13/09/2026
ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ 8.5 ሚሊየን ብር ለመቄዶንያ አበረከተ
“መስከረም 3 የምህረትአብ ቀን እንዲሆን ወስነናል” — ዶ/ር ቢኒያም በለጠ
በማህበራዊ ድጋፉ የሚታወቀው ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ፣ የ2019 ዓ/ም አዲስ ዓመትን በማስመልከት ዛሬ መስከረም 3/2019 ዓ/ም በመቄዶንያ በጎ አድራጎት ተገኝቶ ለሚረዷቸው 9,000 አቅመ ደካማ ወገኖች የምሳ ማብላት መርሃ ግብር አካሂዷል።
ለዚህ የምሳ ማብላት መርሃ ግብር 4.5 ሚሊየን ብር የመደበው ምህረትአብ፣ በተጨማሪም 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ በአጠቃላይ 8.5 ሚሊየን ብር ለመቄዶንያ አበርክቷል።
ምህረትአብ በዚህ አጋጣሚ፣ መቄዶንያ የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት ያለበት ቤት መሆኑን ገልጾ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ተቋም ማገዝና መደገፍ እንደሚገባው ጠቁሟል። በተጨማሪም ስለመቄዶንያ የማይገባ ንግግር የሚያደርጉ ሰዎችን እግዚአብሔር ልቦና እንዲሰጣቸው መልዕክት አስተላልፏል።
የመቄዶንያ መስራች ዶ/ር ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፣ ምረትአብ ሙሉጌታ የሁሌም ደጋፊያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
“ምህረትአብ በየጊዜው ነው የሚያግዘን። እሱ እንደሌሎች ባለሀብቶች ብዙ ሀብት ያለው ሰው ላይሆን ይችላል፤ ግን ያለውን እያመጣ የሚሰጠን ነው። መስጠት ያስደስተዋል፣ ጓደኞቹንም እያስመጣ እንዲያግዙን ያደርጋል” ብለዋል።
ዶ/ር ቢኒያም በለጠ አክለውም፣ “መስከረም 3ን የምህረትአብ ቀን ብለን ሰይመንለታል” በማለት ለምረትአብ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
🌴🌴🌴