Fasil Sileshi Law Office

Fasil Sileshi Law Office Our office is the place where you will get an excellent legal service with greatest care for our clients' needs and satisifaction.

የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማኅበር አዲስ አስተሳሰብ እና አመለካከት ባለው በሙያ ማኅበር መሪነትም አዲስ በሆነ ሰው ሊመራ ይገባዋል።ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ዘመኑን የዋጀ አመለካከት ባለው እና...
04/12/2025

የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማኅበር አዲስ አስተሳሰብ እና አመለካከት ባለው በሙያ ማኅበር መሪነትም አዲስ በሆነ ሰው ሊመራ ይገባዋል።
ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ዘመኑን የዋጀ አመለካከት ባለው እና ባለ ራዕይ በሆነ መሪ ነው።ለውጥ ከዚህ ይጀምራል።
አዲስ ፊት፤አዲስ ኢነርጂ፤አዲስ አመለካከት ለተሻለ የሙያ ማኅበር🙏

ለልደታ ምድብ ችሎት መረጃ ፈላጊዎች
07/08/2020

ለልደታ ምድብ ችሎት መረጃ ፈላጊዎች

17/06/2020

ክፍል 13

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ጉዳይ ዙሪያ መደራደር ግዴታችን ወይስ ምርጫችን?ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር እንየው እስቲ!

ባጠቃላይ አገራት በተለይ ጉዳዩ የአንድ አገር መብት ከሌላኛው አገር መብት አንጻር የሚወሰን ከሆነ እና አለመግባባት ካለ ድርድር ማድረግ ግድ እንደሆነ የዓለም አቀፍን ህግ ፈተሸ ፈተሸ ላደረገ እና መሰረታዊ የዓለም አቀፍ ህግ እውቀት ያለው ሰው የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ስለሆነም እንኳን እደራደራለሁ ብለህ ውል ፈርመህ ይቅርና ባትፈርምም በዓለም አቀፉ የልማድ ህግ መሰረት የአንድ አገር መብት የሌላኛውን አገር መብት የተመለከተ ጉዳይን በውስጡ ከያዘ ድርድር ግድ ነው፡፡የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ይህንን ጉዳይ ኖርዝ ሲ ኮንቲኔንታል እና ፊሸሪስ ጁርሲዲክሽን በተባሉ ክርክሮች ላይ በሰጠው ውሳኔ ትንታኔ ሰቶበታል፡፡ይህ ፍርድ ቤት በአንድ ጉዳይ ላይ የዓለም አቀፍ ህግ መኖሩን የሚረጋግጥ አንዱ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሶስቱ አገራት አለመግባባታቸውን በድርድር ለመፍታት በግልጽ ተፈራርመዋል፡፡ካልተስማሙባቸው ጉዳች አንዱ የግድቡ የውሃ አሞላል እና የግድቡን ውሃ አለቃቀቅ ትግበራ አንዱ ነው፡፡ስለሆነም በዚህ በዚህ ጉዳ ላይ መደራደራቸው ግዴታ ነው፡፡ግዴታ ነው ማለት ግን የግድ መስማማት አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ሙሌቱ እና የውሃ አለቃቅን በተመለከተ ስምምነት ካልተደረሰ በቀር ኢትዮጵያ ግድቡን አትገንባ፤አትሙላ፤አታስተዳድረው የሚል ህግ ግን የለም፡፡በተመሳሳይ ድርድር የይስሙላ ሳይሆን ውጤት ለማምጣት ያለመ እና የይስሙላ ያልሆነ መሆን እንዳለበት ዓለም አቀፍ ህግ ይነግረናል፡፡ከቅን ልቦና ውጪ በሆነ መልኩ ድርድሩን ከመራህ እና ድርድን ካቋረጥክ ደግሞ አላፊነት አለብህ፡፡ግብጽ ወደ ድርድሩ የመጣችው ብታቋርጥ ኢትዮጵያ ውሃውን ግብጽን ሳታማክር እንድትሞላ እድሉን በሰፊው ማግኘት ያስችላት ነበር፡፡ይህንን ስላወቀች ተመለሰች!

በመሆኑም ለምን በገዛ ግድባችን እንደራደራለን የምትሉ ወገኖች አስተያየታችሁ ከህጉ ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥ ይገባችኋል፡፡

ይልቁንም ለድርድር መስዋት የተደረገው ጉዳይ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ በኩል "እሺ እንደራደራለን" ብለው መፈረማቸው ነው፡፡የግድብ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ የአንድ አገር ሉዓላዊ ስልጣን ሆኖ ሳላ በግልጽ ለድርድር ጭዳ ባይደረግ ጥሩ ነበር፡፡ግን ጭዳ ባይደረግስ ኖሮ በጉዳዩ ላይ እንድንደራደር እንገደድ ነበርን?ብለን ስንጠይቅ መልሱ አዎን ነው፡፡ይህ መራር ዓለም አቀፋዊ አሰራር ሃቅ ነው፡፡ምክንያቱም ጉዳዩ የኢትዮጵያ መብት የግብጽ እና የሱዳንን መብት የሚነካ ስለሆነ፡፡

መብቷ የነሱን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይጎዳል?ከራሷ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብት በላይ ሆኖ እነርሱን ይጎዳል?የሚለው ሌላ ጉዳይ ቢሆንም፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ ከክፍል 1 እስከ 12 በነበረን ውይይት ስለመለስነው እርሱን ዞር ብሎ ማስታወስ ወይም ማንበብ ጠቃሚ ሲሆን ከኤፍ ኤም 107.8 ጋር ባደረኩት ውይይት ውስጥ በዝርዝር ተመልሷል፡፡በዚሁ ፔጅ ልጥፍ ላይ ትላንት ስለለጠፍኩት እርሱን ማዳመጥ ጥቅሙ የላቀ ነው፡፡

04/06/2020

የዓባይ ውሃ በረከት ወይስ መርገምት?

ዓለም አቀፋዊ ህግ እይታዎች

ክፍል 11

11. ታሪካዊ መብት እና ዓለም ዓቀፉ ህግ ምን እና ምን?

11.1. በተለምዶ "ታሪካዊ መብት" እያልን የምንጠራው ነገር እውነት ታሪካዊ መብት የሚባል ነገር ኖሮ ነው? ካለስ ግብፅ ከየት አመጣቺው?ምን ማለትስ ፈልጋ ነው?

11.1.1. የታሪካዊ መብት ታሪካዊ የሆነ የታሪክ ትረካ ሲተረክ

በተለምዶ ታሪካዊ መብት እየተባለ የሚጠራው የመብት አይነት ስሙ ተደጋግሞ ሲጠራ እውነትም በህግ የታወቀ ጽንሰ ሃሳብ መስሏል፡፡ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል እንደተባለው ማለት ነው፡፡

ታሪካዊ ዳራውን ስንመለከት "ታሪካዊ መብት" የሚለው ሃረግ ለመጀመሪያ ግዜ ጥቅም ላይ የዋለው የአንግሊዝ መንግስት እ.ኤ.አ በ1925 ዓ/ም የዓባይ/ናይል ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ ይልቁንም በሱዳን ውስጥ ለመስኖ አመቺ ሁኔታዎች ያሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥናት አደርጎ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን ያቋቁማል፡፡ኮሚሽኑም ጥናቱን ሰርቶ በሱዳን ውስጥ ለመስኖ አመቺ ሁኔታ መኖሩን እና ይህም መስኖ ሲጀመር ግብጥን የማይጎዳ መሆኑን አረጋግጦ ሪፖርቱን አቀረበ፤

አስቀድሞ ተደረጎ በነበረ ጥናት እንግሊዝ በሱዳን ውስጥ አያሌ የመስኖና የግድብ ግንባታ ስራዎችን ለመጀመር ስትንቀሳቀስ ሱዳን ውስጥ እና ግብጽ ውስጥ ያሉ የእንግሊዝ ባለስልጣናት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፤ልብ አድርጉ ጉዳዩ በእንግሊዝ እና በእንግሊዝ መካከል የሚደረግ ነበር፡፡ምክንያቱም ሁለቱም አገራት በእንግሊዝ አገዛዝ ስር ነበሩና ነው።

ዞሮ ዞሮ በኮሚሽኑ ሪፖርት መሰረት ሱዳን ውስጥ ሊሰሩ ስለታሰቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች የወቅቱ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስቴር አህመድ ዚዋር ፓሻ ስጋቱን በመግለጽ ሱዳን ለሚገኘው የእንግሊዝ ሹም ደብዳቤ ይጽፋል፡፡የደብዳቤውም ይዘት "በሱዳን ውስጥ የምትሰሩት የመስኖ ስራ በምንም ተዐምር የግብጽን መስኖዎችም ሆነ የወደፊት እቅዶች የሚጎዳ መሆን የለበትም፤በፍጥነት እያደገ ያለውን የግብጽን ገበሬዎች የውሃ ፍላጎት ታውቁታለችሁ፤ገበሬዎችም እየበዙ ነው።የእንግሊዝ ንጉሰ ነገስት ይንን ጉዳይ በደንብ ይገነዘባል።የሚል ታላቅ ተስፋን አደርጋለሁ፡፡" ብሎ ሲጽፍ እዛው ካይሮ ያለው የእንግሊዝ ሹመኛ የመንግስቱን ሃሳብ ያንጸባረቀ ምላሽን ይሰጣል፡፡የመልሱም ይዘት "ለ40 ዓመታት የግብጽን የእርሻ እድገት ሲያረጋግጥ የነበረው የእንግሊዝ መንግስት የሱዳንን እድገት ቢፈልገውም ቅሉ ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብት ለመተላለፍ ምንም አይነት ሃሳብ እንደሌለው እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡"የሚል ነው።ይህ ደብዳቤ ነው እንግዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ታሪካዊ መብት ወይም ተፈጥሯዊ መብት የሚለውን ነገር ያነሳው።ሞኝ እና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንዲሉ ይህንን ይዛ ዛሬም ታደነቁረናለች አጅሬ!

እነዚህ የደብዳቤ ልውውጦች ሁለቱ አገራት እ.ኤ.አ በ1929 ዓ/ም ባደረጉት የውል ምምነት አባሪ ሰነዶች ሆነው ተያይዘዋል፡፡

ከላይ የጠቀስነው እና በ1925 ዓ/ም የተቋቋመው ኮሚሽን ባጠናው ጥናት ላይ ከተገለጹት ቴክኒካዊ ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ጭብጥ ከጥር እሰከ ሃምሌ ያለውን የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት ለግብጽ ብቻ እንዲሆን እና ሱዳን ውስጥ ከጥናቱ በፊት ለነበረው ገዚራ የሚባለው የመስኖ እርሻ የሚያስፈልገውን ውሃ ደግሞ ከሓምሌ መጨረሻ እስከ ታህሳስ ወር ያለውን የወንዙን ፍሰት ብቻ እንዲጠቀም፣ከየካቲት በኋላ ደግሞ ሴናር ከተባለው እዛው ሱዳን ከሚገኘው ግድብ ውስጥ ከተጠራቀመው ውሃ እንዲጠቀም የሚበይን ሪፖርት ወይም ጥናት ነው፡፡

ይህም የኮሚሽን ሪፖርት በቁጥር ሲገለፅ ግብጽ በዓመት 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንድትጠቀም ሱዳን ደግሞ 4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን እንድታገኝ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ነበር፤ይህ የውሳኔ ሃሳብ ነው በ1929 ዓ/ም ስምምነት ውስጥ የተካተተው፡፡

ግብጽ ይህንን ስሌት እና የወንዝ ፍሰት ነው እንግዲህ "ታሪካዊ መብቴ" እያለች የምታደነቁረን! የሷ ታሪካዊ መብት በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ አልነበር? ነገር ግን የታሪካዊ መብቷ ታሪክ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ቀጣዩን በክፍል 12 እንመለስበታለን፡፡
እስከዛው እራችንን ከአስከፊው ኮሮና በሽታ በከፍተኛና በተጋነነ ሁኔታ እየጠበቅን እንቆይ!ምክንያቱም የተያዡ ቁጥር እያሻቀበ ነውና።ይህ ማለት ደግሞ ወደኛ የመዛመት እድሉን እያሰፋ መቷል ማለት ነው።የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና!

30/05/2020

የዓባይ ውሃ በረከት ወይስ መርገምት?
ዓለም አቀፋዊ ህግ እይታዎች

ክፍል 10

10.1. የምክንያተዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ ግንኙነት፤የትኛው የበላይ ነው?

የሁለቱ መራህያን አለመጣጣም የ1997 ዓ/ምቱ የተመድ ድንበር ተሸጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ስምምነት ነፍስ ዘርቶ፤ህይወት አግኝቶ ተፈጻሚ ለመሆን 50 ዓመታን እንዲፈጅ ዋነኛ ምክንያት ነበሩ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡
በቀደሙት ክፍሎች ስለ ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን በዝርዝር እንዲሁም ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህን ደግሞ በአጭሩ ተመልክተናል፡፡ዛሬ ሁለቱ መርሆች ይጋጫሉ?ከተጋጩ የትኛው የበላይ ነው?የሚለውን ጥያቄ መልሰን ግዜ ካገኘን ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድባችን ውይይት እንገባለን፤

ወደ ተነሳንበት ርዕስ ስንገባ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ እየተመለከትነው ባለው ህግ አንቀጽ 7 ስር የተደነገገ ሲሆን አቀራረጹን ስናይ አንድ አገር ጉልህ ጉዳት ማድረስ የለበትም ሲባል እንዴት የሚለውን መልስ ይሰጠናል፡፡መልሱም አንድ አገር #ወንዙን ስትጠቀም በሌላኛው አገር ላይ ጉዳት አታድርስ; ሲባል ወንዙን ሲጠቀም በተቻለው አቅም ጉዳት እንዳይደርስ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስድ ነው፡፡ልክ እኛ አሁን ማስክ እንደምናደርገው፤ሳኒታይዘር እንደምንጠቀመው እና ርቀታችንን እንደምንጠብቀው ማለት ነው፡፡ይህንን ሁሉ ጥንቃቄ አድርገን ኮሮና ሊይዘን(የሰይጣን ጆሮ ይደፈን) ወይም ወደሌላ ሰው ልናስተላልፍ እንችላለን፡፡ኮሮኖ የያዘው ሰው ደግሞ ወደ ሚመለከተው ጤና ተቋም/ማገገሚያ ሄዶ ጤናውን ይከታተላል፡፡ተከታትሎም ወይ ያገግማል ወይ ከዚህ ዓለም በይህወት ያልፋል(የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና)
በድንበር ተሻጋሪ ወንዝም አጠቃቀምም ልክ እንደዛው ነው፡፡ለምሳሌ አንድ አገር ግድብ ከገነባች ወይም ስተገነባ በሌላኛዋ ተፋሰስ አገር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባት፡፡ለምሳሌ ግድቡ ተደርምሶ በታችኛው አገር ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳይከሰት፤ውሃው ተበክሎ የስነ ምህዳር መዛባት እና ውሃውን በሚጠቀሙት ህይወት ባላቸውም ሆነ በሌላቸው አካላት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፤ውሃው በጉልህ ሁኔታ ቀንሶ በታችኛው ተፋሰስ አገር ቀድሞ ጥቅም ላይ እየዋለ ባለው እና ወደፊትም ቢጠቀም ውሃው እንዳይቀንስበት ተገቢወን ጥንቃቄ ማድረግን ሲሆን የታችኛው ተፋሰስ አገር ከሆነ ደግሞ በተመሳሳይ ግድብ ሲገነባ፤ለመስኖ ሲያውለው ወይም በማናቸውም መልኩ ሲጠቀመው የላኛው ተፋሰስ አገር ወደ መጠቀም ሲሸጋገር አጣብቂኝ ውስጥ እዳይገባ ጥንቃቄ የተሞላው አጠቃቀም ግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ለምሳሌ እጅግ ብዙ ሚሊናት ሰዎች ውሃውን እንዲጠቀሙት አድርገህ ሌላኛው ተጋሪ አገር ለመጠቀም ሲሞክር #እኔ እኮ ብዙ ህዝብ የያዝኩበት ነው!ለኔ የህይወት ጉዳይ ነው!; እንዳትል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ውሃውን የሚያባክን አጠቃቀም ወይም ውሃውን ለማይመለከተው ከተፋሰሱ ውጪ ላለ አገር ወይም አጠቃቀም ባለማዋል ሌላኛው ተጋሪ አገር ነገ ሲጠቀም እንቅፋት የማይፈጥር አጠቃቀምን ተግባራዊ በማድረግ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥንቃቄ ማድግንም ይመለከታል፡፡እንጂ የግድ የላኛው ተፋሰስ ብቻ በታችኛው ተፋሰስ ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ ይጠንቀቅ ማለት አይደለም፡፡በመሆኑም ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ የህግ ግዴታ በሁለቱም ተፋሰስ ማለትም የግርጌውንም ሆነ የራስጌውን ተፋሰስ አገር ይመለከታል ማለት ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ በህጉ/በስምምነቱ እንደተመለከተው አንድ አገር ወንዙን ሲጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ ነገር ግን ጉልህ ጉዳት ካደረሰ ማድረግ የሚጠበቅበት ቀጣይ ተግባር ቢኖር ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አንድም ጉዳቱ እንዲቀር የተቻለውን ማድረግ ካልቻለ ጉዳቱ እንዲቀንስ ጥረት እንዲያደርግ ነው፡፡በተጨማሪም ጉዳት አድራሹ አገር ጉዳቱን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ በሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ግምት ውስጥ እያስገባ ጉዳት ከደረሰበት አገር ጋር መነጋገር እንዳለበት እና ንግግሩ ጉዳት ማስቀረትን እና መቀነስን ብቻ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ስለ ካሳ ክፍያም ሊሆን ይችላል፡፡ሲል ህጉ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡እዚህ ጋር አስፈላጊውን ጥንቃቄ፤ጉዳን ማስቀረት፤ጉዳቱን መቀነስ፤ምክንያታዊ አጠቃቀምን ግምት ውስጥ ያስገባ፤እንዳስፈላጊነቱ ስለካሳም ይነጋገሩ የሚሉትን ቃላት እና ሃረጋት ስንመለከት አንድ አገር ግዴታው ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያድርግ እንጂ ፈጽሞ ጉዳት እንዳያድርስ አይደለም፡፡ጉዳት እንዳይደርስ ሲጠነቀቅ ደግሞ ምክንያታዊ አጠቃቀምን ግምት ውስጥ እንዲያስገባ የተፈቀደለት ውሃውን ሲጠቀም ገና ለገና ጉዳት አደርሳለሁ ብሎ እንዳይሸማቀቅ እና ጉዳት ቢያደርስም አጠቃቀሙ ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ ችግር እንደሌለው ሲያጠይቅ ነው፡፡

ለማጠቃለል በዛሬው ውይይታችን በሁለቱ መርህዎች መካከል ግጭት መኖሩን በደንብ የተገነዘብን ሲሆን፤ነገር ግን ከአናቅጾቹ አቀማመጥ እና ይዘት አንጻር ስንመለከት ትልቅ ቦታ የተሰጠው እና የበላይ ሆኖ የተገኘው ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ አጠቃቀም መርህ መሆኑን ተረድተናል፡፡በተጨማሪነትም የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ከላይ የተመለከትነው ዓለም አቀፍ ህግ በጸደቀ በ4ኛው ወር ላይ በቼኮስሎቫኪያ እና በሃንጋሪ መካከል ዳኑብ በተባለ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በተነሳ አለመግባባት በሰጠው ውሳኔ በወንዙ አጠቃቀም በአንደኛው አገር ላይ ጉዳት መድረሱ ቢታወቅምለእንዲሁም ጉዳት ይደርስብኛል እያለ ቢከራከርም ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው መሰረት ያደረገው ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ አጠቃቀምን ነው፡፡የሚገርመው ነገር ፍርድ ቤቱ ስለ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ ምን ያለው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡በጣም የሚገርመው አይደለም ስለ ጉለህ ጉዳት ስለ ትንሽ ጉዳትም አለመናገሩ ነው፡፡

እስካሁን ከተወያየንባቸው ጉዳዮች አንጻር የኢትዮጵያ እና የግብጽ አለመግባባት ከዓለም አቀፉ ህግ አንጻር እና ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቢሄድ ምን ተብሎ ሊወሰን እንደሚችል በቀላሉ መገመት ትችላላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

30/05/2020

የዓባይ ውሃ በረከት ወይስ መርገምት?
ዓለም አቀፋዊ ህግ እይታዎች

ክፍል 9

9. መርህ 2

9.1. ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ/ህግ

ባለፈው በክፍል 8 ውይይታችንን የፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ያየን ሲሆን በተጨማሪነት ደግሞ ይህንን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ ግምት ውስጥ መግባት ስላለባቸው ነገሮች በዝርዝር አይተናል፡፡ነገር ግን የድንበር ተሸጋሪ ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ ገዢ የሆነው ዓለም አቀፍ ህግ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ብቻ ሳይሆን ውሃውን የሚጠቀመው አገር በሌላኛው አገር ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስ የሚከለክልም ህግ/መርህ አለ፤እርሱም ጉልህ ጉዳት ያለማድስ መርህ በመባል ይታወቃል፡፡
ይህ መርህ እየተመለከትነው ባለው የ1997 ዓ.ምቱ የተመድ የድንበር ተሸጋሪ ወንዝ አጠቃቀም ህግ ወይም ስምምነት ላይ በአንቀጽ 7 ስር የተደነገገ ሲሆን አንቀጽ 5 እና 6 ደግሞ ምክንያታዊ አጠቃቀም እና የምክንያታዊ አጠቃቀም መለኪያ መስፈርቶች እንፈቅደም ተከተላቸው ተቀምጠው እናገኛቸዋለን፡፡

ከአንቀጽ 7 አገላለጽ የምንረዳው እያንዳንዱ አገር ድንበር ተሸጋሪ ወንዝን ሲጠቀም በሌላኛው የወንዙ ተጋሪ አገር ላይ ጉልህ ጉዳትን እንዳያደርስ የተከለከለ መሆኑን ነው፡፡
ይህ ጉልህ ጉዳት የተባለው አገላለጽ ትርጉም ቢፈልግም ትርጉም አልተሰጣውም፡፡ለመሆኑ ምን አይነት አጠቃቀምን ነው በሌላኛው ተፋሰስ አገር ላይ ጉልህ ጉዳት ያደርሳል የምንለው?ይህ ነው ከባዱ ጥያቄ ወይም ፈተና እና እስካሁንም ምላሻ ያላገኘው፡፡እያንዳንዱ አገር ለርሱ በሚጠቅመው መልኩ እየተረጎመው ጉዳዩ ቅጥ አምባሩ እንዲጠፋ ሆኗል፡፡ለምሳሌ ግብጽ ከውሃው ላይ በኩባያ እንኳን ቢቀንስ ጉልህ ጉዳት ይደርስብኛል ትላለች፡፡ኢትዮጵያ ደግሞ በመጀመሪያው የግድቡ የሙሊት ደረጃ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብይዝ፤በሁለተኛው ዓመት 18 ብይዝ በቀጣይ እንደ እቅዴ ብሞላ ጉልህ ጉዳት አላደርስብሽም እያለች ጉልህ ጉዳትን በገባት መጠን ትተረጉመዋለች፡፡

እንግዲህ ከውይይታችን የምንረዳው ለአንዱ አገር ምክንያታዊና ፍትሃዊ አጠቃቀም ለሌላኛው አገር ጉለህ ጉዳትን የሚያደርስ አጠቃቀም ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡በመሆኑም በሁለቱ መርሆች መካከል ግጭት ያለ ይመስላል ማለት ነው፡፡በሁለቱ ምርሆች መካከል ግጭት አለ ከተባለ ደግሞ አንዱ መርህ አሸናፊ መሆኑ የግድ ነው፡፡እየተጋጩ መቼስ ለግጭት አፈታት መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም፡፡አንድን አላማ መሰረት አድርገው የተረቀቁ ህጎች እየተጣሉ ሊኖሩ አይችሉም፤ራሳቸው እየተጣሉ አገራትን ሊያስታርቁ በፍጹም አይችሉም፡፡በአንድ ህግ ውስጥ በሁለት አናቅጽ መካከል ግጭት ከተከሰተ ደግሞ በህግ መሃንዲሶች ዘንድ መፍትሄ አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያላባራው አታካሮ አንዱ መነሾ የነዚህ ሁለት ዓለምአቀፍ መራህያን አልተስማምቶሽ ምክንያት ነው፡፡ወደው እንዳመስላችሁ፡፡ለማንኛውም የሁለቱን አናቅጽ ውስጠ ምስጢር እና አፈታት በቀጣይ ክፍሎች እናያለን፡፡ደና እደሩልኝ!

28/05/2020

የዓባይ ውሃ በረከት ወይስ መርገምት?

የዓለም አቀፉ ህግ ምን ይላል? ፖለቲካዊ ወ ዲፕሎማሲያዊ እንድምታዎች

ክፍል 8

ባለፈው በክፍል 7 ውይይታችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1997 ዓ/ም ያጸደቀውን፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚነት ያለውን፤የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ የድንበር ተሸጋሪ ወንዝ ህግ ነው ተብሎ የሚታወቀውን ስመምምነት አወላለድ እና ከመጽደቁ በፊት የነበሩትን አወዛጋቢ&አጨቃጫቂ ነገሮችን በጥቂቱ ለማየት ችለናል፡፡ዛሬ ደግሞ ይዘቱን ይልቁንም ዐበይት መራህያኑን እናያለን፡፡መልካም ንባብ

በክፍል 1 ውይይታችን የዓለም አቀፍ ህግ አሰራርን አይተናል፤ለማስታወስ በአገራት መካከል ግጭት ከተናሳና ግጭቱን ለመፍታት የምንጠቀመው ዓለም አቀፍ ህግን ተጠቅመን ነው፡፡መጀመሪያ የምንጠቀመው የዓለም አቀፍ ህግ ምንጭ በተጋጩት አገራት መካከል የተፈረመ የሁለትዮሽ ስምምነት ወይም እነርሱ ፈራሚ የሆኑበት ማናቸውም ስምምነት መኖሩን በመፈተሸ ሲሆን ስምምነት ከሌለ በልማድ የዳበረ ዓለም አቀፍ ህግን በመፈተሸ ነው፡፡ይህም ከሌለ ሌላ የዓለም አቀፍ ህግ ምንጭ ተብለው የሚታወቁ ያሉ ሲሆን ለአሁን ውይይታችን አይጠቅሙንም፡፡ምክንያቱም ለተነሳንበት የዓባይ ውሃ እና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሁለቱ ያለም አቀፍ ህግ ምንጮች ስለማይወጣ ነው፡፡ዓለም አቀፍ የልማድ ህግ ደግሞ ፈራሚ አገር ሆንክ አልሆንክ ያስገድድሃል፡፡ስምምነት ደግሞ የግድ በፈራሚዎች ላይ ብቻ ይሰራል፡፡

በዚሁ አግባብ ከላይ የጠቀስነው የ1997ቱ የተመድ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሸጋሪ ወንዝ ስምምነት በስምምነቱ ውስጥ 35 አገራት ፈርመው በየፓርላማቸው ሲያጸድቁ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ስለሚል የመጨረሻዋ አጽቂ አገር ቬትናም እ.ኤ.አ በ2017 ዓ/ም እንዳጸደቀችው ተፈጻሚነቱን አግኝቷል፡፡እንግዲህ ይታያችሁ በ1970 ዓ/ም የማርቀቁ ስራ የተጀመረው ስምምነት ከ47 ዓመታት ልፋት፤ድካም፤ድርድር፤ንትርክ፤ክርክር እና ጥናት በኋላ በአለምአቀፍ ደረጃ ውሃን የተመለከተ የመጀመሪያው ስምምነት ሊሆን በቅቷል፡፡ይህም ሲባል ፈራሚዎቹን አገራት ያለጭቅጭቅ የሚያስገድዳቸው ሲሆን ያለፈረሙትን አገራት ግብጽን፤ሱዳንን እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉንም የዓለም አገራት ያስገድዳል፡፡ምክንያቱም በውስጡ በልማድ የዳበሩ ምርሆችን ስለያዘ፡፡በልማድ የዳበረ ህግ ለምን አስገዳጅ እንደሆነ ከዚህ በፊት በነበረን ውይይት ስላነሳነው አልደግመውም፡፡

የህጉ/ስምምነቱ ይዘት

1. የፍትሃዊ እና የምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ፤አንቀጽ 5

ይህ መርህ ብዙ ግዜ በተለያዩ ሚዲያዎች እና ምሁራን ሲጠሩት እንሰማለን፤ሆኖም የአለም አቀፍ ህግ መሰረታዊ እውቀት ለሌለው ተደራሲ ብዙም ግልጽ ላይሆን ስለሚችለ እና የህጉ/ስምምነቱ መሰረታዊ እና ራስ በመሆኑ በመጠኑ እናየዋለን፡፡በዚህም መሰረት ይህ መርህ አገራት ድንበር ተሸጋሪ ወንዛቸውን በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ ሲሆን በአንቀጽ 6 ላይ ደግሞ አገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ተግባራዊ ሲያደርጉ ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ነገሮችን ዘርዝሯል፡፡ዝርዝሮቹ እነዚህ ብቻ ናቸው ሳይሆን ሚለው እንደነገሩ ሁኔታ እና ተፋሰሱ እንዳለበት ሁኔታ ሌሎች ነገሮችንም ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚቻል በሚጠቁም መልኩ ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ግምትውስጥ ይግቡ የተባሉትም ነገሮች ተፋሰስ አገሩ ወይም ወንዙ ያለበት አካባቢ(ጆግራፊ)፤የውሃው መጠን፤የውሃው ተፈጥሮ፤የአየር ጸባዩ(ክላይሜት) እና ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላቸው ማናቸውም ነገሮች ግምት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡ይህ ብቻ አይደለም የተፋሰስ አገራቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቻቸው፤በተፋሰስ አገራቱ ያሉት ህዝቦች በወንዙ ላይ ምን ያክል ጥገኛ ናቸው፤አንዱ አገር ውሃውን ሲጠቀም በሌላኛው አገር ላይ ያለውን ተጽእኖ፤አሁን እየተጠቀመ ያለው አገር እና ወደፊት ውሃውን መጠቀም በሚፈልግ ወይም መጠቀም በሚችለው አገራት መካከል ያለውን ሁኔታ(ይህንን ግልጽ ላመድረግ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ማለትም ግብጽ እስከዛሬ ስትጠቀም የኢትዮጵያን የወደፊት ወንዙን የመጠቀም መብትና አጋጣሚን ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባት ማለት ነው፡፡) ይህ ብቻ አደለም፡፡ሌላም ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡እነርሱም ውሃውን ሲጠቀሙ የወደፊቱን ትውልድ ጥቅምም ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ፤የውሃውን ደህንነት ማለትም እንዳይበከል&እናዳይቀንስ&ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን እንዳያጣ እና እነዚህን ነገሮችም ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡ ወጪዎችንም ታሳቢ እንዲያደርጉ፡፡ሲሆን በመጨረሻነት የተቀመጠው መስፈርት ልክ እንደወንዙ ወይም ወንዙ የሚሰጠውን ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ሌላ አማራጭ የተፈጥሮ ሃብት መኖርን ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ እና ይህንን ግምት ውስጥ ሲያስገቡ ወደፊት ለመጠቀም ላቀዱት እቅድም ሆነ አሁን እየተጠቀሙበት ላለው ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ተመልክቷል፡፡እነዚህ መስፈርቶች በተናጠል ሳይሆን ሁሉም አንድላይ ታይተው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ግብጽ አንዱን ነጥላ እያነሳች የምታደነቁረንን ነገር አስታውሱልኝማ! #እኔን ይጎዳኛል፡፡;የምትለውስ ነገር! አይጣል ነው!ካረጁ ብቻ ሳይሆን ከደነቆሩ፤ከተቸከሉ፤ከደረቁ፤ከነፈዙ፤አውቀው ከተኙ ወዘተ አይበጁ! ሊባልም ይገባል፡፡ይቆየን

ቁጥሩ እያሻቀበ ስለሆነ መጠንቀቁን ጠበቅ!ፈጣሪ ኮሮናን ያጥፋልን፤ያጠፋፋልን፤ዓለማችን ወደቀድሞ ቦታዋ እንድትመለስ ፈጣሪ/አሏህ ይርዳን፡፡እኛም ያጠፋነውን ይቅር ይበለን!ሃጥያቶቻችንን ይደምስስልን፤እኛም በቀጣይ ለመታረም ቃል እንግባ፤እንዋደድ፤እንከባበር፤አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ እንባባል፤ትህትናን ገንዘብ እናድርግ፤ይቅር ባዮች እንሁን፡፡እነዚህን አሁኑኑ ተግባራዊ ማድረግ እንጀምር!እርሱ ይርዳን አሜን!

26/05/2020

ያባይ ወንዝ በረከት ወይስ መርገምት?ከዓለም አቀፉ ህግ አንጻር

ክፍል 7

7.1 ውሃን አስመልክቶ ያለው አለም አቀፍ ህግ እድገት እና አሁናዊ ሁኔታ

ትላንት በነበረው ውይይታችን መንግስታዊ ያልሆኑ የአለም አቀፍ የህግ ሞያተኞች መሃበራት ላለም አቀፉ ድንበር ተሸጋሪ ወንዝ ህግጋት ያበረከቱትን ትሩፋት እና በተለይም ያለም አቀፍ ህግ ሞያተኞች መሃበር እ.ኤ.አ በ1966 ዓ/ም ያወጣውን እና ዘ ሄልሲንኪ ሩልስን አይተናል፡፡ይህ መመሪያ ለፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ ዘብ ቆሞ አለምን በዚሁ መርህ የበላይነት ሲመራ ቆይቶ እ.ኤ.አ እስከ 1997 ዓ/ም ድረስ አገልግሏል፡፡ይህ መርህ አለምን እየመራ ባለበት ሰዓት በመካከሉ ማለትም የተባበሩት መንስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1970 ዓ/ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም ዘንድ ተቀባይነት ያለው የውሃ ህግ ተረቆ እንዲቀርብለት በስሩ ለተቋቋመው የዓለም አቀፍ ህግ ኮሚሽን ስራ ሰቶ ስራው ደግሞ ማለትም የማርቀቁ ስራ 27 ዓመታትን ፈጅቶ በ1997 ዓ/ም ረቂቁ እስኪቀርብ ድረስ የሄልሲንኪ ሩልስ ስራ ላይ እንደ ነበር አይተናል፡፡ በክፍል 6 ውይይታችን፤በተጨማሪነትም የሄልሲንኪ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀምን እንዴት ወደ መሬት ማውረድ ይቻላል ለሚለው 11 መስፈርቶችን ዘርዝሮ ዝርዘሮቹ ደግሞ የመጨረሻ እንዳልሆኑ እና ሌሎች ሁኔታዎች እንደ አግባቡ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ክፍተት መተውኑም አይተናል፡፡ከ11ዱ መስፈርቶች መካከል አንዱ አገራት ውሃውን ሲጠቀሙ በሌላኛዎቹ ተፋሰሱ አገራት ላይ የሚደርሰውን ጉልህ ጉዳት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው የሚያትተው ክፍል ነው፡፡ጉልህ ጉዳት ማድረስ አንዱ ቅድመ ሁኔታ እንጂ የመስፈርቶች ሁሉ መስፈርት እንኳን አለመሆኑን አይተናል፡፡

ወደ ዛሬው ርእስ ስንመለስ ምንም እንኳን አያሌ ስምምነቶች እና የተለያየ ይዘት ያላቸው አለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ስምምነቶች ቢኖሩም አለም አቀፍ ተፈጻሚነት ያለው ህግ ተረቆ የጸደቀው የ1997 ዓ/ም ነው፡፡የማርቀቁ ሂደት 27 ዓመታትን የፈጀ እና 34 የሚሆኑ ከየ አገራቱ የተመረጡ ያለም አቀፍ ህግ ጠበብቶችን ያካተተ ቡድን የለፋበት ኮሚሲዮን ያረቀቀው ሰነድ ነው፡፡ሰነዱም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፊት ቀርቦ የተለዬዩ ትችቶችን አስተናግዶ፤ተሸሽሎ በክርክር እና በውይይት ዳብሮ እንደገና ተስተካክሎ በኮሚሲዮኑ በ1994 ጸድቆ በውይይት ዳብሮ የተመድ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በ1997 እ.ኤ.አ ተቀብሎ አጸደቀው፡፡አለም አቀፍ ተቀባይነት እና አስገዳጅነት ያለውን ህግ ለማርቀቅ ምን ያክል ፈታኝ እንደሆነ የወሰደውን ግዜ አይቶ መፍረድ የሚቻል ሲሆን የላኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አገራት አቋም መለያየት የፈተናዎች ሁሉ ፈታና ነበር፡፡

ለስምምነቱ መጽደቅ ወሳኝ ፈተናዎች እና የክርክር ርእሳን የነበሩት 3 ምክንያቶች ሲሆኑ እነርሱም 1ኛ አስቀድመው የተደረጉ ስምምነቶች እጣ ፈንታ እና ወደፊት በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ የሰነዱ ተጽእኖ፤2ኛ በሰነዱ እኩል እውቅና የተሰጣቸው የፍትሃዊ ወ ምክነንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሃውያን መስተጋብር እና በ3ኛ ደረጃ ደግሞ በሰነዱ የተመለከተው የግጭት አፈታት ዘዴዎች አጨቃጫቂና አወዛጋቢ ጽንሰ ሃሳቦች ነበሩ፡፡በአገራቱ መካከል የተካሄዱት ብርቱ ውይይቶች እና ጭቅጭቆች እንዳሉ ሆነው በ104 አገራት ይሁንታ፤በ3 አገራት ተቃውሞ እና በ26 አገራት ድምጸ ተዐቅቦ በማግኘት የጸደቀ ሲሆን፤ወደ አስገዳጅነት ለመቀየር የ35 አገራትን ፊርማና በየፓርላማቸው የማጽደቅ ቅድመ ሁኔታን በማስቀመጥ የተመድ በሚያዝያ 1997 ዓ/ም ያደረገውን ስብሰባ አጠናቋል፡፡

የስምምነቱ ይዘት ምን ይላል?ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ከጉልህ ጉዳት አለማድረስ መርህ አንጻር እንዴት ተቃኝ?ሎሎች አስገዳጅ መርሆዎችስ ምን ይመስላሉ?የሚሉትን ጥያቄዎች በክፍል 8 እንመለስባቸዋለን፡፡
እስከዛው ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ በአካላዊ ፈቅታ፤በእጅ መታጠብ እና ራስን በቤት ውስጥ በመወሰን፤ግዴታ መውጣት ካለብን ደግሞ ያፍና አፍንጫ መከለያን በማድረግ፤በማድረግ ብቻ ሳይሆን አድርገንም ከሌሎች ሰዎች 2 እርምጃ እርቀን እንድንጠነቀቀው አሳስባለሁ፡፡ደህና እደሩልኝ፡፡

25/05/2020

ዓለም አቀፉ የጠበቆች ማህበር ኢትዮዽያ የፍትህ ስርአቷን ለማሻሻል የወሰደችውን እርምጃዎች አድንቆ ቀጣይ ስራዎችን እንደሚያበረታታ እና ድጋፉን እንደሚቸር አስታወቀ።በተለይም ጠበቃው ሁሉ የግድ አባል የሚሆንብትን ማህበር Statutory Bar መቋቋም እንደሚደግፍ እና ለእንቅስቃሴው አድናቆቱን ቸሯል።ይህንን ይሚገልጸውን ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ልኳል።

ዝርዝር መረጃዎቹን ባማርኛ እና በእንግሊእኝስ ከስር ከተመለከተው ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይችላሉ።

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2524131134470698&id=2109591915924624
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2524130501137428&id=2109591915924624

Address

Chad Street
Addis Ababa

Telephone

+251911247463

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Fasil Sileshi Law Office posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Fasil Sileshi Law Office:

Share