25/08/2024
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሠራር ጥሰዋል ባላቸው ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ ጀመረ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢፌፖሚ):-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሠራር ጥሰዋል ባላቸው ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ ጀመረ።
ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሠራር በመጣስ ግርግርና ወከባ በፈጠሩ፡-
- በዮሀንስ ዳንኤል በርሄ፣
- በአማኑኤል መውጫ አብርሃ፣
- በናትናኤል ወንድወሰን ሹሜ፣
- በኤልያስ ድሪባ በዳኔ፣
- በይዲድያ ነጻነት አበበ እና
- በእሌኒ ክንፈ ተክለአብ በተባሉ ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋል የቻሉት በሀገራችን ካለው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የአየር መዛባት ምክንያት አውሮፕላኑ መብረር አይችልም ያሉ የበረራ ባለሙያዎችን በማስገደድ በረራውን ለማስቀጠል በፈጠሩት አምባጓሮና ግርግር ወንጀል ተጠርጥረው እንደሆነ የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ገልጿል።
የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ከተመሠረተባቸው የወንጀል ክስ በተጨማሪ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሽብር ወንጀልም መጠርጠራቸውን ጨምሮ ገልጿል።
በወቅቱ የአየር መንገዱ የደህንነት ኃይሎችና የበረራ ባለሙያዎች በትዕግስት ሁኔታውን ለማርገብ ቢማጸኗቸውም፣ ድብቅ አጀንዳቸውን እያራመዱ አሻፈረን ማለታቸውንም በወንጀል ምርመራ መዝገቡ ተካቷል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ የበረራ ሕግና አሰራርን በመጣሳቸው እንዲሁም በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በነገው ዕለት ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ፍርድ ቤት ፖሊስ እንደሚያቀርባቸው ታወቋል።