06/09/2022
ይዞታ አስተዳደር ሰ/መ/ቁጥር 215098
በፕሮፖርሽን ካርታ ውስጥ ተካትተው የሚገኙ ይዞታዎች ውስጥ የሚገነቡ አጥርም ሆነ ሌላ ግንባታ ሊከናወን የሚችለው የግንባታ ፈቃድ ተጋሪ የሆኑ ግለሰቦች ለግንባታው ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ነው።
በዚህ መዝገቡ የችሎቱ ሐተታ እንደሚከተለው ይነበባል።
በተለያዩ ምክንያቶች መሬቱ ተከፍሎ መስጠት ካልተቻለ የተነፃፃሪ የመሬት ድርሻ ይዞታ ካርታ የሚሰጥ መሆኑ በይዞታ አስተዳደር አግልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 12/2004 አንቀፅ 13.1 የተመለከተ ሲሆን አሁን በተያዘው ጉዳይም ከላይ እንደተመለከተው ተጠሪዎችና አመልካቾች የመፀዳጃ ቤት የሚገነቡላቸው ግለሰቦች ለይዞታቸው ያላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በተነፃፃሪ የተሰጠ ሲሆን በዚህ አግባብ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከተሰጠ ደግሞ በጋራ በግቢው ውስጥ የሚኖሩ ባለይዞታዎች በጋራ ተስማምተው ካልመጡ በተናጠል ለማልማት የማይፈቅድላቸው መሆኑን ከአንቀፅ 13.6 እና ከተነፃፃሪ ካርታ አሰጣጥ አጠቃላይ ግብና አላማ ለመረዳት የሚቻል ሲሆን አሁን በያዝነው ጉዳይም የአሁን ተጠሪዎች መፀዳጃ ቤቱ እንዲገነባ ፈቃዳቸውን የሰጡ ስለመሆኑ የሚያመለክት ግልጽ ማስረጃ ወይንም የፈቃድ መስጫ ሰነድ ሆኖ ተረጋግጦ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩ፤ ቃለጉባኤውም በዚህ አግባብ የሚያረጋግጥ አለመሆኑ በስር ፍርድ ቤት የተረጋገጠ ከመሆኑ አንፃር የስር ፍርድ ቤቶች የተነፃፃሪ ካርታው ተጋሪዎች ፍቃድ ሳይገኝ በአመልካቾች በኩል መፀዳጃ ቤቱን ለመገንባት መንቀሳቀሳቸውን የሁከት ተግባር ነው ማለታቸው የሚነቀፍ ሆኖ [አልተገኘም]።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ይዞታ አስተዳደር አግልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 12/2004 አንቀፅ 13.1