03/12/2025
የወንጀል ህግ እና የፍሐብሔር ህግ ልዩነት
ህጎች የተለያዩ ዓላማዎችን መሰረት በማድረግ ሊከፋፈሉ የሚችሉ ሲሆን ከክፍፍል አይነቶች ውስጥ የወንጀል ህግ እና የፍሐብሔር ህግ ክፍፍል አንዱ ነው፡፡ በመሰረቱ የወንጀል ህግ የህብረተሰብ ህግ (public law) አካል ሲሆን የፍሐብሔር ህግ ደግሞ የግል ህግ (private law) አካል ነው፡፡ ህጎች በወንጀል እና በፍሐብሔር ሲከፈሉ የተሳታፊ አካላትን (parties)፣ የሚያካትቱትን ጉዳይ፣ የሚያስከትሉትን የሀላፊነት አይነት እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ የወንጀል እና የፍሐብሔር ህግን መሰረታዊ ልዩነቶች እንዲሁም ጉዳዮቹን የማየት ስልጣን ያላቸውን አካላት የምንዳስስ ይሆናል።
የወንጀል ህግ
የወንጀል ህግ ህብረተሰቡን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚወጣ እና የወንጀል ድርጊቶችን ከነቅጣታቸው የሚዘረዝር ህግ ሲሆን ዓላማውም ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን የመንግስት፣ የህዝብን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው (የወንጀል ህግ አንቀጽ 1)፡፡ ይህ ማለት የወንጀል ህግ በዋናነት የህብረተሰቡን አጠቃላይ ጥቅም የሚያረጋግጥ ህግ ነው። ስለሆነም አንድ የወንጀል ድርጊት በአንድ ግለሰብ ላይ ቢፈፀምም ድርጊቱ የህብረተሰቡን ጠቅላላ ጥቅም የሚነካ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱን በዛ ግለሰብ ላይ የደረሰው ጉዳት ለምሳሌ የአካል ጉዳት ቢሆን በግለሰቡ ላይ ብቻ የሚቆም አይሆንም፡፡ ግለሰቡ ላይ በሚደርሰው የጤና እክል ምክንያት የህብረተሰቡ ጠቅላላ ጥቅም ለምሳሌ ጥፋት ፈፃሚው ላይ ተገቢው ቅጣት ወይም እርምጃ ካልተወሰደ ተመሳሳይ ድርጊቶች የመከሰት እድላቸው ስለሚጨምር እና ይህ ደግሞ ቂም በቀልን ስለሚያስፋፋ መንግስት በግለሰብ ላይ ለሚደርስ የወንጀል ድርጊት የዋናውን ድርሻ በመውሰድ በፖሊስ ምርመር እንዲጣራ በማድረግ በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲቀጡ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ዜጎች ምንም አይነት ክፍያ ሳይከፍሉ በወንጀል ጉዳዮች በመንግስት በመወከል መብታቸው እንዲከበር ይደርጋል፡፡
የወንጀል ሕጉ አምስት ዓላማዎች ለማስፈፀም ያለመ ሲሆን እነዚህም መቅጣት (retribution)፣ መከልከል (deterrence)፣ አቅም ማሳጣት ወይም ማገድ (incapacitation)፣ ማረም (rehabilitation) እና መልሶ ማቋቋም (restoration) ናቸው። በሌላ በኩል የተለያዩ የወንጀል የቅጣት አይነቶች ያሉ ሲሆን እነሱም፡- ማስጠንቀቂያ እና ተግሳፅ፣ የገንዘብ መቀጮ፣ የግዴታ ሥራ፣ ከህዝባዊ መብቶች መሻር፣ እስራት እና የሞት ቅጣት ናቸው፡፡
የወንጀል ድርጊቶች በሰዎች አካል፣ ህይወት ወይም ንብረት ላይ ሆን ተብለው ወይም በቸልተኝነት ሊፈፀሙ ይችላሉ፡፡ በሰው አካል ላይ የሚፈፀም ጉዳቶች ለምሳሌ በአካል ላይ ጉዳት ማድረስ (ጥርስ ማውለቅ)፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ ደግሞ ስርቆት፣ ማታለል፣ ሆን ብሎ ንብረት ማውደም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የወንጀል ድርጊት ማድረግ ያለብንን ባለማድረግ ሊፈፀም ይችላል፡፡ ለአብነት ያክል በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰው አለመርዳት (የወንጀል ህግ አንቀፅ 575) በህግ የተጣለውን ግዴታ ባለማድረግ ከሚያስቀጡ ወንጀሎች አንዱ ነው፡፡
የወንጀል ድርጊቶች ተፈፅመው ሲገኙ ተበዳዩን በመወከል ክስ የሚከሰው የመንግሰት አካል የሆነው ዐቃቤ ህግ ነው፡፡ የወንጀልን ድርጊት ለማስረዳት የሚቀርበው ማስረጃ ወንጀሉ መፈፀሙን ከጥርጣሬ በፀዳ (beyond reasonable doubt) መልኩ የሚያስረዳ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የወንጀል ቅጣት የሰዎችን ነፃነት ብሎም ህይወት የሚያሳጣ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ስለሆነም በወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው ጥፋተኝነቱ በማስረጃ እስኪረጋገጥ ድረስ ነፃ ነው ተብሎ የመገመት መብት (presumption of innocence) አለው፡፡
በግል አቤቱታ ከሚያስቀጡ ወንጀሎች ውጪ ወንጀል መፈፀሙን ያወቀ ማንኛውም ሰው ምርመራ እንዲጣራ ለፖሊስ ማመልከት ይችላል፡፡ ይህ ማለት በወንጀል ጊዜ በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት ሳይሆን በመጀመሪያ ወደ ፖሊስ በመሄድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ምርመራ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው በወንጀል ሊጠየቅ የሚችለው ራሱ በፈፀመው ወንጀል ብቻ ነው፡፡ በህግ የተጣለበት ልዩ ግዴታ ከሌለበት እና ይህንን ግዴታውን አለመወጣቱን ካልተረጋገጠበት በቀር ሌላ ሰው ለፈፀመው ድርጊት የወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ የለም (የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ መሆን)፡፡
የፍትሐብሔር ህግ
የፍትሐብሔር ህግ በግለሰቦች መካከል፣ በግለሰቦች እና በድርጅቶች መካከል፣ በመንግስት እና በግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች መካከል ያለን ግንኙነት የሚገዛ ህግ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ክስ የሚቀርበው የፍትሐብሔር ጉዳት ደርሶብኛል በሚል ወገን ሲሆን ክስ አቃራቢው የደረሰበትን ጉዳት መጠን በመግለፅ ጉዳቱ እንዲካስ ክስ ማቅረብ ይችላል፡፡
የፍትሐብሔር ህግ ዓላማ የደረሰን ጉዳት መካስ ወይም ተከራካሪ ወገኖች ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ወደ ነበሩበት መመለስ ሲሆን በተጨማሪም ያለአግባብ እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶችን ማገድ (injunction) ለምሳሌ ሁከት ማስወገድ እና መፈፀም ያለበት ነገር ግን ያልተፈፀመ ድርጊት ካለ ለአብነት ንብረት ለመሸጥ በተደረገ ስምምነት ላይ ሻጩ ገንዘብ ከተቀበለ በኃላ ንብረቱን ለገዢው ካላስረከበው ንብረቱን እንዲያስረክበው ማስገደድን ያካትታል፡፡ በአጠቃላይ የፍትሐብሔር ህግ ከገንዘብ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ያለው ሲሆን በተጨማሪም ግለሰባዊ ግንኙነቶችን ለምሳሌ ፍቺ፣ የልጆች አያያዝና ቀለብ የመሳሰሉት የተካተቱበት ነው፡፡
በፍትሐብሔር ህግ የሚካተቱ ጉዳዮችን እንደ ምሳሌ ብናይ የቤተሰብ ህግ፣ የውርስ ህግ፣ የውል ህግ፣ የንብረት ህግ፣ ከውል ውጪ ስለሚኖር ሀላፊነት ህግ፣ አሰሪና ሰራተኛ ህግ እና ሌሎችም ናቸው፡፡ በፍትሐብሔር ጉዳይ አንድ ሰው ራሱ በፈፀመው ወይም ባልፈፀመው ድርጊት ብቻ ሳይሆን እሱ ሀላፊ የሆነባቸው ሰዎች ወይም ንብረቶች ባደረሱት ጉዳት ተጠያቂ ወይም ሀላፊ የሚሆንበት ሁኔታ አለ (የፍትሐብሔት ህግ 2027)፡፡ ለምሳሌ አስራ ስምንት አመት ያልሞላው ልጁ በሰው ላይ ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ቢያደርስ የፍትሐብሔር ካሳ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡
የፍትሐብሔር ክስን ለማስረዳት የሚያስፈልገው ማስረጃ በአብላጫ ወይም በአመዛኝ (preponderance of evidence) የሚያስረዳ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ማለት ብልጫ ያለው ወይም 50+1 ማስረጃ ያቀረበ ወገን አሸናፊ ይሆናል፡፡ በወንጀል ጊዜ ግን ከጥርጥሬ በፀዳ ሁኔታ ማስረዳት ግድ ይላል፡፡ በፍትሐብሔር ክስ ላይ የቀረቡትን ክሶች ተከሳሹ በዝርዝር እያንዳንዱን ክዶ ካልተከራከረ ወይም በዝምታ ካለፋቸው እንዳመነ ይቆጠራል፡፡ በታመኑ ጉዳዮች ላይ ማስረጃ መመርመር ሳያስፈላግ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መስጠት ይችላሉ፡፡ በወንጀል ጉዳይ ግን ተጠርጣሪው ቢያምንም ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነ ጊዜ ማስረጃዎችን ሊሰማ ይችላል፡፡
የወንጀል እና የፍትሐብሔር ጉዳይን የማየት ስልጣን ያላቸው አካላት
የወንጀል እና የፍትሐብሔር ጉዳዮች እንደመለያየታቸው መጠን ጉዳዮቹን ተቀብለው የሚያዩት የመንግስት አካላት እና ጉዳዮቹ የሚስተናገዱበት ሂደት የተለያየ ነው፡፡
የወንጀል ጉዳይ የሚታየው በወንጀል ፍትህ ሥርዓት ውስጥ ሲሆን የወንጀል ፍትህ ሥርዓት (criminal justice system) ወንጀልን በመከላከል ላይ የሚያተኩር ቢሆንም ወንጀል ስለመፈፀሙ አመላካች ነገር ሲገኝ የወንጀል ምርመራ ማድረግ፣ ክስ ማቅረብ፣ ውሳኔ ማሰጠት፣ ቅጣት ማስፈፀም እና አጥፊው ታርሞ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችል ተግባር መፈፀምን ይጨምራል፡፡
እያንዳንዱ የወንጀል ፍትህ አካል (ተቋም) የሚወጣው የራሱ ተግባር ያለው ሲሆን እነዚህ ተግባራት ግን ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ አይደሉም፡፡ አንዱ የሚሰራው ሥራ የሚሰራበት መንገድ በሌላኛው ላይ ቀጥተኛ የሆነ ውጤት አለው፡፡ ከዚህ አኳያ የወንጀል ጉዳይ እንዲያዩ የተመደቡ ፍርድ ቤቶች የሚያዩት በፖሊስ እና ዐቃቤ ህግ የቀረበውን ነው። ማረሚያ ቤቶች የሚያርሙት በፍርድ ቤቶች ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ ያገኙትን ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች የሚያርሙበት መንገድ (ቅጣትን የሚያስፈፅሙበት መንገድ) በቀጣይ መሰል ጥፋት በቀድሞ አጥፊ ተፈፅሞ እንደገና በፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤት ላይ ጫና እንዳይፈጥር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ከላይ እንደተገለፀው በወንጀል ጉዳይ ውስጥ የሚሳተፉት የመንግስት አካላት ፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤት እና ማረሚያ ቤቶች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ወንጀል ተፈፅሞብኛል የሚል አካል ወይም ወንጀል መፈፀሙን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው የወንጀል ጥቆማ ለፖሊስ ማቅረብ አለበት፡፡ ፖሊስ የቀረበለትን ጥቆማ ወይም አቤቱታ ከዐቃቤ ህግ ጋር በመመርመር ዐቃቤ ህግ ክስ በመመስረት ፍርድ ቤቶች ደግሞ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ይህን በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ የሚያስፈፅሙት ማረሚያ ቤቶች ናቸው፡፡
በወንጀል ጉዳይ ተበዳይ የሆነ ሰው ለሚደረግለት የፍትህ አገልግሎት ምንም አይነት ክፍያ መክፈል አይጠበቅበትም፡፡ ይልቁንም ተበዳይን ወክሎ ክስ የሚከሰው እና የሚከራከረው ዐቃቤ ህግ ሲሆን ተበዳይ ደግሞ እንደ ዐቃቤ ህግ አንድ ምስክር ተቆጥሮ የፍትህ ስርዓቱን ያግዛል ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ጉዳይ በግለሰቦች መካከል ያለን ግንኙነት የሚገዛ የህግ አካል እንደመሆኑ መጠን የፍትሐብሔር ክስ መቅረብ የሚችለው ጉዳዩ ይመለከተኛል በሚል (vested interest) ባለው ወይም ጉዳት ደርሶብኛል የሚል ወገን እና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37/2 መሰረት አንድን ቡድን ወክሎ አቤቱታ የማቅረብ መብት ባለው ወገን ብቻ ነው፡፡ በፍትሐብሔር ጉዳይ ክስ የሚቀርበው ቀጥታ ለፍርድ ቤት ሲሆን በህግ በተፈቀዱ ጉዳዮች በግልግል ዳኝነት እልባት ሊያገኙ ይችላሉ።
የፍትሐብሔር እና የወንጀል ህግ ከተሳታፊ አካላትን (parties)፣ ከሚያካትቱት ጉዳይ፣ ከሚያስከትሉትን የሀላፊነት አይነት እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች አንፃር በርካታ ልዩነቶች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህል ልዩነቶች በአግባቡ መረዳት ሰዎች ጉዳያቸውን ሳይንገላቱ በሚመለከተው አካል እንዲፈፀምላቸው ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ