11/07/2025
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የካምባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በ2017ዓ.ም በጀት ዓመት ከ998 በላይ የክስ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጠ።
የካምባ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በ2017ዓ.ም በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018ዓ.ም ጠቋሚ ዕቅድ ሰነድ ቀርቦ ውይይት በተደረገበት መድረክ የካምባ ከተማ መ/ደ/ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አክሊሉ ካሌብ እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ በፍትሐብሔር እና በወንጀል 1,011መዛግብት ቀርበዋል።
ከእነዚህ ከቀረቡ መዛግብት መካከል 998 መዛግብቶች ላይ ውሳኔ በመስጠት የዕቅዱን 98.7% መፈፀም ተችሏል ብለዋል። በተለያዩ የዳኝነት ሥራዎች ከ414,745 ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ገልፀዋል ፡፡ የማጣራት አቅም 100%፣ በስታንዳርድ የመወሰን አቅም 99%፣የፋይሎች መጨናነቅ ወደ 1.01መቀነሱን፣ውጤታማነት መዝገብ የማፅናት አቅም 99%መሆኑን አክለው ገልፀዋል።
ያለ እድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈር፣ በሴቶች ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ ቀለብ የመሳሰሉ የክስ መዝገቦች ጉዳዮች፣ ሸማቾች፣ ህብረት ሥራ፣ የማይክሮ ፋይናንስ ብድር አመላለስ በበጀት ዓመቱ ውሳኔ የተሰጠባቸው መዝገቦች ውስጥ በልዩ ችሎትና ልዩ ኩረት ተሰጥቶ ስለተሰራ በአብዛኛው 100% አፈፃፀም መመዝገቡን ገልጸዋል።
አማራጭ ሙግት የዕርቅ አፈፃፀም 256 መዝገብ 100% ሲሆን የተገልጋይ እርካታና አመኔታ ከማረጋገጥ አንፃር የተሻለ አፈፃፀም የታየበት ዓመት መሆኑን፣ ለ16ሰዎች ነፃ የህግ ድጋፍና ለ432ሰዎች የነፃ ህግ ምክር ተሰጥቶ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከ5891 ለሚበልጡ ባለ ጉዳዮችና ተገልጋዮች የንቃተ ህግ ትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠቱንም አክለው ገልፀዋል።
በመጨረሻም የበጀት አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን በማንሳት አስፈፃሚ መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና በፍ/ቤቱና በሠራተኛው ስም በማቅረብ ቀጣይ የተሻለና ከፍ ያለ ደጋፍና ቅንጅት በሚፈልገው በፍ/ቤቱ ህንፃ ቆሞ የቀረውን ለማስቀጠል ቆርጠው ድጋፍ እንድያደርጉም ጥሪ በማቅረብ የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ቀልጣፋ ለማድረግ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን የማሟላት ክፍተት የነበረውን በመቅረፍ ረገድ በቅንጅት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚፈልግ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ከአጠቃላይ ሰራተኞችና ክትትል አቀራረብ ፖሊሶች የተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጎ ምላሽ በመስጠት በ2018ዓ.ም ዕቅድ ላይ መክረው በቀጣይ በጀት ዓመት ፍርድ ቤቱ የውሳኔ አቅሙን በማሳደግ እና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። በመጨረሻ በዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሰራተኞች ማበረታቻና ሰርቲፍኬት በመሸለም እና ሠራተኛው ከፍሎ ያጠናቀቀውን የህዳሴው ግድብ ማስጨረሻ የተቆጠበ ቦንድ በማስረከብ ተጠናቋል።