Seba Dean Ethiopia

Seba Dean Ethiopia To Inform Best Info

ይነበብ
26/03/2022

ይነበብ

✴✅ ልብ ብለው ይህን ቀይ ስህተት.? ያንብቡ!! ✅✴
------------❀━┅┉┈ ┈┉┅━❀-------
ወጣቱ ልጅ ሚስት ሊያገባ በዋዜማው እለት ሽር ጉድ ላይ ሳለ እናት ድንገት ከዚህ አለም በሞት ትለየውና የሰርጉን ፕሮግራም ወደ አመት አዘዋወረው ። የማይደርስ የለምና ያ የቀጠሮ ቀን አመቱን አክብሮ ብቅ አለ ። ልጁም የሚፈልጋትን ሴት አገባ ። ያን ግዜ አባት በባዶ ቤት ብቻቸውን ሊቀሩ ተገደዱ ።

ምክንያቱም ባለቤታቸው ከሞተች በኋላ ከዚህ አንድ ልጃቸው ሌላ ማንም አልነበራቸውም ። ልጅም ከአዲሷ ሚስቱ ኑሮ ጀመረ ። ልጁ አንዳንዴ ሚስቱን ይዟት አባቱን ሊጠይቅ ይመጣል ። አንዳንዴ ደሞ እሱ አባቱን ጠይቆ እስኪመለስ እሷ ቤተሰቦቿ ዘንድ ትጠብቀዋለች ። ብዙ ግዜ የሷን ቤተሰቦች ብቻ እንዲጠይቅ ታስገድደው ነበር ።

በዚህ መልኩ አምስት አመታት ተቆጠሩ ። በዚህ ል እኚህን ምስኪን አባት በእርጅና ላይ በሽታው አዳከማቸው ። የአባቱ ሁኔታ ያሳሰበውም ልጅ አባቱን ቤት ሊወስዳቸው እና ሙሉ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ሲጠይቃቸው ። የልጁ ሚስቱ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው እንግዳ እንዳይሆኑ ስለስጉ ጥያቄውን አልተቀበሉትም ። ከዚያም የረጅም ግዜ የልጃቸው ውትወታ ለጥያቄው እጅ እንዲሰጡ አደረጋቸውና ልጃቸው ቤት ቀሪ ዘመናቸውን ሊያጠናቅቁ ብቅ አሉ ።

ያን ግዜ የልጃቸው ሚስት ደስታ ራቃት ። ሁለት አይነት ምግብ ማብሰል ጀመረች ለሽማግሌው በግዴለሽነት ትሰራና ታቀርብላቸው ነበር ። አባት ምግብ ብቻቸውን መብላት ቢከብዳቸው እንኳን ከልጃቸውና ከልጅ ልጆቻቸው አብረው መብላት አትፈቅድላቸውም ነበር ። የሚስቱ እና ያባቱ ሁኔታ ትንግርት የሆነበትም ልጅ በሁለት መዕበላት ውስጥ ሆኖ ይናወጥ ጀመር ከአባቴ ልሁን ወይስ ከሚስቴ !!!

ያን ግዜ ሚስት እንድ ሀሳብ ሰነዘረች ፦"ለምን ሚስት አናመጣላቸውም እነሱንም ትንከባከባለች እኛም እንገላገላለን" አለች ። ልጅም በዚህ እድሜያቸው አግብተው መኖር እንደማይችሉ ስላመነ አንድ አማራጭ ፊቱ ላይ ድቅን አለለት ። አረጋውያን ማቆያ/ሰው የሌላቸው ሽማግሌዎች የሚኖሩበት ድርጅት ውስጥ ሊወስዷቸው ወሰኑ እና ይዘዋቸው ሄዱ ። ልጁም ለዘመናት አብሮት የኖረውን የገዛ አባቱን በገዛ እጁ ገብቶ ማያውቅበት ግቢ ውስጥ አስገብቶት እንባውን እያፈሰሰ ተመለሰ ።

አባቱን እዛ ግቢ ውስጥ ካስገባቸው በኋላ በሳምንቱ ሊጠይቃቸው ወደ ግቢው ሲገባ አባት በብጣሽ ወረቀት መልዕክት አስቀምጠውለት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል ። መልዕክቱ እንዲህ ይል ነበር ፦

"ልጄ !!! ካሳለፍኳቸው ምርጥ ግዜያት ሁሉ ደስ የሚለኝ ድሮ ከስራ ስገባ አንተ ያለህበት ክፍል ገብቼ ላንተ መጫወቻዎችን ጣፋጭ ነገሮችን ስሰጥህ ነበር ።

ልጄ !!! ካሳለፍኳቸው ምርጥ ግዜያት ሁሉ ደስ የሚለኝ ዋና ላስለምድህ ገንዳ ውስጥ አንተን ተሸክሜ ምዋኝበት ግዜ ነበር።

ልጄ !!! ካሳለፍኳቸው ምርጥ ግዜያት ሁሉ ደስ የሚለኝ አንተ ህፃን እያለህ ቢሮ ይዤህ ስሄድ አንተም ቢሮ ውስጥ የሚጠቅሙኝን ወረቀቶች ስትቀዳድድብኝ በፍቅር ፈገግ እያልኩ የምመለከትህ ግዜ ነበር ።

ልጄ !!! በህይወቴ ካሳለፍኳቸው ምርጥ ግዜያት ሁሉ ደስ የሚለኝ ላንተ የምትፈልገውን ሁሉ ልብስ ልገዛ በኪሴ ያለውን ብር ባጠቃላይ ሳወጣ እና አንተ አምሮብህ እኔ ደሞ የተቀደደ ልብስ ስለብስ ነበር ።

ልጄ አሁን እኔ አንተን አልወቅስህም ። ነገር ግን በእንባ ተሞልቼ ይሄን ምፅፍልህ የኔ መጨረሻ እንዲህ ይሆናል ብዬ አስቤ ስለማላውቅ ነው ። የህይወቴ መጨረሻ ባንተ እቅፍ እንዲሆን ነበር ምኞቴ ። ውድ አባትህ" እንብቦ እንደጨረሰ እንባውን እያፈሰሰ ፀፀቱን ተሸክሞ ወጣ

በህይወት እስካላችሁ ድረስ አባታችሁን እናታችሁን እያገለገላችሁ ኑሩ። ቆም ብለክ አስብ አስቢ ።

ምርጥ መጣጥፎች
ሼርርርር

22/11/2021

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መከላከያን በግንባር ሆነው ለመምራት ከነገ ጀምረው ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ

**********
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መከላከያን በግንባር ሆነው ለመምራት ከነገ ጀምረው ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ አስታውቀዋል።

"ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለመላው ኢትዮጵያዊያን አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ያስተላለፋት መልዕክት እንደሚከተለው ይቀርባል።

ውድ የሀገሬ ልጆች፣
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት። ይሄን ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል። ድንበሯን ሊደፍሩ የሞከሩ አይበገሬ ክንዷን አይተዋል። ሊያስገብሯት የቋመጡ አቀርቅረው ተመልሰዋል። ክህደት ለፈጸሙባት ተገቢውን ትምህርት መስጠት፣ ከጀርባ የወጓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣትን ታውቃለች። ለሺህ ዘመናት የተጎናጸፈችው ነጻነትና ሉዓላዊ ክብር በችሮታ የተገኘ አይደለም። ያለ ዋጋ ነጻነትን አጽንቶ መጠበቅ አይቻልምና፤ ኢትዮጵያ የሚለው የነጻነት ስም የደም ዋጋ ተከፍሎበታል፣ ብርቱ ጀግኖች ሞተውለታል።

በታሪክ የምናውቃቸው አባቶቻቸው በአስተዳደርና በርእዮተ ዓለም ይለያያሉ፤ ለመብት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በነበራቸው አመለካከት ይለያያሉ። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ባላቸው ቦታ ግን ልዩነት አልነበራቸውም። በቋንቋ፣ በብሔርና በጎሳ ብዝኃነት ቢኖራቸውም የአልደፈርም-ባይ ቆራጥነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል። የግል ፍላጎታቸው የቱንም ያህል የተራራቀ ቢሆን፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነታቸው በላይ ይቀመጣል።

ድሮም ሆነ ዛሬ የእያንዳንዳችን ፍላጎት፣ የሁላችንም ሕይወት ከኢትዮጵያ በታች ነው። እኛ ኖረን ኢትዮጵያ ከምትሞት እኛ ሞተን ኢትዮጵያ እንድትኖር እንፈልጋለን። የሁላችንም የሆነች፣ ነጻነትና ፍትሕ የሰፈነባት፣ በገናናነቷና በነጻነቷ በዓለም አደባባይ የምትጠራ ሀገር እንድትኖረን ምኞታችን ነው። ለኢትዮጵያ ትልቅ በመመኘት፤ ሀገራችን አንገቷ ቀና እንዲል በመፈለግ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዐቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል። ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ ለማድረግ ሞክረናል። ካለፈው በጎውን ወስደን ጥፋቱን በይቅርታ ለማረም ተንቀሳቅሰናል። “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” ብለን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። የመለያየትና የጥላቻን ግንብ አፍርሰን የመደመርና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን ልንገነባ ቃል የገባነውን ወደ ተግባር ለመተርጎም ዐቅማችን የፈቀደውን አድርገናል።

ኢኮኖሚው እንዲያገግምና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፤ የዳኝነት ሥርዓታችን እንዲሻሻል፣ የሰብአዊ መብት አያያዛችን እንዲስተካከል፤ የውጭ ግንኙነት መርሐችን ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ታግለናል። በዚህ መካከል እንደ ሰው በርትተናል። እንደ ሰውም ደክመናል። እንደሰው አልምተናል፣ እንደ ሰውም አጥፍተናል። በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በኢትዮጵያ ክብርና በኢትዮጵያ ታላቅነት ግን ለአፍታም አዘንብለን አናውቅም።

ኢትዮጵያ የምታጓጓ ሀገር ናት። ከትናንትናዋ ይልቅ ነገዋ ታላቅ ነው። መከራ ማለፍ ነባር ችሎታዋ ነው። ይሄንን የገጠመንን መከራም እናልፈዋለን። ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል። በአንድ በኩል ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራሷ ፈቃድና በራሷ መንገድ ብቻ የምታድግ ኢትዮጵያ ላለማየት የጥፋት በትር ሰንዝረዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ ከተነሣች፣ ተነሥታም ካሸነፈች፣ ከዚህ በኋላ ለማንም የማትመለስ ትሆናለች። ይሄን አፍሪካዊ መንገድ ለማደናቀፍ ሁሉንም ዓይነት የክፋት መሣሪያዎች አሰልፈዋል። የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን የእነርሱን ብርታት በኢትዮጵያ ድካም ላይ ለመገንባት ተነሥተዋል። የኢትዮጵያ ፍላጎት ይዞ ማለፍ እንጂ ጥሎ ማለፍ አልነበረም፤ ለዚህ ነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በዋናነት ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ያደረግነው፤ ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ትግል ነው። ኢትዮጵያ አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው።

ጥቁር ሕዝቦች የራሳችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር እንዳይኖረን ሆን ተብሎ የሚደረግ አንገት የማስደፋት ትግል ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ እንዳያገኙ የተከፈተ ዘመቻ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ።

በመጨረሻም ይህ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ነው። ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው። በዓለም ላይ በክብር የምንጠራበት ስም እንዲኖረን የሚደረግ ትግል ነው። መኖር ወይም አለመኖራችንን የሚወስን ትግል ነው። ያለ ጥርጥር ግን እናሸንፋለን። ኢትዮጵያን ጠርቶ መሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።

ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ። ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ፡፡ የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ፡፡ በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው ይከውናሉ።

ጎልማሶች በዘዴና በብልሃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ፣ አረጋውያን እናትና አባቶች በጸሎት እየተጉ፣ ሁሉም ሰው ተባብሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋግጣል። ከዚህ በኋላ በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። መደረግ ያለበትን እኛው ራሳችን እናድርገው። ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም ነው፤ የነጻነት ምልክት ነው። አልጠራጠርም፣ የእኔ ትውልድ ለአሸናፊ ስሙና ለነጻነት ምልክቱ የሚጠበቅበትን ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር መዝገብ ላይ በወርቅ ብዕር ያትማል።

አመሰግናለሁ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ኅዳር 13፣ 2014 ዓ.ም

Address

Awassa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Seba Dean Ethiopia posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share

Category