣ በቀጣይም ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች የማስረጃ አቀራረብ ክፍተቶችና ከባለሙያዎች የስነ-ምግባር ክትትል ጋር ተያይዘው የሚነሱ አሰራሮችን በማጠናከር የህዝብና የመንግስት ሀብትን የማስጠበቅ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

ፈትህ መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ በለጎ ሐይቅ ሪዞርት አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶችን 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቀረበባሕር ዳር፣ ሐምሌ 24/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)የአማራ ክል...
31/07/2026

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶችን 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቀረበ

ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 24/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች 2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርበዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የተወሰደ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድ ከመታቀዱ በተጨማሪ በየደረጃው ያሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እቅድ ጋር የሚናበብ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና ዓመታዊ እቅድ እንዲያቅዱ ተደርጎ ወደ ሥራ የተገባ ስለመሆኑ ክቡር ፕሬዝደንት አቶ አለምአንተ አግደው ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡

የሥራ ተነሳሽነትን ፣ ትጋትን እና የሙያ ሥነ-ምግባርን በማሻሻል የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ በባለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው 438 ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ፍርድ ቤቶች የእውቅና እና ማበረታቻ መስጠት፣ እንዲሁም የጋራ ርዕይ ለመያዝ እና አቅም ለመገንባት በማለም 2185 የሚሆኑ የፍርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የተሳተፉበት የዳኞች ኮንፍረንስ የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የዳኝነት ነጻነት ለማረጋገጥ በፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ቁጥር 297/2017 መሰረት የዳኞች የሕግ ከለላ መረጋገጡ የዳኝነት ነጻነትን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና መጫወቱን የገለጹት ክቡር ፕሬዘዳንቱ፣ የዳኞችን የላቀ ሥነ ምግባር ለማረጋገጥ እና ተጠያቂነትን ከማምጣት አኳያ የዲሲፕሊን ደንብ በማውጣት እና የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የተሰሩ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ ፍ/ቤቶች የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓትን በመዘርጋት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን እና የችሎት ሥርዓት መመሪያ በማውጣት ውሳኔ የሚያገኙ መዛግብት ብዛት በመጨመር፣ የማጥራት አቅምን በማሳደግ እና የመዛግብት የመጨናነቅ ምጣኔን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመስራት በአጠቃላይ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡ መዛግብት 94.46 ከመቶ ለሆኑ መዛግብት እልባት በመስጠት ከፍተኛ የሆነ አፈጻጸም መመዝገቡን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሳደግ ለዳኞች የሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የውጪ ሀገራት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ከመደረጉ ባሻገር፣ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የሕግ ውይይት በማድረግ ጥራት እና ተገማችነት ያለው ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የእውቀት አስተዳደር ቋት እና ዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎት መተግበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከውጤት አንጻርም ጥራት ያለው ውሳኔ ሰጭነትን ለማሳደግ የታቀደው እቅድ በተሻለ ሁኔታ የተፈጸመ ስለመሆኑ ተገልጿል።

ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተደራሽ፣ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት የተላበሰ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በክልሉ ፍርድ ቤቶች ሰፊ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መሰራታቸውን ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው የገለጹ ሲሆን፣ የስማርት ኮርት፣ ኢ- ፋይሊንግ፣ ድምጽን ወደ ጽሁፍ መቀየር፣ የጥሪ ማዕከል፣ ድረ -ገጽ፣ የደብዳቤ ሥርዓት እና የመሳሳሉት የተሰሩ ሥራዎች በዝርዝር ተገልጸዋል። ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጨማሪ በሁሉም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በ27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች እና በባሕር ዳር እና እንጅባራ ማረሚያ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ስራዎች መሠራታቸው ተገልጿል።

ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢ -ፋይሊንግ ሲስተም በመጠቀም 16,606 መዛግብት የተከፈቱ ሲሆን ከአሜሪካን አገር ጆርጂያ ግዛት እና ሜሪላንድ ግዛት ምስክርነት ቃል መስጠት የቻሉትን ጨምሮ 2,564 ተገልጋዮች በስማርት ችሎት ወይም እርቀት ክርክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ብር 51,280,000 (ሃምሳ አንድ ሚሊዬን ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ) ወጪ ከማውጣት ታድጓቸዋል፡፡

ተገልጋዮች ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የሞባይል መተግበሪያ እና የተቋሙን ድረ- ገጽ በመጠቀም እንዲሁም በ 6152 የጥሪ ማእከል አማካኝነት መረጃ የሚያገኙበት አግባብ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።

አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ከማስፋት አንፃር የተሰሩ ስራዎችን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ የሆኑ ዘላቂ በሆነ ሁኔታ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት በጥናት ለተለዩ 15 የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጠት መቻሉን፣ 538 ሴቶች የሆኑበት የ7381 የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ መደረጉን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ 1377 ቀበሌዎች ውስጥ ሥራ ማስጀመር መቻሉን፣ በግንቦት እና በሰኔ ወር ብቻ 1195 መዛግብት ቀርበው ለ1048 መዛግብት እልባት መስጠት መቻሉ ተገልጿል።

በዚህም 29,943,887 ብር ወጪ መቀነስ መቻሉ ተገልጿል። በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት በማጠናከር 2485 መዛግብት በስምምነት መቋጨት መቻሉ ተገልጻል፡፡

የቅንጅት ሥራዎችን በማጠናከር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና አያያዝ የተሻለ ለማድረግ እና በሌሎች በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ እቅድ በማውጣት ሰፊ ሥራዎች ለመሥራት መቻሉ ተገልጿል።

ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ የሆነውን የክልሉ የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲቲዩት ለማጠናከር እና የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ለማስቻል የተሰሩ ሥራዎች በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

የፍርድ ቤቶች የሰው ሃብት ልማት እና ተቋማዊ ግንባታ፣ ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር አንጻር በዞን ከፍተኛ እና ወረዳ ፍርድ ቤቶች የተሰሩ ሥራዎች፣ የሕግ ግንዛቤ እና ማኅበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነት፣ የተጋላጭ የማህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችን እና ሌሎች ጉዳዮች በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ ፍርድ ቤቶች መኖር ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ተገማች፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ፍትሃዊ እና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አይተኬ ሚና ያላቸው መሆኑን ክቡር ፕሬዘዳንት አቶ አለም አንተአግደው ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ላነሷቸው ጥያቄዎችም ክቡር ፕሬዝደንቱ ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።© የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region

Address

Bahrdar Giyorgis

Telephone

0583210017

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የአብክመ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድቤቶች ዳኞች እና ዐቃቢያን ህግ ድምፅ.""". posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share

Category