Abduljebar Hussein Law Office

Abduljebar Hussein Law Office Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Abduljebar Hussein Law Office, Lawyer & Law Firm, Adama.

ወራሽነትን ስለማጣራትና ስለ ውርስ አጣሪ =======================የሟች ውርስ ሟች በሞተበት ጊዜና ቦታ የሚከፈት ቢሆንም የሟች ውርስ እስከሚጣራ ድረስ የሟች ንብረት ''አንድ የተ...
09/08/2021

ወራሽነትን ስለማጣራትና ስለ ውርስ አጣሪ
=======================
የሟች ውርስ ሟች በሞተበት ጊዜና ቦታ የሚከፈት ቢሆንም የሟች ውርስ እስከሚጣራ ድረስ የሟች ንብረት ''አንድ የተለየ ንብረት፣፣ አንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ይኸም ማለት የሟች ንብረት ከሌሎች ሰዎች ንብረት ወይም ከወራሾቹ ንብረት ጋር ሣይቀላቀል የባለቤትነት መብቱ ለወራሾች ሣይተላለፍ እንደ አንድ ልዩ ንብረት፣ Distinct estate፣ ሆኖ መያዝ እንዳለበት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 942 ይደነግጋል፡፡ ይኸም የሚሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የሟች ውርስ ሣይጣራ ንብረቱ ከሌሎች ሰዎች ንብረት ጋር ቢቀላቀል ውርሱን ለማስተዳደርም ሆነ ለማከፋፈል የሚያጋጥመው ችግር ከባድ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ውርስን የማጣራቱ ሥራ በሟች የውርስ ስርዓት አፈጻጸም ውስጥ በቀላሉ የማይታይና እጅግ በጣም አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ የውርስ ማጣራት ሥራ በሟች የውርስ ስርዓት ለማስፈፀም አስፈላጊ ተግባር ነው ካልን የውርስ ማጣራቱን ተግባር ሀላፊነት ወስዶ የሚያስፈጽም አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መኖር አለባቸው፡፡ እነዚህ ውርሱን የማጣራት ተግባር የሚፈጽሙትን ሰዎች የውርስ አጣሪ በመባል ይታወቃሉ።


1. #ወራሽነትን ስለማጣራት

ውርስ ማጣራት ማለት፣
የሟች ወራሾች እነማን እንደሆኑ አጣርቶ መወሰን፣
የውርሱ ሀብት መጠን አይነትና ግምት እንደዚሁም የሚገኝበትን ቦታ አጣርቶ መወሰን፣
ሌሎች ሰዎች ከሟች የተበደሩትን ገንዘብ መሰብሰብና በሟች ውርስ ላይ ሊከፍላቸው የሚገቡ አስገዳጅ የሆኑ አዳዎችን አጣርቶ መክፈል፣
እንደዚሁም ሟች ልዩ የኑዛዜ ስጦታ ያደረጉላቸውን ሰዎች የተሰጣቸውን ልዩ የኑዛዜ ስጦታ መክፈል፣
ማለት እንደሆነ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 944 ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡

እነዚህ የውርስ ማጣራት ተግባራት በብቃት እስኪከናወኑ፣ የውርሱ ንብረት እንደ ናአንድ የተለየ ንብረትን እንደሚቆጠርና ከውርሱ ሀብት ላይ ገንዘብ ለመጠየቅ መብት ያላቸው ሰዎች ማለትም የሟች አበዳሪዎች እና የፍርድ ባለመብቶች ለገንዘባቸው ዋስትናና መያዥያ የሚሆናቸው ይኸው በመጣራት ላይ ያለው የውርሱ ንብረት ነው፡፡ ይኸም በመሆኑ ውርሱ በመጣራት ላይ እያለ ከሟች ወራሾች ገንዘብ ጠያቂ የሆኑ ሰዎች በውርሱ ንብረት ላይ አንዳችም የይገባኛል ጥያቄ ማቅረብ እንደማይችሉና ምንም አይነት መብት እንደሌላቸው ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 943/1/ እና 943/3/ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች የራሣቸው ጠቀሜታና ግብ አላቸው፡፡ ምክንያቱም የሟች ውርስ በሚጣራበት ጊዜ የሟች ወራሾች አበዳሪዎችና ገንዘብ ጠያቂዎች የውርሱን ንብረት በመያዥያነት አንዳይዙ የሚያደርገው የሟች ወራሾች ከውርሱ ንብረት ድርሻ ሊያገኙ የሚችሉት ከሟች እዳ የተረፈ ንብረት ሲኖር ብቻ በመሆኑ ነው፡፡
ህጉ የሟች ወራሾች አበዳሪዎች ውርሱ በመጣራት ላይ እያለ በውርሱ ንብረት ላይ የይገባኛል ጥያቄ እንዳያቀርቡ በሟች ወራሾች እዳ ምክንያት የውርሱ ንብረት በመያዣነት እንዳይያዝ የሚከለክል ነው፡፡
እንደዚሁም ውርሱ በመጣራት ላይ እያለ ከሟች ውርስ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ከሟች ወራሾች የግል ሀብት ላይ አንዳችም መብት እንደሌላቸው እና የሟችን የውርስ ንብረት ብቻ መከታተል እንዳለባቸው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 943 ድንጋጌዎች ያሣያሉ፡፡
እዚህ ላይ ውርስን ማጣራት አስፈላጊነት በመጀመሪያ ከሟች ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ውርሱ ከመከፋፈሉ በፊት ገንዘባቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ፣ በማስከተልም ከውርሱ በእዳነት የሚጠየቁ ለምሣሌ ለሟች የቀብር ስነ ስርዓት የወጣው ወጭ፣ ከውርሱ መከፈል ያለበት የቀለብ እዳ እና ሟች በልዩ ኑዛዜ የሰጣቸው ስጦታዎች በቅደም ተከተል ተከፍለው ሲያበቁ ነውና ከዚህ የተረፈ ንብረት ካለ ነው የሟች የሕግ ወራሾችና ጠቅላላ የኑዛዜ ተጠቃሚዎች ከሟች ውርስ ንብረት ድርሻቸውን ያገኛሉ፡፡

በመጨረሻም የውርስ ሕጋችን ወራሾችና የኑዛዜ ስጦታ የተደረገላቸው ሰወች ውርሱን ስለማጣራት ወይም ስለመካፈል በመካከላቸው በሚደረገው ክርክር ሁሉ አንድ ወይም ብዙ የዘመድ አስታራቂ ዳኞች እንዳያዩት ለመስማማት እንደሚችሉ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 945 ይደነግጋል፡፡

2. #የውርስ አጣሪ

ከላይ እንደተገለፀው ውርስን ማጣራት በሟች የውርስ ስርዓት አፈጻጸም ወቅት እጅግ በጣም አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ ይህንን ውርሱን የሚያጣራው ሰው ወይም ሰዎች የውርስ አጣሪ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የውርስ አጣሪ ከሶስቱ በአንደኛው መንገድ ሊሾም እንደሚችል የውርስ ሕጋችን ይደነግጋል፡፡ የውርስ አጣሪ፣

በሟች ኑዛዜ መሠረት፣
በሕግ ሊመረጥ ወይም ሥልጣኑን ከሕግ ሊያገኝ፣
በዳኞች ሊሾም ይችላል፡፡

የመጀመሪያውን በተመለከተ ሟች አንድ ኑዛዜ የተወ እንደሆነና ሟቹ በዚሁ ኑዛዜ ውስጥ የኑዛዜው አስፈጻሚ የሾመ እንደሆነ ሟች የመረጠው ሰው የውርሱ አጣሪ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሟች በኑዛዜ የውርስ አጣሪ የሾመ እንደሆነ ሟች በግልጽ በኑዛዜው ካላመለከተ በስተቀር በሟች ኑዛዜ ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ የተደረገለት ሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውርሱን የማጣራት መብት ይኖረዋል፡፡ ሟች የውርስ አጣሪውን በኑዛዜ የሾመ እንደሆነ ወይም ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ አድርጐ እንደሆነ ጠቅላላ ኑዛዜ ስጦታ የተደረገለት ሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውርሱን የማጣራት መብት በቅደም ተከተል ይኖራቸዋል፡፡ ሟች የውርስ አጣሪውን በኑዛዜ የሾመ እንደሆነ ወይም ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ የተደረገለት ሰው የተገኘ እንደሆነ የሟችን ያሉ ኑዛዜ ወራሾች የውርስ አጣሪነት ስልጣን የሚያስቀረው እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 948 ተደንግጓል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሟች በኑዛዜ የውርስ አጣሪ ያልሾሙ እንደሆነ ወይም ሟች ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ ያደረገለት ሰው የሌለ እንደሆነ የሟች ያለ ኑዛዜ ወራሽ የሆኑ ሰዎች ሰውየው ከሞተበት ቀን አንስቶ ያለ አንዳች ፎርማሊቲ የውርስ አጣሪነት መብት እንደሚኖራቸው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 947 የሚደነግግ ሲሆን ብዙ ሰዎች የውርስ አጣሪ በሆኑ ጊዜ የአጣሪነቱን ተግባር በመተባበር መስራት እንዳለባቸው ወይም አንዱን በመወከል ለማሠራት እንደሚችሉ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 958 ይደነግጋል፡፡

ሶስተኛው የውርስ አጣሪ የሚሰየምበት ስርዓት በፍርድ ቤት ውሣኔ የውርሱ አጣሪ የሚሰይምበት ሁኔታ ነው፡፡ የውርስ አጣሪ በፍርድ ቤት የሚሰየመው፣
የሟች ወራሾች የማይታወቁ አንደሆነ፣
ያለ ኑዛዜ ወራሾች ውርሱን ለማጣራት የማይፈቅዱ መሆናቸውን ገልፀው ያሣወቁ እንደሆነ፣
ሟች የኑዛዜም ሆነ ያለ ኑዛዜ ወራሽ ያልተወና የሟችን ሀብት መንግስት የሚወርሰው በሆነ ጊዜ፣
የአስተዳደር ሕጐችን ወይም ደንቦችን መሠረት በማድረግ ዳኞች የውርሱን አጣሪ እንደሚሰይሙ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 949 ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡

እንደዚሁም ዳኞች በሟች ኑዛዜ፣ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት የተሰየመውን የውርስ አጣሪ በሌላ የውርስ አጣሪ የመተካት ስልጣን እንዳላቸው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 951 ይደነግጋል፡፡ የውርስ አጣሪን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 949 መሠረት መሰየምንና በሕግ ወይም በሟች ኑዛዜ ወይም ፍርድ ቤቱ ራሱ የሰየመውን የውርስ አጣሪ መተካት /replacement / እና substitution/ ሁለት የተለያዩ ጽንሰ ሀሣቦች ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ በሕግ በሟች ኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤቱ የተሰየመን አንድ የውርስ አጣሪ ስልጣንና ሀላፊነት በማንሣት ሌላ/ሌሎች/ የውርስ አጣሪ የሚሰይመው፣
ውርስ አጣሪው የተሾመበት ኑዛዜ ዋጋ ያለው ኑዛዜ መሆኑ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ወይም፣
በሌላ ምክንያት ውርስ አጣሪውን በመለየት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ሲኖር ወይም፣
ብዙ ውርስ አጣሪዎች ለምሣሌ ስልጣናቸው 947 የሚመነጭ ብዙ ያለ ኑዛዜ ወራሾች ኖረው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 958 በሚደነግገው መሠረት ውርሱን በመተባበር በመግባባት ለማስተዳደርና ለማጣራት ያልተስማሙ እንደሆነ ወይም፣ ከወራሾቹ መካከል አንዱ አካለ መጠን የላደረሰ ልጅ ወይም የተከለከለ ሰው ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ለምሣሌ በአገር ባለመኖሩ፣ እብደቱ በግልጽ ያልታወቀ ሰው በመሆኑና በሌሎች ምክንያቶች ጥቅሙን ለማስከበር የማይችል በሆነ ጊዜ ወይም፣
የውርሱ አስተዳዳር ወይም የማጣራቱ ስራ ልዩ ችግር ያስነሣና ልዩ ሙያ ያላቸውን ሰወች ወይም ሌላ ችግሩን ለመቅረፍ የሚችል የውርስ አጣሪ መሰየም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም፣
በሕግ ሟች ኑዛዜ ወይም በዳኞች የተሰየመው አጣሪ ቸልተኛና ትጉህ ያልሆነ እንደሆነ ወይም የማጭበርበር ባህሪ የሚታይበትና ሀቀኝነት የጉደለው የሆነ አንደሆነ ወይም አጣሪው የማጣራት ስራውን በሚገባ ለመፈፀም ችሎታ የሌለው መሆኑ የታወቀ እንደሆነ፣
ዳኞች ከማናቸውም በጉዳዩ ያገባኛል ከሚል ባለጉዳይ ጥያቄ አቅራቢነት በሕግ፣ በኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሣኔ ተሰይሞ የነበረውን የውርስ አጣሪ በመሻር በአካባቢው ውል ለማዋዋል ስልጣን የተሰጠውን ሰው ወይም ማናቸውንም ለስራው ብቁ ነው ብለው የሚመርጡትን ሌላ ሰው በውርስ አጣሪነት ለመሰየምና ለመተካት እንደሚችሉ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 951 ተመልክቶ እናገኘዋለን፡፡

በውርስ ህጋችን በግልጽ እንደተመለከተው በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የተመረጠ ወይም የተተካ የውርስ አጣሪ የሚከተሉት ግዴታዎችና ሀላፊነቶች ይኖሩበታል፡፡
ሟች በህይወት ዘመኑ ያደረገው ኑዛዜ ካለ ኑዛዜውን መፈለግና የሟችን የኑዛዜ ወይም ያለኑዛዜ ወራሾች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ፣
የውርስ ንብረት ከብልሽትና ከብክነት ለመታደግ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድና ሌሎችንም አስፈላጊ ተግባራት በመፈጸም የውርሱን ሀብት ማስተዳደር፣
በግልጽ የታወቁ፣ ክርክርን የማያስነሱ መከፈል ያለባቸውን የውርስ እዳዎች በፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1014 በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሰረት መክፈል፣
ሟቹ በልዩ ኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎች መክፈልና የሟችን የኑዛዜ ቃል ለመፈጸምና ውጤት ለመስጠት ማንኛውንም አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ፣
ጥያቄው ያገባኛል በሚል ማናቸውም ባለጉዳይ ሲቀርብና ዳኞችን የሚያሳምን ሆኖ ሲገኝ ስለስራው መልካም አፈጻጸም አንድ ዋስ ወይም ሌላ የመልካም ስራ አፈጻጸም ማረጋገጫ ሊሆን የሚችል መያዣ ማቅረብ፣
ስራውን ለመተው ሲፈልግ አዲስ አጣሪ እስከሚሰየምና ተተክቶ ስራውን እስከሚጀምር ድረስ የአጣሪነት ስራውን የማከናወን፣
ሟች በአደረገው ኑዛዜ ስለአጣሪነቱ የስልጣን ወሰንና ስለስራው አፈጻጸም የሰጠውን መመሪያና ትእዛዝ ተከትሎ የመስራትና ዳኞችም ስለስልጣኑ ወሰንና ስለስራው አፈጻጸም የሚሰጡትን ትእዛዞች በማክበር የአጣሪነት ስራውን ማከናወን፣
ውርሱን አጣርቶ ከጨረሰ በኋላ ለወራሾቹ ስለማጣራቱ የስራ ክንውን ሪፖርት ማቅረብ፣
ውርስ አጣሪው ማናቸውንም የህጉን ድንጋጌዎች በሟች ኑዛዜ የተሰጡትን መመሪያዎች ወይም በዳኞች የተሰጡትን ትእዛዞች በሚቃረን በጥፋቱ ወይም በቸልተኝነቱ መንገድ ለሚያደርጋቸው ጉዳዮችና በዚያ መሰረት ለሚደርስ ጉዳት በሀላፊነት የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበት፣
ከፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 952፣ 954-957 እንደዚሁም የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 960 እና 961 በማየት መረዳት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ህጉ በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ በውርስ አጣሪነት ለሚሰየሙ ሰዎች ያስቀመጠላቸው መብት አለ፡፡ ከመብቶቹ መካከል እጅግ በጣም አስፈላጊው የውርስ አጣሪነት ስራ ማንም ሰው በፈቃዱ ብቻ ሊያከናውነው የሚገባና ማንም ሰው ያለፈቃዱ የአጣሪነት ስራዎችን ለመቀበል የማይገደድ መሆኑ ነው፡፡ አንድን ተግባር አንድ ሰው ተገድዶ እንዲያከናውን ማድረግ የተከለከለና መሰረታዊ የሆነውን የሰው ልጅ ነጻነት መብት የሚነካ በመሆኑ የውርስ አጣሪነትን ተግባር አንድ ሰው ሳይፈልግ እንዲቀበልና እንዲሰራ ማድረግ እንደማይቻል የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 953 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ሁለተኛው መብቱ ደግሞ ውርስ አጣሪው ስራውን እፍጻሜ ለማድረስ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ለመስራት በግልጽ ግዴታ የገባ ካልሆነ በቀር በማናቸውም ጊዜ ስራውን መተው የሚችል መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ ‹በግልጽ ግዴታ የገባ ካልሆነ በቀር› የሚለው ሀረግ ነው፡፡ በዝምታ በህግ፣ በሟች ኑዛዜ ወይም በዳኞች የውርስ አጣሪ ሆኖ እንዲሰራ መመረጡን ተቀብሎ ስራ መጀመሩ ብቻውን የማጣራት ስራውን በማናቸውም ጊዜ የመተው መብቱን አያስቀርበትም፡፡ ስራውን የመተው መብቱ ቀሪ የሚሆነው በግልጽ እራሱን ግዴታ ያስገባ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

ሌላው እዚህ ላይ መታየት ያለበት ውርስ አጣሪው ይህንን የማጣራቱን ስራ የመተው መብቱን እንደፈለገው ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ የሟች ውርስ ንብረት የግድ መጠበቅና በጥንቃቄ መያዝ ስለሚገባው ሌላ ተተኪ አጣሪ እስኪመረጥና ስራውን እስኪረከብ ድረስ ስራውን እየሰራ መቆየት ያለበት መሆኑ የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 954 ድንጋጌዎችን በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ለውርስ አጣሪ የተቀመጠለት መብት አጣሪው ውርሱን ለማጣራት ለሰራው ስራ የአገልግሎት ዋጋ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ ነው፡፡ የውርሱ አጣሪ የአገልግሎት ክፍያውን የሚያገኘው ሟች በኑዛዜው ውስጥ በሰጠው መመሪያ ወይም ወራሾቹ በሚያደርጉት ስምምነት ወይም ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ መሰረት ሊሆን እንደሚችል የፍትሀ ብሄር ህግ ቁጥር 959 ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም አጣሪው ውርሱን በማጣራት ለሰራው ስራና ግልጋሎት ከውርሱ ንብረት ላይ ከላይ ባስቀመጥናቸው ሁኔታዎች ሲወሰንለት የአገልግሎት ዋጋ የማግኘት መብት እንዳለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የውርስ ህግ መሰረት ‹ውርሱን ስለማጣራት› የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ምንነትና ይዘት እንደዚሁም ጠቀሜታ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ የመጀመሪያው በምእራፍ ሁለትም ለመጠቆም እንደተሞከረው ‹የሟች ውርስ መከፈት› እና ‹የሟችን ውርስ ማጣራት› የሚሉት ጽንሰሀሳቦች እጅግ በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ የሟች ውርስ መከፈት የምንለው ሟች ህይወቱ ካለፈበት ቅጽበት ጀምሮ ምንም አይነት የሲቪል መብት ግዴታ ሊኖረው ስለማይችል ህጉ የሟች ህይወት ካለፈችበት ሰኮንድ ጀምሮ የሟች መብትና ግዴታ ለሟች ወራሾች ለማስተላለፍ የሚያደርጋቸውን ጥንቃቄ የሚመለከት ነው፡፡

የሟች ውርስ የሚከፈተውም ሟች መኖሪያ ስፍራና ሟች በሞተበት ጊዜ እንደሆነ በፍትሀ ብሄር ህግ ቁጥር 826 ተመልክቷል፡፡ የሟችን ውርስ ማጣራት የምንለው ደግሞ የሟችን ያለኑዛዜና በኑዛዜ ወራሾች የሚለዩበት፣ የሟች እዳ የሚከፈልበት፣ የሟች አበዳሪዎች እና ተበዳሪዎች የሚለዩበት፣ ንብረቱ በሟች ወራሾች እስኪተላለፍና ውርሱ እስከሚዘጋበት ቀን ድረስ የንብረት ማስተዳደር ስራዎች የሚከናወንበት ውስብስብ ተግባር ነው፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው የውርስ ህግ አጣሪ ስለሚሆኑ ሰዎች ሲደነግግ ቀዳሚውና የመጀመሪያው የውርስ አጣሪ የሚሆነው ሟች በኑዛዜ የውርስ አጣሪ አድርጎ የሾመው ሰው እንደሆነ ከገለጸ በኀላ ሟች በኑዛዜ የውርስ አጣሪ አድርጎ የሾመው ሰው ከሌለና በኑዛዜው የውርስ አጣሪ እንደሚሆንና ጠቅላላ ኑዛዜ የተደረገለት ሰው መገኘት የሟችን ያለኑዛዜ ወራሾች የአጣሪነት ስራ እንደሚያስቀረው በፍትህብሄር ህግ ቁጥር 948 ንኡስ ቁጥር 2 እና 3 የሚደነግግ ሲሆን የሟች ውርስ መዘጋት ማለት ደግሞ የሟችን ንብረት ለወራሾች በአግባቡ የማከፋፈል ስራን አይጨምርም፡፡

የውርስ አጣሪው ሀላፊነት ከላይ ያነሳናቸውን ተግባር በመፈጸምና የሟችን ወራሾችና የሟች ከእዳ ተከፍሎ የሚቀረውን ንብረት በማጣራት፣ ዝርዝርና የመጨረሻ ሪፖርት ለወራሾቹ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የውርሱን ንብረት ማስተዳደርም ሆነ የሟችን ንብረት መከፋፈል የወራሾች መብትና ሀላፊነት እንጂ የውርሱ አጣሪ አይደለም፡፡
በመሆኑም ውርስ አጣሪ በዋነኛነት ሊፈጽማቸው የሚችላቸው ተግባራት፣
ከሟች ውርስ መብት አለን የሚሉትን ሰዎች ሁኔታ መወሰን፣
የሟችን የውርስ ንብረት ማስተዳደር፣
የሟችን የውርስ እዳ መክፈል፣ ናቸው፡፡
©℗®

https://t.me/Consultancy2012
Call us for
©Ethio - Legal Service

Legal Service

14/04/2021

በወንጀል ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው?
----------------------------------------------
ክፍል ሁለት፡-
ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌስቡክ ገጻችን ተከታታዮች በክፍል አንድ ዝግጅታችን ሁከት ሲባል ምን ማለት ነው?በፍትሓብሄር ህጎች ያለው ገጽታና በፍትሓብሄር ጉዳዮች ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች በሚል አርዕስት አንድ ጥንቅር ወደ እናንተ ማድረሳችን ይታወሳል፤ በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ በወንጀል ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆኑ ወደ እናነተ ለማድረስ ቃል ገብተን በተለያየነው መሰረት፤ እንሆ ዛሬ በቀጠሯችን ክፍል ሁለትን ወደ እናንተ እናደርሳለን ከወዲሁ መልካም ንባብ ተመኝን፡፡
በወንጀል ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው?

የሁከት ማድረግ ወንጀል በማይንቀሳቀስ ንብረት (ቤት ፣ ይዞታ፣ መሬት ሕንጻ) ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን የወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 685-687 አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጅ ዓለም አቀፉ የሕግ ሳይንስም ይሁን የእኛ ሀገር ሕግ ሁከት የግል ነጻነቶች መገለጫ በሆኑ የግል ቤቶችና ሌሎች የተከለሉ ወይም የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የሚፈጸም የመድፈር ተግባርም በነዚህ ይዞታዎች ላይ ሁከት በማድረስ ሊፈጸም እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥበቃ በተደረገላቸው ይዞታዎች ላይ የሚደረግ የሁከት ተግባር ተፈጸመ የሚባለው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑን ዓለም አቀፉ ተሞክሮ ያሳያል፡፡

ሁከት የፈጠረው ሰው ወደአንድ ይዞታ ወይም የተከለከለ ስፍራ ለመግባት ወይም ገብቶ ለመቆየት በሕግ ወይም በሌላ አግባብ ያልተፈቀደለት መሆን አለበት፡-
ይህም ማለት ሁከት የፈጠረው ሰው ወደሌላ ሰው ይዞታ ለመግባት ወይም ገብቶ ለመቆየት የማይፈቀድለት መሆኑን የሚያውቅ ወይም ከነገሮች ሁኔታ አንጻር ያልተፈቀደለት ስለመሆኑ በቂ የማወቅ እድል ያለው መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 686 (1) እንደሚደነግገው ማንም ሰው እያወቀ መብት ሳይኖረው ወይም ጥቅም ለማግኘት ሲል በሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ ላይ ሁከት ሊፈጥር እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ “በሕግ ሳይፈቀድለት (ከሕግ ውጭ)” የሚለው አነጋገር የሕብረተሰቡን ሰላምና ደሕንነት ለማረጋገጥ ሲባል በፍርድቤት የመበርበሪያ ትእዛዝ ወይም የሚመለከተውን አካል በማስፈቀድ የሚደረጉ ጣልቃ-ገብነቶችን ከሁከት ተግባር ለመለየት የተቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ወደ አንድ ይዞታ ለመግባት ወይም ይዞ ለመቆየት የሚያስችል ፈቃድ በሕግ በተፈቀደ መብት፣ ምክንያታዊ ሰው ሊረዳው በሚችለው ምልክት፣ በንግግር ወይም በጽሑፍ ሊገለጽ ይችላል፡፡

እዚህ ላይ አከራካሪው ጉዳይ አንድ ቦታ ወይም ይዞታ ያልተፈቀደና የተከለከለ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ይሕ ጥያቄ የሚነሳው በግልጽ በሕግ ክልከላና ጥበቃ የሚደረግባቸውን ወይም በግልጽ በሚታወቅ ሁኔታ የተከለከሉ ይዞታዎችን በሚመለከት ሳይሆን ብዙ ጊዜ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ለምሳሌ የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት)፣ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተፈቀዱ አካባቢዎችን ወዘተ የሚመለከት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምንም እንኳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 686 (1) በጥቅሉ “የሌላ ሰው ይዞታ የሆነውን መሬት ወይም ሕንጻ የወረረ ወይም የያዘ ወይም ፤ በማናቸውም ሌላ አኳኋን የሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ በሆነ መሬት ላይ ሁከት ያደረሰ እንደሆነ …” በማለት ቢያስቀምጠውም በሌላ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ (አንቀጽ 604) ላይ ግን እነዚህን ይዞታዎች ለመዘርዘር ይሞክራል፡፡

በመሆኑም የወንጀል ሕግ በጠባቡ የሚተረጎም በመሆኑ ከላይ “በማናቸውም ሌላ አኳኋን” ሚለው አገላለጥ ከወንጀል ሕጉ ከራሱ ድንጋጌዎችና ዓላማዎች አንጻር በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ያሕል የተለቀቁና የተተው ይዞታዎች ላይ ሁከት ተፈጠረብኝ የሚል የግል አቤቱታ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ የወንጀል ክስ አቅራቢ ይዞታው በእርግጥም የተለቀቀ፣ የተተወና ለማንኛውም ሰው ክፍት የተደረገ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ አካባቢው ላይ ያለውን ሁኔታ በአግባቡ በመመልከትና በመመርመር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

ወደ ይዞታው ለመግባት ወይም ለመቆየት የሚያስችል ቅድመ-ሁኔታ (ሕግ፣ የጥንቃቄ እርምጃ ወይም ስነ-ስርዓት) አለመሟላት፡-
በሌላ በኩል ምንም እንኳን ይዞታው ለመግባት የተፈቀደ ቢሆንም ወደይዞታው ለመግባት የሚፈልግ አካል ግን ለመግባት ወይም ለመያዝ ወይም በይዞታው ለመቆየት የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያሕል የተፈቀደለት ልዩ ባለሙያ መሆኑን ማሳየት፣ ነዋሪ መሆኑን ወይም የፍተሻ ቅድመ-ሁኔታን መፈጸም ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ በተጨማሪም በይዞታው ለመገልገል ወይም ለመጠቀም ከሚያስፈልግ ነገር ውጭ ሌሎች አላስፈላጊ እቃዎችን ወይም መሳሪያዎችን መያዝ አለመያዙ ሁከት የማድረግ ወይም አለማድረግ ሁኔታዎችን የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ ላብራቶሬ ለመግባት የሚያስፈልግ ቅድመ-ሁኔታ ወደአንድ ሆቴል ለመግባት ከሚያስፈልግ ቅድመ-ሁኔታ ሊለይ ይችላል፡፡

ተገቢው ጥንቃቄና ሕጋዊ ስነ-ስርዓት ሳይፈጸም የሚደረግ ሁከትን በተመለከተ ይሕንኑ ስነ-ስርዓትና የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ በሚገባው የመንግስት ሰራተኛ ወይም የሰራዊት አባል ሊፈጸም የሚችል ሲሆን ይዞታውን ለመቆጣጠር ከሚያስችል ኃይል በላይ ወይም በሕግ ከታዘዘው ወይም ከተፈቀደው ስርዓት ውጭ የሰውን ንብረት መያዝን ወይም መውሰድን የሚመለከት ሲሆን ይሕ በሆነ ጊዜ በሁከት ማድረግ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገልና የግል ይዞታዎችን በመድፈር ወንጀልም ሊያስጠይቅ ይችላል፡፡

ውድ አንባቢያን ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁን ጥንቅር በዚሁ አበቃን ጥሩ ትምህርት እንዳገኛችሁበት ተስፋ እናደርጋለን፤ በቀጣይ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ሰላም፡፡
Source:- FDRE Attorney General

05/04/2021

አላባ (Usufract) /የንብረት ህግ ላይ/
========================
የአላባ መብት ከአንድ ግዙፍነት ያለው የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ግዙፍነት ከሌለው የባለቤትነት መብት ተቀንሶ በንብረቱ ለመገልገል (usus) ወይም ፍሬውን የመሰብሰብና መውሰድ (fructus) መብት በመስጠት የሚቋቋም የንብረት ግንኙነት ነው፡፡ ይሄውም አንድ ሰው ካለው የባለቤትነት መብት ቀንሶ ለሌላ ሰው የሚያስተላልፈው መብት ነው፡፡ አንድን ንብረት በአላባ የማስተላለፍ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ ". . . ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል" በሚለው ስር የሚወድቅ ህገ-መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው መብት ነው፡፡ አላባ ከፍ/ብ/ህጉ አንፃር ሲታይም ከቁጥር 1309-1358 ባሉ ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የምናገኘው በንብረት የመገልገል ወይም ፍሬው የመሰብሰብና የመውሰድ ወይም ሁለቱ መብቶች አንድ ላይ ተዳብለው ልናገኛቸው የምንችል የንብረት ማስተላለፍያ አገባብ ነው፡፡
የአላባ መብት መሰረቱ (subject matter) ግዙፍነት ያላቸው (corporeal things) የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው (incorporeal things) እንደ ቅጅ መብትና ፈጠራ ያሉ የንብረት መብቶች ናቸው፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1204/1/፣ 1126፣ 1309/1/ /2/ እና 1347 እና ቀጠቀዮቹ) የአላባ መብት ምንጭ (source) ውል፣ ኑዛዜ ወይም ሕግ ሊሆን ይችላል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1184 እና 1185) የአላባ መብት መሰረት የሚንቀሳቀስ ንብረት በሆነ ግዜ ተጠቃሚው ንብረቱን በእጅ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1186/1/) የአላባ መብት መሰረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ ግን የአላባ መብት ምንጭ የሆነው ውል ወይም ኑዛዜ መመዝገብ ስለሚኖርበት በይዞታው ስር በማድረግ ብቻ የአላባ ተጠቃሚነትን መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1184 እና 1185) በኢትዮጵያ ፍ/ብሄር የፍትህ ስርዓት የአላባ መብት ከህግ የሚመነጨው ከማይንቀሳቀስ የውርስ ሃብት ጋር በተያያዘ መንገድና፣ ለአካለ መጠን ባላደረሰ ልጅና ሞግዚቱ ወይም በባልና ሚስት መካከል ያለን ግንኙነት መሰረት በማድረግ ሲሆን የሚተላለፍበት ስርዓትም በማግኘት (acquisition, Possession etc.) በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1310 እና 1311 ላይ በተደነገገው መሰረት ነው፡፡
የንብረት ባለቤትነት መብት (ownership right) ሶስት መሰረታዊ መብቶችን ማለትም የሌሎችን መብት ሳያውኩ (ሳይነኩ) (without impairing any one’s right) እንደፈለጉ ማድረግ (abusus right) በንብረት የመገልገልን (usus) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመውሰድ (fructus) መብቶችን የሚያጐናፅፍ ሲሆን የአላባ መብት የንብረቱ ባለቤት (owner) የባለቤትነት መብቱን (ownership right or abusus right) ለራሱ በማስቀረት የተቀሩትን ሌሎች ሁለት መብቶች ማለትም በንብረቱ የመገልገልና (right of using) እና ፍሬውን ሰብስቦ የመውሰድ (enjoying the thing) ለአላባ ተጠቃሚው በማስተላለፍ የሚገኝ መብት ነው፡፡ የአላባ መብት ተጠቃሚው በሂወት አስካለ ድረስ ሊገለገልበት የሚችል መብት እንጂ እንደሌሎቹ የንብረት መብቶች ወደ ተወላጆቹ ወይ ወላጆቹ በውርስ ሊተላለፍ የሚችል መብት አይደለም፡፡ይህ ማለትም አንድ ሰው በንብረት ያላውን የባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የአላባ መብት ለሌላ ሰው በኑዛዜ መስጠት የሚችል ቢሆንም ይህ የአላባ ተቀባይ በሚሞትበት ጊዜ ይህን የአላባ መብቱ ለወራሾቹ በኑዘዜ ማሰተላለፍ አይችልም ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322(1)) አንዱ የአላባ መብት ማስገኛ መንገድ ውል እንደምሆኑ መጠን የአላባ መብት በአላባ ሰጪና ተቀባይ መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚቋቋም የንብረት መብት በሚሆንበት ጊዜ በተዋዋዮቹ መካከል በርካታ መብቶችና ግዴታዎች (bundle of rights and duties) ያሉበት ነው፡፡
1.1. የአላባ ተጠቃሚ መብትና ግዴታ
 በአላባ የተሰጠውን መብት ለመገልገል ንብረቱን በራሱ ወይም በወኪሉ አማካይነት በይዞታው ስር ማድረግና በዚህ መብቱ ለመስራት በባለቤቱ፣ በወራሾቹ ወይም ንብረቱን በእጃቸው ላይ ባደረጉ 3ኛ ወገኖች ላይ የባለይዞታነት ክስ (possessory action) የመመስረት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1311 እና 1341)
 የማይንቀሳቀስው ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በመንግስት በሚወሰድበት ግዜ የአላባ ተጠቃሚው በመልቀቅ ምክንያት የተሰጠውን ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319(2))
 የአላባ ተቀባዩ ያለውን መብት መሰረት በማድረግ የመድን ሽፋን የመግዛትና ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320 እና ን/ህ/ቁ 654)
 ፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 የአላባ ተጠቃሚው የአላባ ንብረቱን በቁጥጥር ስር ማደረግ አለበት ሲል እንደሚደነግግ ሁሉ የአላባ ተጠቃሚው ይህን የአላባ መብት የሚያገኘው ከህግ ከሆነ መብቱን የሚያገኘው ወድያውኑ (automatic) ነው፡፡ መብቱ የመነጨው ከውል በሆነ ጊዜ ስመምነቱ እንደተፈፀመ፣ በውርስ ከሆነም ውርሱ ሲከፈት፤ በኑዛዜ ከሆነ ደግሞ የውርስ ንብረት የማጣራቱ ስራ እንዳለቀ የአላባ መብቱን ያገኛል፡፡
 የአላባ መብቱ መሰረት የሆነው ነገር የፍጆታ እቃ (consumable good) ከሆነና ሳይጐዳ በመብቱን ሊሰራበት የማይችል በሆነ ግዜ የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡ ይህ ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት እንደፈለገ ያረገዋል(will have the right to dispose) ማለት ነው:: ለምሳሌ፡- የአላባ መብቱ የተሰጠው በወይን ላይ ከሆነ ወይኑን የመጠጣት፣ የድንጋይ ከሰል ከሆነ በድንጋይ ከሰሉ የመገልገልና የመጨረስ፣ ገንዘብ ከሆነም ገንዘቡን ወደ ሌላ የማስተላለፍ መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1327(1))
 የአላባ መብቱ የተሰጠው ፍሬ ለመሰብሰብ ከሆነ የአላባ ተቀባዩ የተፈጥሮ ፍሬዎች (natural fruits) እንደ ጥጃዎች (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1171 እና 1328(1)) ፣ ሲቪል ፍሬዎች (civil fruits) እንደ ኪራይ፤ ወለድ ወይም የተጣራ ትርፍ (interests, arrears or dividends) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331 እና 1347) እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች (periodical products) (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1170/2/ እና 1333) የመሰብሰብ መብት ይኖረዋል፡፡
 የአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ሃብቶች ወይም የአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ነገሮች (pre-mature things) ሲበስሉ ወይም ውሉ ሲቋረጥ የበሰሉ ካሉ የአላባ ተጠቃሚው እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1328(1))
 የአላባ ንብረቱ ለምሳሌ እንደ ቤተ መፅሐፍ ፣ ፈረስና የቤት እቃ ያለ ሲሆን የአላባ ተጠቃሚው ይህንን ንብረት ለሌላ 3ኛ ወገን በኪራይ (lease) የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331)
 በአላባ የተሰጠን ንብረት መሬት ወይም ቤት ሲሆን ከተኸራየ በኋላ የገዛ ወይም በዋስትና የያዘ ሰው ቢኖሩም ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የአላባ ተጠቃሚው በአላባ መብቱ ይሰራበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1332(2))
 የንብረቱ ባለቤት በአላባ የሰጠውን የማይንቀሳቀስ ንብረት በዋስትና (mortgage) ለሌላ ሶስተኛ ወገን መስጠት የሚችል ቢሆንም የአላባ ተቀባይ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1340፣ 3047 እና 3072)
 አላባ ተቀባዩ የዋስትና (mortgage) ዋናው እዳ (principal debt) የመክፈል ግዴታ የለበትም፡፡ የከፈለ እንደሆነ ግን አላባ ሰጪውን ገንዘቡ እንዲመልስለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1340 (2))
 የማይንቀሳቀስ ንብረት ማስለቀቅንና የመድህን ካሳ ክፍያን መሰረት በማድረግ በሚነሱ ክርክሮች መብት አለኝ ብሎ በክርክሩ ውስጥ ልግባ የማለት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 ፤1341፣ ን/ህ/ቁ. 654 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 33(2))
 በአላባ በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ነገር የሰራው ካለ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ነቅሎ የመውሰድ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346(2))
 በአላባ የተሰጠው ንብረት ከእጁ ወይም ከይዞታው ከወጣ እንዲመለስለት ወይም ሁከቱ እንዲወገድለት የባለ ይዞታ ክስ (possessry action) የመመስረት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1149፡ 1311፡1341 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33(2))
 በአላባ የተሰጠው ንብረት ቢወድምም የአላባ ተጠቃሚው በትራፊው ወይም በቀሪው ዎና (ruins) መገልገል ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1344)
 በአላባ የተሰጠውን ንብረት የመስጠትና የኪራዩን ገቢ የመስብሰብ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331) ስለዚህም የአላባ ግንኙነት እጅግ በርካታ መብቶችን ሊያስገኝ የሚችል የንብረት ግንኙነት እንደሆነ ከንብረት ህጉ ይዘት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ነው፡፡
 በአላባ የተሰጠውን ንብረት ደረጃውን ጠብቆ በቅን ልቦና የማስተዳደርና የተቋቋመበትን አላማ መሰረት በማድረግ በአላባ መብቱ የመገልገል ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1312 ፣ 1326 ፤ 1328 እና 1330)
 እንደ የጣራ ማፍሰስ፣ መለስተኛ የግንብ መሰንጠቅ፣ የቀለም ቅብ ያሉ ተራ የጥገና ስራዎች የመስራት ግዴታ አለው፡፡ የአላባ መብቱ የተገኘው በውርስ (inheritance) ሲሆን የአላባውን ንብረት ዕዳ ወይም ወለድ የመክፈል ግዴታና መደበኛ ወጪ እንደ ግብር ያሉ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የግብር መክፈል ግዴታ በመፈፀም ላይ ያለ የአላባ ተጠቃሚ ለተከታታይ 15 ዓመታት ቢከፈልም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1168 በመያዝና መገልፈገል ብቻ (usucaption) የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ አያደርገውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1313 እና 1314)
 የአላባ ውሉ ሲቋረጥ የአላባው ንብረት በሂደት የሚመጣውን መጥፋትና መበላሸት (loss and deterioration) ሳይጨምር እንደነበረው ለባለቤቱ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1317 ፣ 1326፤ 1327(2) ፣1343 ፤ 1346 እና 2027)
 የአላባ ተጠቃሚ በአላባ የተሰጠውን ንብረት በሚንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (pledge)፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (mortgage)፣ በንብረት አገልግሎት (servitude) ወይም ለሌላ ሰው በአላባ የመሰጠት ወይም የማስተላለፍ መብት ቢኖረውም ይህን መብቱን በስራ ላይ በሚያውልበት ግዜ የባለቤቱን መብት መጉዳት (impair) የለበትም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 እና 1324)
 የአላባ መብት ቀሪ በሚሆንበት ግዜ የንብረቱን ዋጋ ሳይሆን ንበረቱን በዓይነት ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
 በአላባ የተሰጠው ንብረት በሶስተኛ ወገኖች እጅ ሲገባ (usurpation) ወይም የጣለቃ መግባት (interference) ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለባለቤቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1342)
 በአላባ የተሰጡት እንስሳት በሚሆንበት ግዜና ከእነዚህ የተወሰኑት በአደጋ ወይም በበሽታ ያለቁ እንደሆነ የነዚህን ምትክ ከሚወለዱት የመተካት ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህ እንሰሳት በጠቅላላ በአደጋው ወይም በበሽታው ካለቁ ግን ቆዳቸውን የማስረከብ ወይም የቆዳውን ዋጋ ለባለቤቱ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1345)
 መሰረታዊ ለውጥ ያለማድረግ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1330)
 ንብረቱን የማቀብ (preserve) ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1309)
 ለንብረቱ ለማስተዳደር፡ ፍሬውን ለማግኘትና ለመጠቀም የሚያስፈልገውን ወጪና ወለድ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1313) ስለዚህ አንድ የአላባ ተጠቃሚ በርካታ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም ያሉበት ነው፡፡

1.2. የአላባ ሰጪ መብትና ግዴታ
 የአላባ ውል ግዜው ሲያልቅ ንብረቱን የመረከብ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322 እና 1327)
 በአላባ መብትነት በሰጠው ንብረትና በመብቱ ላይ ተፅእኖ (jeopardy) አለ ባለ ግዜ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ መብቱ እንደነበረው እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
 ልዩ ወጪዎች እንዲከፍል በሚጠየቅበት ግዜና ይህን ወጪ የአላባ ተጠቃሚው በብድር መልክ የማይሰጠው ከሆነ በአላባ ሰጥቶት ከነበረው ንብረቱ ገሚሱን በመሸጥ እዳውን የመክፈል መብት፡፡
 በአላባ የሰጠውን ንብረት በዋስትና (mortgage) የመስጠት መብት፡፡
 በአላባ ተጠቃሚው ዋስትና (Securities) እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
 የአላባ ተቀባዩን መብት ሳይጋፋ በንብረቱ የማዘዝ መብት አለው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323)
 የባለቤትነት መብቱን መሰረት በማድረግ የመድን ዋስትና የመግዛትና የመድን ሽፋን የተሰጠው አደጋ እውን ሲሆን (whenever the risk materialises) ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320)
 በአላባ ከተሰጠው ንብረት ጋር ያለአግባብ የተላለፈ ንብረት ካለ የማስመለስ መብት፡፡
 ለአላባ ተቀባይ እንዲሆን ከተወሰነው በላይ ፍሬ ወይም ትርፍ ከተገኘ የመውሰድ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1328(2) እና 1348)
 በአላባ በተሰጠው መሬት ውስጥ የተቀበረ ገንዘብ (treasure) ከተገኘ ባለቤት በመሆኑ የመውሰድ መብት፡፡( ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1329)
 የአላባ ተጠቃሚው በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ስራ ሰርቶ ከሆነ የአላባ መብቱ ከተቋረጠ ግዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ንብረቱን ለማንሳት ካልጠየቀ አላባ ሰጪው የዚህ ተጫማሪ ስራ ባለቤት ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346/2/ ) ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡
በአላባ የሰጠውን ንብረት ለአላባ ተጠቃሚው የማስረከብ ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
የአላባ ውሉ በፅሑፍ እንዲሆንና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለው፡፡
በአላባ የተሰጠው ንብረት ጥገና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ሲሆን ወጪውን የመሸፈን ግዴታ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1338)
የጦርነት መዋጮ፣ የሰራዊት ሰፈር፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ወጪ ወይም ረግረጐች የማድረቅ የመሳሰሉ ልዩ ወጪዎች (extra ordinary charges) የመክፈል ግዴታ የአለባ ሰጪው ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1315)
በመደበኛ አገልግሎት ምክንያት ዋጋው ቢቀንስ (depreciation caused by ordinary wear and tear) የንብረትን ማሽቆልቆል መሰረት በማድረግ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረግ ወጪ ቢኖር የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1326 )
1.3. የአላባ ግንኙነት ቀሪ ስለመሆን
 የአላባ ተጠቃሚው በውሉ ያሉትን ግዴታዎች የጣሰ አንደሆነ የአላባ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 (3) እና 1324)
 የአላባ ተጠቃሚው ሲሞት የአላባ መብት በውርስ የሚተላለፍ መብት ባለመሆኑ ምክንያት ቀሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአላባ ተጠቃሚነት መብቱ የተሰጠው ለባልና ሚስት በጋራ በሆነ ጊዜ የአንደኛው መሞት የአላባ ተጠቃሚነቱን መብት ሙሉ ለሙሉ ቀሪ አያደርገውም፡፡ በሌላ አነጋገር በሂወት ካለው ስው ጋር የአላባ ግንኙነቱ ይቀጥላል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
 የአላባ ውሉ ግዜ ሲያልቅ በአላባ ተጠቃሚ የመሆን መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
 የአላባ መብት ተጠቃሚነት መብት የተሰጠበት ነገር እንደ ጥሬ ገንዘብ ባሉ አላቂ ነገሮች (consumable goods) ሲሆንና ሲያልቁ የአላባ መብት የተቋቋመበት ውል ቀሪ ይሆናል፡፡
 የአላባ ተጠቃሚው በራሱ ፍላጐት በግልፅ የአላባ ተጠቃሚነት መብቱን ሲተው (express waiver) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323(2))
 በአላባ የተሰጠው ንብረት ሙሉ ለሙሉ ሲወድም የአላባ ጥቅም መሰረት (subject matter of the usufract) በሌለበት ሁኔታ መብቱ ሊኖር ስለማይችል የአላባ ግንኙነቱን እንዲቀር ያስገድዳል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319፣ 1343) ስለዚህ የአላባ ግንኙነት እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ወይም ከህግ የሚመነጭ መብት በአንድ ወቅት ሊቋረጥ የሚችል ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በመቋረጡ የሚኖረው ውጤትም፡-
 ከአላባ ተጠቃሚው ጋር የተደረጉ ውሎች ውጤት አልባ (extinguished contracts) ይሆናሉ፡፡
 በአላባ የተሰጠው ንብረት የማይንቀሳቀስ ንብረት በሆነበት ግዜና ተከራይቶ ወይም በዋስትና ተሰጥቶ ከቆየ የውሉ ግዜ በማለቁ ብቻ የአላባ መብቱ ቀሪ ሊሆን ስላማይቻል 3ኛ ወገኞች ለሶስት ዓመት የግድ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአላባ መብት ግዙፍነት ባላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም ግዙፍነት በሌላቸው የንብረት መብቶች ላይ ሊመሰረት የሚችል ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው የዜጐች በንብረት የመገልገል፤ፍሬ የመሰብሰብንና መውሰድን መብት የሚያጎናፅፍ ከውል ፤ ከህግ ወይም ከኑዛዜ የሚመነጭ ግንኙነት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከውል፤ ከህግና ከኑዛዜ የሚመነጩ በርካታ የአላባ ተጠቃሚና አላባ ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ንበረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ወይም ከህግ የሚመነጩ መብቶች (legal rights) ተመስርቶ ቆይታው ይርዘም ይጠር ሰዎች በመብቱና ግዴታው ሲሰሩበት ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ቀሪ የሚሆን ንብረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነትም ነው፡፡

04/04/2021

የወንጀል ተካፋይ የሆነን ሰው ምስክር አድርጎ ከክስ ነፃ ስለማድረግ
*******************************
"1. ከክስ ነፃ የማድረግ ምንነትና አይነት
ከክስ ነፃ ማድረግ ማለት ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው በህግ ከሚጣል ግዴታ፣ ከመከሰስ ወይም ከቅጣት ነፃ ለማድረግ የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ ከክስ ነፃ ማድረግ የተለያየ አይነት ያለው ሲሆን ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመንግስት ሀላፊዎችን ከክስ ነፃ ማድረግ፣ የሉዓላዊነት ነፃነት እና የዲፕሎማሲ ነፃነት ሊሆን ይችላል፡፡

2. ምስክርን ከክስ ነፃ ማድረግና ዓላማው
በወንጀም ፍትህ አስተዳደር በውንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ በማድረግ እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ ሀገራት ተግባራዊ የሚደረግ አሰራር ነው፡፡ ይህ አሰራር ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው በጉዳዩ ዙሪያ ጠቃሚ ማስረጃ የሚሰጥና ለምርመራና ክስ ስራ ውጤታማነት ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ከክሱ ነፃተደርጎ የምስክርነት ቃል እንዲሰጥ የሚደረግበት ነው፡፡ አንድ ሰው ከክስ ነፃ የሚደረገው ከእሱ ለሚገኘው ማስረጃ/ምስክርነት ለውጥ ተደርጎ ነው ማለት ነው፡፡

በወንጀል ተካፋይ የሆነውን ምስክር ከክስ ነፃ ማድረግ ሁለት አይነት አለው፡ ግለሰቡ ምስክር ከሚሆንበት ወንጀል ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ አንዱ ሲሆን ግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ቃል በእሱ ላይ እንደማስረጃ እንዳይቀርብ ብቻ ማድረግ ሁለተኛው ነው፡፡

ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው በወንጀል ድርጊቱ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ የሆነውን ሰው ነፃ በማድረግና ምስክርነቱን በመጠቀም ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራን ውጤታማና ቀላል ማድረግን ዓላማ በማድረግ ነው፡፡ አሰራሩ ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ የህዝብን ጥቅም የማስከበር እና የምስክሩን ጥቅም ለማጣጣም የተዘረጋ ነው፡፡

ይህ አሰራር ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውጤታማነት የሚያበረክተው ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል፣ ምስክሩ በተጽዕኖ የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጥ በጥንቃቄ እና በልዩ ሁኔታ አስፈላጊው መስፈርት ሲሟላ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ይመከራል፡፡ ለአብነት ነፃ የተደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ በሌሎች ማስረጃዎች እንዲደገፍ እና የሚሰጠው ምስክርነት ትክክለኛነቱ የመስቀለኛ ጥያቄ በመሳሰሉ ስልቶች እንዲረጋገጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

3. ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ቅድመ ሁኔታ
በውንጀል የተሳተፈን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግ እና እንደ ምስክር መጠቀም በተለያዩ ሀገራት የተለያየ አሰራር ያለው ሲሆን በሀገራት የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችም ይለያያሉ፡፡ በዚህ መሰረት በአንዳንድ ሀገራት ከክስ ነፃ የሚደረገው ሰው ምስክር የሚሆንበት ጉዳይ እና እሱ ነፃ የሚሆንበት የወንጀል ጉዳይ ግንኙነት ያላቸው መሆን ይገቧል፡፡ በተጨማሪም ከክስ ነፃ ለማድረግ የጉዳዮቹ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ማስረጃ/ምስክርነት ክብደትም ከግምት ይገባል፡፡ ይህ ማለት ነፃ የሚደረገው ሰው የሚሰጠው ምስክርነት ለጉዳዩ ውጤታማነት ወሳኝና ጠቃሚ ማስረጃ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል የተወሰኑት ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከወንጀል ክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ የተደረገውን ሰው ከፍትሐብሔር ተጠያቂነት አያድነውም ወይም በፍትሐብሔር ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡
በአጠቃላይ የብዙ ሀገራት የህግ ማዕቀፍ እንደሚያሳየው ምስክርን ከክስ ነፃ የማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው ግለሰቡ ምስክር የሚሆንበት ወንጀል ከባድነት፣ የምስክርነቱ ጠቃሚነትና ቅቡልነት እንዲሁም ግለሰቡ በወንጀሉ ያለው ተሳትፎና ምስክር የሚሆንባቸው ሰዎች ያላቸው ተሳትፎ እንደ መመዘኛ ተወስዶ ነው፡፡

4. ከክስ ነፃ ማድረግ በኢትዮጵያ
በሀገራችን በተለይ በሙስና ወንጀል ጉዳዮች የወንጀል ተሳትፎው አነስተኛ የሆነን ሰው ከክስ ነፃ ማድረግና በሌሎች ላይ ማስረጃ እንዲሆን ማድረግ የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገራችን የህግ ማዕቀፍ ሲታይ በተለያዩ የህግ ሰነዶች እውቅና የተሰጠው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አሰራር እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡

በ2003 ዓ.ም የወጣው የሀገራችን የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ለወንጀል ተግባር በተቋቋሙ ቡድኖች፣ በረቀቁ ዘዴዎች ወይም በትጥቅ በታገዘ ወይም በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት አመፅ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፈ ሰው ሌሎች ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት እና ለምርመራና ክስ ስራው ውጤታማነት ጠቀሜታ ያለው ማስረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆነ በዐቃቤ ህግ ውሳኔ ተጠያቂነቱ ዝቅ የሚልበት ወይም በሙሉ የሚቀርበት አሰራር በህግ እንደሚወሰን ያስቀምጣል፡፡ ይህ አሰራር ተግባራዊ የሚደረገው እንደ ሙስና፣ ሸብርተኝነት ወይም ወንጀሉ ውስብስ ሆኖ የተጠርጣሪውን ትብብር ማግኘት አስፈላጊ በሚሆንበት ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ፖሊሲው ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 በወንጀል ተካፋይ የሆነ ሰው ስለተፈፀመው ድርጊት ጠቃሚ ማስረጃ ከሰጠ ከክስ ነፃ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4 (1) ላይ አንድ ሰው መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ ነፃነት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ማንሳት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት የሀገራችን ህግ ማዕቀፎች መረዳት የሚቻለው አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረገው ከባድና ውስብስብ በሆኑና የተከሳሹን ትብብር በሚፈልጉ ወንጀሎች፣ በግለሰቡ የሚሰጠው ማስረጃ ለምርመራውና ክስ ስራው ውጤታማነት ጠቃሚ ከሆነ እና ግለሰቡ ማስረጃ/ምስክርነት ከሰጠ እንደሆነ ነው፡፡"
ምንጭ:- ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ገጽ

አራጣ /Usury/ እና መዘዙ
=========================
አራጣ የሰዉ ልጅን የግብይት ታርክ በቅርበት ተከትሎ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በዘርፉ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፍ ያበረከቱ ምሁራንም ቢሆኑ አራጣ ከአራት ሺህ አመት ያላነሰ ታርክ እንዳለዉ በመግለጽ የቅርብ ግዜ ክስተት እንዳልሆነ ደጋፊ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ ስለ ታርካዊ አመጣጡ ይህንን ካልኩኝ ወደ ዋናዉ የጽሁፉ አላማ ማለትም የአራጣን ምንነት፣ የሚያስከትለዉን የወንጀል ሃላፊነት/ተጠያቂነት፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ አንዲሁም በሀገር እኮኖሚ ላይ የሚያስከትለዉን ጉዳት ለአንባቢያን ግንዛቤ ማስጨበጥ በመሆኑ ያንኑን እንደሚከተለዉ በዝርዝር እናያለን፡፡
አራጣ በተለያዩ ሀገራት ሕግጋት እና በተለያዩ የሙያ መስክ ባሉ ምሁራን በተጻፉ መጻህፍት ላይ የተለያዩ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በሀገራችን ሕግ አራጣ ያለዉን ቦታ ከስር በጥልቀት የሚናየዉ ቢሆንም በመደበኛዉ አረዳድ ግን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሳተመዉ የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት በገጽ 312 ላይ አራጣ ማለት ‘’ከፍተኛ የገንዘብ ብድር ወለድ’’ ነዉ በማለት ጠቅለል ያለ ትርጉም መስጠቱን እንመለከታለን፡፡
የሆነዉ ሆኖ ለዚህ ጽሁፍ አላማ ብቻ ሲባል አብዛኛዎቹ የአራጣ ትርጉሞች በዉስጣቸዉ ከያዙዋቸዉ ፍሬ ነገሮች በመነሳት ተግባሩን ‘’በህግ ወይም ተቀባይነት ባለዉ ልማድ ከተፈቀደዉ በላይ በሆነ የወለድ ምጣኔ ገንዘብ ማበደር ነዉ’’ ብለን በአጭሩ መተርጎም እንችላለን፡፡
እዉን የአራጣ ተግባር የተወገዘ ነዉን ?
ለአንድ ተግባር ተቀባይነት ወይም ዉጉዝ መሆን በርካታ ግላዊ /Subjective Standard/ እና ዉጪያዊ /Objective Standard/ መመዘኛዎች ያሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ከሞራላዊ፣ አመክንዮአዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ሕጋዊ መመዘኛዎች የሚያልፉ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአራጣ ተግባር በበርካታ አከባቢዎች በተለይም በገጠራማዉ አከባቢ የተስፋፋ ቢሆንም ከላይ በተዘረዘሩት መስፈርቶች በአብዛኛዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
በአለማችን ላይ በርካታ ተከታይ እና ታርክ ካሉዋቸዉ ሀይማኖቶች ዉስጥ በአይሁዳዉያን እምነት አራጣ ማበደር ከአይሁዳዊያን ወገኖቻቸዉ ዉጪ ላሉት ባዕዳን ከሚፈቅደዉ ዉጪ ሌሎቹ ታላላቅ ሀይማኖቶች ማለትም በክርስትና፣ በእስልምና፣ በቡዲዚም እና በሕንዱይዝም የሐይማኖት ተቋማት አስተምሮ አራጣ ማበደር የተከለከለ ነዉ፡፡ በክርስትናዉ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሐይማኖት ምንጭ በሆነዉ በቅዱሱ መጽሀፍ ከስልሳ ጊዜ በላይ የአራጣ ተግባር ተኮንኗል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በእስልምናዉ ሀይማኖት ጭራሹኑን የወለድ ምጣኔዉ ከግምት ሳይገባ ከተቀማጭ ገንዘብ ትርፍ/ወለድ መቀበል የተከለከለ እንደሆነ እናዉቃለን፡፡
ከሞራል አንጻርም ጉዳዩን ብንመዝነዉ አብዛኛዉን ግዜ የአራጣ ብድር ሰለባ የሆኑት በአስቸኳይ ሁኔታ የሚደርስላቸዉን ገንዘብ የሚፈልጉ እና በከፍተኛ ሁኔታ የገንዘብ ችግር ላይ ያሉ ሰዎች በመሆናቸዉ ማናቸዉን ዋጋ ከፍለዉ ገንዘብ ከማግኘት ወደኋላ የማይመለሱ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ በመሆኑም ገንዘብ አቅራቢ/አራጣ አበዳሪዎች የሚወስኑትን የወለድ ምጣኔ ላይ ድርድር በማድረግ ለማስቀነስ ሁኔታዉ የማይፈቅድላቸዉ በመሆኑ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለተወሰነ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብሎ የሌላዉን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ህይወት፣ የቤተሰብ ህልዉና አደጋ ላይ መጣል በየትኛዉም የሞራል መመዘኛ ቢታይ ተቀባይነት ያለዉ ተግባር አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ እርዳታ የሚፈልገዉን ሰዉ ለመጠቀሚያነት ማመቻቸት በተገለጸዉ ሁኔታ የሞራል ልዕልናን የሚጋፋ ተግባር መሆኑ እሙን ነዉ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አራጣን ከአመክንዮአዊ /Logical/ አሰራር ሆነ አስተሳሰብ አንጻር ብናየዉ ድጋፍ ያለዉ ተግባር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የወለድ ፅንሰ ሀሳብ አበዳሪው ገንዘቡን ቢጠቀምበት ሊያገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ከዚያ ዉጪ ሰርቶ ሊያገኝ ከሚችለዉ በላይ መጠየቅ አመክንዮአዊ ትርፍ አይሆንም፡፡ ከአራጣ የሚገኝ ትርፍ ያልተደከመበት፣ ፍትሀዊ ያልሆነ እንዲሁም በሌላ ግለሰብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ አራጣ አበዳሪዉን የሚያኮራ እና የድካሙን ዋጋ እንዳገኘ የሚያስቆጥር ትርፍ አይደለም፡፡
በመጨረሻም አራጣ ብድር ከወንጀል ሕጋችን አንጻር ሲታይ እንደአብዛኛዎቹ ሀገራት የአራጣ አበዳሪነት ተግባር የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 712 ላይ “ማንም ሰዉ የተበዳዩን ችግረኛነት፣ የበታችነቱን፣ ወይም የገንዘብ ችግሩን ወይም መንፈሰ ደካማነቱን ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለዉ መሆኑን መሰረት በማድረግ በሕግ ከተፈቀደዉ ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረዉ እንደሆነ ወይም ካበደረዉ ገንዘብ ጋር በግልጽ ተመጣጣኝነት የሌለዉን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠዉ ያደረገ ወይም ቃል ያስገባዉ እንደሆነ ……. በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡
ከወንጀል ሕጉ ድንጋጌ አንጻር አበዳሪዉን በወንጀል ለማስቀጣት መሟላት ያለባቸዉ ሁለት አበይት ፍሬ ነገሮችን /Elements of the Provision/ አሉ፡፡ የመጀመርያዉ የተበዳሪዉ የገንዘብ ችግር፣ የግንዛቤ ደረጃ እና መሰል የመደራደር አቅሙን የሚያሳጡ ዉስጣዊና/ዉጪያዊ ምክንያቶች ሲሆኑ ሌላኛዉ ደግሞ በሕግ ከተፈቀደዉ የወለድ ምጣኔ በላይ ተቀብሎ ማበደር ናቸዉ፡፡ በሕግ የተፈቀደዉ የወለድ ምጣኔ ማለት በወንጀል ሕጉ ላይ ባይቀመጥም በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2479 ላይ እንደዉሉ ሁኔታ በአመት ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት በመቶ የሚደርስ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ከላይ የተገለጸዉ የድንጋገዉ የመጀመሪያዉ ፍሬ ጉዳይ ማለትም በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 712 (1) የተገለጸዉ የተበዳሪዉ የግል እና ዉስጣዊ ምክንያት ሀሳቡ ግልጽ ቢሆንም በአብዛኛዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች ላይ የምንመለከተዉ ግን ሕጉ በተገቢዉ ሁኔታ እየተተረጎመ ነዉ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡
ምክንያቱም የሕጉ አቀራረጽ በግልጽ የሚያሳየዉ በሕግ ከተቀመጠዉ የወለድ ምጣኔ በላይ በመቀበል ገንዘብ ማበደር ብቻዉን የአራጣ ተግባር እንደተፈጸመ የማያስቆጥር እና በተጨማሪነት አበዳሪዉ የተበዳሪዉን የገንዘብ ችግር፣ የመንፈስ ደካማነት፣ የልምድ እና አነስተኛ ግንዛቤዉን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ተግባሩን የፈጸመ መሆኑ መረጋገጥ ያለበት መሆኑን ነዉ፡፡
ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት በፍርድ ቤቶቻችን በተጨማጭ እየታየ ያለዉ የአበዳሪዉ ከላይ የተገለጹት ዉስጣዊ ምክንያቶች ከግምት ሳይገቡ የወለድ ምጣኔዉ በሕግ ከተቀመጠዉ በላይ ብቻ መሆኑን ካረጋገጡ አበዳሪዉን በአራጣ አበዳሪነት ከመቅጣት ወደ ኋላ የማይሉ መሆኑን ጸሃፊዉ ለዚህ ጽሁፍ ሲል ባደረገዉ መጠነኛ ጥናት አረጋግጧል፡፡ ይህ ሁኔታ በአፋጣኝ ማስተካከያ ካልተደረገበት የሕግ ክልከላዉን አላማ ከግብ እንዳይደርስ ከማሰናከሉም ባሻገር በተደጋጋሚ ጊዜ በፍርድ ቤቶቻችን የሚሰጡ የሕግ ትርጉሞች ተቀባይነት እና ተአማኒነት እንዳይኖራቸዉ አሉታዊ ሚና የሚኖረዉ መሆኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡
ከላይ የተገለጸዉ በፍርድ ቤቶቻችን የሚታየዉ የሕግ አተረጓጎም እንዳለ ሆኖ የአራጣ ማበደሪያ መንገዶች ሕጋዊዉን ተግባራት በማስመሰል የሚፈጸሙ እና ተበዳሪዎቹም አብዛኛዉን ግዜ ጉዳዩን በተለያዩ ምክንያት የማያጋልጡ በመሆኑ ከሚፈጸመዉ ወንጀል አንጻር ጥፋተኞቹን ለሕግ በማቅረብ እና በወንጀል በማስቀጣት የተገኘ ዉጤት እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ አራጣ አበዳሪዎች ተግባሩን ለመፈጸም ከሚጠቀሙት መንገዶች ዉስጥ ተግባሩ በብድር መልክ ሆኖ አራጣ አበዳሪዉ ለተበዳሪዉ ከሰጠዉ የገንዘብ መጠን በላይ እንዳበደረ አድርጎ ማስፈረም፣ አበዳሪዉ በብድር ከሰጠዉ የገንዘብ መጠን በላይ የሆነ የገንዘብ መጠን በቼክ ላይ አስጽፎ መቀበል እና ከብድር ገንዘብ በላይ ዋጋ ያለዉን ንብረት በመረከብ ገንዘቡ በወቅቱ ባይመለስና ቢዘገይ በአዳሪዉ የንብረቱን ስሜ ሀብት በራሱ ስም ማዛወር እንዲችል በማድረግ መዋዋል እና የመሳሰሉት የሚዘወተሩ ዘዴዎቻቸዉ ናቸዉ፡፡ አበዳሪዎች እነዚህን የማበደር ዘዴዎችን በልምድ እና በንባብ ባዳበሩት እዉቀት በመጠቀም የሚከዉኑት በመሆኑ ከህግ ተጠያቅነት የማምለጥ ዕድላቸዉ በጣም ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአራጣ ተግባር ዉስጥ ለዉስጥ እየተስፋፋ ከፍተኛ ጉዳት እደረሰ መሆኑን ጸሃፊዉ ያምናል፡፡ ጉዳቱን ከአባዳሪዉ አንጻር ስናየዉ ተግባሩ ወንጀል በመሆኑ ጥፋተኝነቱ ሲረጋጥ አበዳሪዉ ከመደበኛዉ ስራዉ እና ህይወቱ ተገልሎ በርካታ አመታትን በእስር ለማሳልፍ የሚገደድ በመሆኑ ዉጤቱ በቤተሰቡ፣ በራሱ እና በጥገኞቹ እና በእርሱ በሚረዱት ሰዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ከተበዳሪም አንጻር ስንመለከት አራጣ በሚበደርበት ወቅት በአፋጣኝ ገንዘቡን ለማግኘት የሚፈልግ በመሆኑ ከፍተኛዉን የወለድ ሚጣኔ ተደራድሮ ለማስቀነስ የሚያዳግተዉ በመሆኑ ሰርቶበት ሆነ ችግሩን ተወጥቶ ብድሩን መመለስ የሚያዳግተዉ በመሆኑ ቋሚ ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረቱን/ጥሪቱን ሰብስቦ ለአበዳሪዉ በመስጠት ጎዳና ላይ የመዉጣት እድሉ ሰፊ ነዉ፡፡ በስራ ላይም ቢሆን አራጣ በአዳሪዎች አብዛኛዉን ጊዜ የሚሰሩት ትርፋቸዉን ሰብስበዉ ንብረት ለማፍራት ሳይሆን ዕዳቸዉን ለመክፈል መሆኑን በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል፡፡ ከላይ በአበዳሪዉ ላይ እናዳየዉ የአራጣ ተግባር ዉጤቱ በሌሎች ሰዎች ላይ ጭምር አሉታዊ ተጽእኖ የሚኖረዉ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በአራጣ አበዳሪ እና ተበዳሪ ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁኔታ በጠቅላላዉ ማህበረሰቡ ላይ ከሚያደርሰዉ ተጽእኖ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በመሆኑም ማንም ሰዉ ከአራጣ ተግባር እንዲታቀብ ጸሀፊዉ ምክሩን ይለግሳል፡፡
Written by Melkamu Ogo on Abyssinia Law

Address

Adama

Telephone

911424549

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Abduljebar Hussein Law Office posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share