ለሚ ኩራ ፍትህ ጽ/ቤት-Lemi Kura Justice Office

ለሚ ኩራ ፍትህ ጽ/ቤት-Lemi Kura Justice Office Providing legal information and guidance, Protecting public and governmental interests through litigation

11/08/2026
23/07/2026

በትዳር ጓደኛ ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

መግቢያ
ትዳር በሕግ ጥበቃ የሚሰጠው የቤተሰብ መሠረት ሲሆን ተጋቢዎች እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩ፣ እንዲተጋገዙ፣ ውሳኔዎችን በመመካከር እንዲወስኑ እንዲሁም ልጆቻቸውን በመረዳዳት እንዲያሳድጉ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም በባለትዳሮች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት መነሻነት አንዱ በሌላው ላይ ጥቃት የሚያደርሱበት አጋጣሚ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈፀም አካላዊ ጉዳት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ በወንጀልነት የተደነገገ እና የወንጀል ተጠያቂነትንም የሚስከትል ድርጊት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዋና ዐላማም ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በአጭሩ መዳሰስ ይሆናል፡፡

የአካል ጉዳት ምንነት
ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 555 እና 556 ፍሬ ነገሮች በመነሳት የአካል ጉዳት ማለት ለተጎጂ ሕይወት የሚያሰጋ ወይም በሰውነትም ሆነ በአእምሮ ላይ ዘወትር ጠንቅ የሚያተርፍ ጉዳት፣ የተጎጂው አካል ወይም ከሕዋሳቶቹ አንዱ መጉደል፣ እንዳያገለግሉ መሆን፣ በሚያሰቅቅና ጉልህ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ የመልክ መበላሸት እንዲሁም ከባድ ባይሆን እንኳን በተጎጂው አካል ወይም ጤና ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው፡፡

የወንጀል ተጠያቂነት
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 564 በትዳር ጓደኛ ወይም ከጋብቻ ውጪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብሮ በሚኖር ሰው አካል ወይም የአእምሮ ጤንነት ላይ ከባድ ወይም ቀላል ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ጥቃት ማድረስ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 555 እስከ 560 ድንጋጌዎች መሠረት ተጠያቂነት እንደሚስከትል ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት
* የትዳር ጓደኛን ሕይወት በሚያሰጋ ወይም በሰውነትም ሆነ በአዕምሮ ላይ ለዘወትር ጠንቅ በሚያተርፍ ሁኔታ ጉዳት ማድረስ ወይም አስፈላጊ ከሆኑት ብልቶች ወይም ሕዋሳቶች አንዱን ማጉደል፣ እንዳያገለግሉ ማድረግ ወይም በሚያሰቅቅና ጉልህ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ መልክ ማበላሸት ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከባድ የሆነ ጉዳትን ወይም በሽታ በትዳር ጓደኛ ላይ አስቦ እንዲደርስ ማድረግ እንደነገሩ ሁኔታና እንደጉዳቱ ክብደት ከአስራ አምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ወይም ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 555 መረዳት ይቻላል፡፡
* በተያያዘም ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ውጪ አስቦ በትዳር ጓደኛ ላይ ጉዳት ማድረስ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 556 መሠረት የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ያስቀጣል፡፡ ሆኖም
• ጥፋተኛው ጉዳቱን ያደረሰው በመርዝ ወይም በገዳይ መሳሪያ ወይም የአካል ጉዳት ለማድረስ በሚችል በማናቸውም ሌላ መሳሪያ በመጠቀም ከሆነ
• ጥፋተኛው የሙያ ወይም ሌላ ግዴታን በመተላለፍ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ
• ተጎጂው የትዳር ጓደኛ ደካማ፣ በሽተኛ ወይም ራሱን ለመከላከል የማይችል ከሆነ
ድርጊቱ በወንጀል ክስ አቅራቢነት ከስድስት ወር እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
* በሌላ በኩል በቸልተኝነት በትዳር ጓደኛ ላይ ጉዳት ማድረስም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 559 ተጠያቂነት የሚያስከትል ድርጊት ነው፡፡ በዚህም በቸልተኝነት በትዳር ጓደኛው አካል ወይም ጤንነት ላይ ቀላል ጉዳት ያደረሰ ሰው ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከብር አንድ ሺ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ሆኖም
• የደረሰው ጉዳት ከላይ በአንቀጽ 555 የተመለከተው ዓይነት (ከባድ የአካል ጉዳት) ከሆነ ወይም
• ጉዳት አድራሹ የሌላን ሰው አካል ወይም ጤንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ ያለበት እንደ ህክምና ባለሞያ ያለ ሰው ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማያንስ ቀላል እስራትና ከብር አንድ ሺ የማያንስ መቀጮ ይሆናል፡፡

ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳው እጅ እልፊት ሲሆን ይህም አካል ጉዳት ወይም የጤንነት ጉድለት ባስከትልም እንደሰንበር፣ የደም መቋጠር ምልክቶች ወይም በቶሎ የሚያልፍ ሕመም የመሳሰሉ የመጋፋት ድርጊቶች በትዳር ጓደኛ ላይ መፈፀም የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከብር ሶስት መቶ በማይበልጥ መቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜም በሶስት ወር በማይበልት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ነው፡፡

ማጠቃለያ
ትዳር በተጋቢዎች መካከል የመከባበር ግዴታ የሚጥል እንደመሆኑ ተጋቢዎች መደማመጥና መከባበር የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህንን ተላልፎ በትዳር ጓደኛ ላይ የአካል ጉዳት ማድረስ ወይም የእጅ እልፊት መፈፀም የወንጀል ተጠያቂነት የሚስከትል መሆኑን መገንዘብና ከመሰል ድርጊት መታቀብ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externabo

16/07/2026

የግዥ ዘዴዎች በኢትዮጵያ የንብረት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሕግ

መግቢያ

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሕዝባዊ አገልግሎቶችን በብቃት ለመስጠትና ተልኳቸውን ለመወጣት የሚያስፈልጓቸውን ግብአት ማለትም ዕቃዎች፣ ሥራዎች እንዲሁም አገልግሎቶች በወቅቱና በጥራት ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህንን ፍላጎት በማሟላት ሂደት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 ተቋማት ሊከተሏቸው የሚገቡ አራት መሠረታዊ የግዥ ዘዴዎችንና ስልቶችን በግልጽ አስቀምጧል። እነዚህም ግልጽ ጨረታ፣ በማጣሪያ የሚከናወን ጨረታ፣ ውስን ጨረታ እና በቀጥታ የሚፈፀም ግዥ ናቸው። አዋጁ የመንግሥትን የፋይናንስ ጥቅም በላቀ ደረጃ ለማስከበር ሲባል ማንኛውም መሥሪያ ቤት ከተደነገጉት ከእነዚህ አራት ስልቶች ውጪ ግዥ መፈጸም እንደማይችል በጥብቅ ይከለክላል። ይሁን እንጂ መደበኛውን ሥርዓት ተከትሎ ግዥ ለመፈጸም የማይቻልባቸው ልዩ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ የሚቻልበት የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል። ይህ ጽሑፍ የጨረታን ምንነት፣ በአዋጁ የተደነገጉትን አራቱን የመንግሥት ግዥ ዘዴዎች፣ እያንዳንዱን ስልት ለመጠቀም መሟላት ያለባቸውን ቅድመ-ሁኔታዎችና መተግበሪያ መስፈርቶች በአጭሩ ይዳስሳል።

የጨረታ ምንነት
በአዋጁ አንቀጽ 2(13) መሠረት ጨረታ ማለት የግዢ ወይም የንብረት ሽያጭ ማስታወቂያ ይፋ ከሆነበት ወይም ጥሪ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ አሸናፊው ተለይቶ ውል እስኪፈፀም ድረስ ያለው የግዥ አፈፃፀም ወይም የንብረት ሽያጭ ሂደት ነው፡፡

ግልጽ ጨረታ (Open Tendering)
በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 31 መሠረት ግልጽ ጨረታ ለማንኛውም ፍላጎትና ብቃት ላለው አቅራቢ እኩል እድል የሚሰጥ ሲሆን በመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን በተዘጋጀ መደበኛ የጨረታ ሰነድ የሚከናወን መደበኛ ሥርዓት ነው። በአዋጁ አንቀጽ 35(1) መሠረት ከሚፈፀመው የግዢ አይነት፣ ባህሪ እና የገንዘብ መጠን በመነሳት ብሔራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ ጨረታ ሊሆን ይችላል፡፡

ብሔራዊ ግልጽ ጨረታ የተፈለገው ዕቃ ወይ አገልግሎት በአገር ውስጥ ብቻ ሊቀርብ የሚችል መሆኑ ሲረጋገጥ የገንዘብ ገደብ ሳደረግበት ወይም ግዢው በአገር ውስጥ ተጫራቾች ሊሟላ የሚችል ሲሆን ደግሞ ዋጋው ለግንባታ ሥራ እስከ ሶስት ቢሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዥ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር፣ ለምክር አገልግሎት እስከ ዘጠና ሚሊዮን ብር እና ከምክር ውጭ ለሆኑ አገልግሎቶች እስከ 250 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ ከሆነ ስለመሆኑ ከአዋጁ አንቀጽ 35(2) እና ከፌደራል መንግሥት ግዢ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 አንቀጽ 54(2) ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ደግሞ የግዥው ግምታዊ ዋጋ ከተቀመጡት የገንዘብ ጣሪያዎች በላይ ሲሆን ወይም ዋጋው ከጣሪያው በታች ቢሆንም እንኳ የውጭ አገር ተጫራቾች ካልተሳተፉ ግዥው ውጤታማ እንደማይሆን ሲረጋገጥ ጥቅም ላይ እንደሚውል በአዋጁ አንቀጽ 35(3) ተመልክቷል፡፡

በማጣሪያ የሚከናወን ጨረታ (Selective Tendering)
በማጣሪያ ጨረታ ውስብስብ እና ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ማዘጋጀት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሁለት ዙር ጨረታ በማዘጋጀት ፍላጎታውን የሚያሟላ የጨረታ ሰነድ የሚያቀርብ ተጫራች የሚመርጡበት የግዥ ዘዴ ሲሆን አሸናፊ ሆኖ የሚመረጠው ወደ ሁለተኛው ዙር ከተሸጋገሩ ተጫራቾች መካከል ስለመሆኑ ከአዋጁ አንቀጽ 32 ተደንግጓል፡፡
የሁለት ደረጃ ጨረታን ተግባራዊ ለማድረግ በአዋጁ አንቀጽ 31(2) ከተቀመጡት አራት ቅድመ-ሁኔታዎች ቢያንስ አንዱ መሟላ አለበት። ይኸውም፡-
 መሥሪያ ቤቱ የሚገዛውን ዕቃ ወይም አገልግሎት ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ለማዘጋጀት አስቸጋሪ ሆኖ የግዢ ፍላቱን በከፍተኛ ደረጃ ለማሟላት የሚያስችል መፍትሄ ሲገለግ
 ግዥው ለመሥሪያ ቤቱ ምርምር፣ ሙከራ፣ ጥናትና ልማት ሥራዎች የሚውል ሲሆን
 ቀደም ሲል ጨረታ ወጥቶ የሚፈለገው ግዢ ባህሪ ግልጽ ባመሆን ምክንያት ተወዳዳሪዎች ሳይቀሩ ሲቀሩ ወይም የቀረቡት ሰነዶች በሙሉ ውድቅ ሲደረጉ እና ይም የሆነው የተሟላ የፍላጎት መግለጫ መዘጋጀት ባለመቻሉ እንደሆነ ሲታመን እንዲሁም
 የሚገዛው ዕቃ፣ አገልግሎት፣ከምክር ውጪ የሆነ አገልግሎት ወይም የግንባታ ሥራ ባህሪ ወይም ተፈጥሮን አስመልክቶ ከተወዳዳሪዎች ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡
ውስን ጨረታ (Limited Tendering)
ውስን ጨረታ የጨረታ ማስታወቂያ ማውጣት ሳያስፈልግ ቁጥራቸው ውስን ለሆኑ ተሳታፊዎች በኤሌክትሮኒክ ሥርአት አድራሻቸው በሚላክ ግብዣ የሚቀርቡ ተጫራጮችን በማወዳደር አሸናፊ የሚለይበት ዘዴ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 33 ተመልክቷል፡፡ ይህ ዘዴ ከመደበኛው ግልጽ ጨረታ የሚለየው በዋናነት ለሁሉም ክፍት ባለመሆኑ ሲሆን በሁለት መንገዶች ይፈጸማል። የመጀመሪያው የተገደበ ጨረታ ሲሆን ተግባራዊ የሚሆነው በአዋጁ አንቀጽ 33(3) እና በመመሪያው አንቀጽ 63 መሠረት
o ግዥው ከተወሰኑ አቅራቢዎች ብቻ የሚገኝ ሲሆን ወይም
o የግዥው መጠን በመመሪያው ከተቀመጠው የገንዘብ ጣሪያ ማለትም ለግንባታ ሥራ
ዘርፍ ከብር 60 ሚሊዮን፣ ለዕቃ ግዢ ከብር 12 ሚሊዮን፣ ለምክር አገልግሎት ከ7 ሚሊዮን እና ለአገልግሎት ግዢ ከ9 ሚሊዮን ካልበለጠ ወይም
o ቢያንስ አንድ ጊዜ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ ተወዳዳሪ ሳይገኝ ሲቀር ነው።
ሁለተኛው የዋጋ ማቅረቢያ ዘዴ ሲሆን ወዲያውኑ ጥቅም ላይ ሊውሉ ወይም በጅምላ ሊገዙ ያልቻሉ፣ ለገበያ የተዘጋጁና የታወቀ ገበያ ያላቸውን ዕቃዎች፣ የግንባታ ሥራዎች፣ የምክርና ሌሎች አገልግሎቶች ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ክፍት በማድረግ ወይም ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ክፍት በማድረግ ግዢውን መፈፀም የማይቻል መሆኑ በመ/ቤቱ የበላይ ኃላፊ ሲረጋገጥ ደግሞ ከሦስት ያላነሱ ተጫራቾችን በመጋበዝ ለመግዛት የሚያገለግል ነው፡፡ የመንግሥት መ/ቤቶች በዚህ ዘዴ ግዢ መፈፀም የሚችሉት ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን ያልበለጠ እና የሚገዙት ዕቃዎች ለገበያ ተብለው የተዘጋጁ፣ ወዲያው ጥቅም ላይ የሚውሉ ወይም በጅምላ ሊገዙ ያልቻሉ ወይ የታወቀ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች፣ የምክር አገልግሎቶች፣ የግንባታ ሥራዎችና ሌሎች አገልግሎቶች ሲሆኑ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 33(4) ና (5) እንዲሁም በመመሪያው አንቀጽ 64 ተመልክቷል፡፡ ሆኖም የፌዴራል ትምህርትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም የሕክምና ተቋማት ለምግብ ግብዓቶች፣ ለምርምርና ለሕክምና መሣሪያዎች ግዥ ይህንን የዋጋ ማቅረቢያ ዘዴ በልዩ ሁኔታ እንዲጠቀሙ በአዋጁ ተፈቅዶላቸዋል።

ቀጥተኛ ግዥ (Direct Procurement)
በቀጥታ የሚፈጸም ግዥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዕቃዎች፣ ሥራዎች ወይም አገልግሎቶችን ያለ ምንም የገበያ ውድድር ከአንድ ከተወሰነ አቅራቢ ብቻ የሚያገኙበት እና እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚወሰድ ልዩ የግዥ ስልት ነው። ይህንን ዘዴ ለመጠቀም በቂና ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ የቅድመ-ፈቃድ ማረጋገጫ ማግኘት የሚገባ ሲሆን አዋጁ ስልቱ ተግባራዊ የሚሆንባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በጥብቅ ደንግጓል። ይኸውም
• የሚፈለገው ዕቃ ወይም አገልግሎት ከአንድ አቅራቢ ብቻ የሚገኝ ሲሆን
• ግዢው በጣም አስቸኳይ ከመሆኑ የተነሳ ወዲያው ካልተፈፀ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ችግር የሚፈጥርና መ/ቤቱ ሥራ አፈፃፀም ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ሲረጋገጥ
• የሚፈለገውን አቅርቦት በሌሎች የግዥ ዘዴዎች ማሳካት ያልተቻለ መሆኑ ሲረጋገጥ
• አስቀድሞ ለተገዙ አቅርቦቶች መለዋወጫ እቃዎች ወይም ተጨማሪ አገልግሎቶችን መግዛት ሲያስፈልግ እና እነዚህን አቅርቦቶች ከሌላ ተወዳዳሪ መግዛት መ/ቤቱ ከሚጠቀምበት ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ምክንያት ከመጀመሪያው አቅራቢ መግዛት ግድ ሲሆን
• በመጀመሪያው ውል ያልተካተቱ ተጨማሪ ግንባታዎችን ከመጀመሪያው ተቋራጭ ነጥሎ ማሠራት በቴክኒክም ሆነ በኢኮኖሚ አዋጭ ካልሆነ
• ቀደም ሲል በውድድር የተመረጠ አቅራቢ ሥራውን በአጥጋቢ ሁኔታ አጠናቆ በዚያው እንዲቀጥል ሲፈለግ
• ለተለየ የግዢ ፍላጎት ማሟያ በለቀማ ግዢ መፈፀም የሚያስገድድ ሁኔታ ሲፈጠር
• ሽያጩ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ፣ ለመ/ቤቱ ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ እና በመደበኛ አቅራቢነት ከተሰማሩ ተወዳዳሪዎች ሊገኝ የማይችል ዕቃ ወይም አገልግሎት ሲሆን
• የመንግሥት ባለበጀት መ/ቤቶች ለሚኖራቸው የግዥ ፍላጎት ወጪን በመሸፈን ከመንግሥት ባለበጀት መ/ቤት ግዢ መፈፀም ሲያስፈልግ
• ለምርምር ወይም ለሕክምና የሚውሉ ሚስጥራዊ ግዥዎች ሲሆኑ
• በሌላ መሥሪያ ቤት በግልጽ ጨረታ ከተገዛ ዕቃ ወይም ከምክር ውጪ የሆነ ሌላ አገልግሎት ጋር በዓይነትና በዋጋ አንድ ዓይነት ሆኖ ቀደም ሲል አቅርቦቱን ከፈፀመ አቅራቢ ለአንድ ጊዜ ብቻ መፈፀም ከጊዜና ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር አዋጭ መሆኑ በመ/ቤቱ የበላይ ኃላፊ ሲታመንበት
• ዋጋቸው በመንግሥት በቀጥታ የሚወሰን ዕቃዎችና ከምክር ውጪ የሆኑ አገልግሎቶች ሲሆኑ እንዲሁም
• አቅርቦቱ ከሚታወቁ እና ገንዘብ ሚኒስቴር በየጊዜው በሚለየው የድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ በተካተቱ ድርጅቶች በበይነ መረብ ገበያ የሚገኝ፣ ዋጋው አስቀድሞ በበይነ መረብ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ፣ ግዢው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ የሚፈፀም እና የመ/ቤቱ የበላይ ኃላፊ በዚህ መልኩ ግዢው መፈፀሙ የመንግሥትን እና የመ/ቤቱን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ሲያምንበት እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 34 ተደንገግጓል፡፡

ይህ ዘዴ ጥቅም ላይ ሲውል የተጠያቂነትን መርህ ለማረጋገጥ እንዲያስችል መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ግዥ ለመፈጸም ያስገደዱትን ምክንያቶችና የቀረቡትን ተጨባጭ ማስረጃዎች በዝርዝር መመዝገብና ለኦዲት በሚያመች መልኩ ማደራጀት አለበት። በተጨማሪም ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚያቀርበው አንድ አቅራቢ ብቻ ቢሆንም እንኳ መንግሥት ለሚያወጣው ገንዘብ ተመጣጣኝ ጥራትና ትክክለኛ ዋጋ ማግኘቱን ለማረጋገጥ ጠንካራ የዋጋ ድርድር ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም በቀጥታ የሚፈጸም ግዥ ወደ ትግበራ ከመሸጋገሩ በፊት የግዥው አስፈላጊነትና አሳማኝነት በዝርዝር ቀርቦ ከፍተኛ ሥልጣን ካለው የመንግሥት አካል ወይም ከሚመለከተው የበላይ ኃላፊ የጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል።

ማጠቃለያ
በአዋጅ ቁጥር 1333/2016 ግልጽ ጨረታን እንደ ዋነኛ መርህ በማስቀመጥ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ቢሆንም እንደ ፍላጎቱ ውስብስብነትና እንደ ሁኔታዎቹ አስገዳጅነት በማጣሪያ የሚከናወኑ፣ ውስንና ቀጥተኛ የግዥ ስልቶችን በልዩ ሁኔታ ፈቅዷል። እነዚህ አማራጭ ዘዴዎች የተቋማትን የአሠራር ቅልጥፍና ለማሳደግና ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ አላቸው። ሆኖም አጠቃቀማቸው ሕጋዊ ቅድመ-ሁኔታዎች የተከተለ እና በጥብቅ ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል።

Source:- Ministry of Justice

26/06/2026

ማስታወቂያ

ቀን ሰኔ 19 /2018

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ኃላፊነት፤ የማህበራዊ አገልግሎትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ በተደራጀና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት የሚዘረጋ ሕግ አውጥቶ ተግባራዊ እያደርገ ይገኛል፡፡ በዚሁ ሕግ መሰረትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት ከ142 በላይ በጎፈቃደኛ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ የሕግ ባለሙያዎች ጥሪ አስተላልፎ በ11ዱም ክፍለ ከተማ በማሰማራት ለከተማው ህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡ ቢሮውም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሲሰጡ ለቆዩ የህግ ምሩቃን ላበረከቱት በጎ ስራ የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡
አሁንም በሁለተኛው ዙር በ2019 በጀት ዓመት በክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት (free legal aid service) በመስጠት ነዋሪዎችን ለማገልገል የምትፈልጉ የሕግ ምሩቃን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሚያሰማራችሁ ክፍለ ከተማ ወይም ወረዳ አስተዳደር በመገኘት አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆናችሁ ከሰኔ 25 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በየክፍለ ከተማው ፍትህ ጽህፈት ቤት ቀርባችሁ እንድትመዘገቡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ማሳሰቢያ፡ ለምዝገባ ስትመጡ ከዩኒቨርስቲ መመረቃችሁን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት እና መታወቂያ መያዝ ይኖርባችኋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ

11/02/2026

የፕላስቲክ ከረጢቶች /ፌስታል ምርቶችን/ መጠቀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት

መግቢያ
በኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥርና የከተሞች እድገትን ተከትሎ ባልተገባ መልኩ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች ማለትም እንደ ፕላስቲክ/ፌስታል/ ያሉት የአካባቢን ስነ ምህዳር በመበከል፣ የውሃ መስመሮችን በመዝጋት፣ ለረጅም ጊዜ ሳይበሰብሱ በመከማቸት ለተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት መንስኤ ሲሆኑ ይታያሉ። በተለይ የፕላስቲክ ምርቶች ሳይበሰብሱ ለብዙ ዓመታት በመቆየት የስነ ምህዳር ጠንቅ እንደሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮች ያወሳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ የአካባቢ እንክብካቤን የተመለከቱ ሕጎች ያሏት ሲሆን የሁሉም ሕግ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግስታችን ብንነሳ በአንቀጽ 44/1/ ስር ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በዚሁ ሕገ መንግስት አንቀጽ 92 ስር መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል። በዚህ መነሻነት የወንጀል ሕጉ እና ሌሎች አዋጆች ለምሳሌ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ቁጥር 513/1999 ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከጉዳቱ መጠን እና በኢትዮጵያ ካለው የስርጭት አድማስ አንጻር በተለይ የፕላስቲክ ምርትን አስመልክቶ የሕግ ማእቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኗል። ስለሆነም የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም የሚከለክል አለፍ ሲልም የወንጀል ቅጣትን የሚደነግግ አዋጅ ቁጥር 1386/2017 ወጥቶ በስራ ላይ ውሏል። በዚህ አጭር ጽሁፍም እነዚህን ክልከላዎች እና የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት እንዳስሳለን።

የፕላስቲክ ምርት/ፌስታል/ ምንነት
በአዋጅ ቁጥር 1383/2017 አንቀጽ 2/9/ ስር እንደተደነገገው ፕላስቲክ ማለት በዋናነት ከፔትሮኬሚካል የተሰራ፣ ለስላሳና የማይበሰብስ የፖሊመር ይዘት ያለው ምርት እንደሆነ ትርጉም ተሰጥቶታል። ይህም በተለምዶ ፌስታል ተብሎ የሚጠራውን ምርት የሚያመለክት ነው። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 2/10/ ስር እንደሰፈረው የፕላስቲክ ከረጢት ማለት አነስተኛ ጥግግት ያለው፣ በቀላሉ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ እና ሌሎች ምርቶችን ለመያዝ የሚያገለግል ፕላስቲክ እንደሆነ ተመላክቷል። ይኸውም የፌስታል ከረጢትን የሚያመለክት ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ፌስታል ጉዳይ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 2/11/ ስር አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ይኸውም መልሶ ጥቅም ላይ የማይውል ወይም መልሶ ኡደት የማይደረግ እና አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሎ ቀጥታ የሚወገድ የፕላስቲክ ምርት እንደሆነ በዚሁ ድንጋጌ ተገልጿል።

በፕላስቲክ ምርት/ፌስታል/ ላይ የተደረገው ክልከላ
ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ
• መጠቀም ወይም ለመጠቀም ይዞ መገኘት፣
• ማምረት፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ መሸጥ፣ ለንግድ ዓላማ ማከማቸት ወይም ይዞ መገኘት ክልክል መሆኑን እና አስተዳደራዊ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በአዋጁ አንቀጽ 24/9/ ስር ተደንግጓል። ሆኖም ግን የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች እንዲመረቱ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውሉ በልዩ ሁኔታ በመመሪያ ሊፈቅድ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 14 ስር ተደንግጓል።

የወንጀል ተጠያቂነት
በአዋጁ አንቀጽ 25 ስር ክልከላዎችን መተላለፍ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተደንግጓል። ይኸውም፡-
• ማንኛውም ሰው የፕላስቲክ ከረጢት/የፌስታል ከረጢት/ ከተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ ከተገኘ ከ2,000/ሁለት ሺህ ብር/ በማያንስና ከ5,000/አምስት ሺህ ብር/ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።
• ማንኛውም ሰው የፕላስቲክ ከረጢት/የፌስታል ከረጢት/ ካመረተ ወይም ወደ አገር ውስጥ ካስገባ፣ ለገበያ ካቀረበ ወይም ከሸጠ፣ ለንግድ ዓላማ ካከማቸ ወይም ይዞ ከተገኘ ከ50,000/ሀምሳ ሺህ ብር/ በማያንስና ከ200,000/ሁለት መቶ ሺህ ብር/ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እና ከ5/አምስት አመት/ በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ይኸውም የፕላስቲክ ከረጢት/ፌስታል/ ከግለሰባዊ አገልግሎት ውጪ ለንግድ ዓላማ ጥቅም ላይ ሲውል ከገንዘብ ቅጣት በተደራቢነት በእስራት እንደሚያስቀጣ መረዳት ይቻላል።
• ከላይ የተመለከቱትን የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ የገንዘብ ቅጣቱ ከላይ የተገለጸውን 3/ሶስት እጥፍ/ ይሆናል።

ማጠቃለያ
የፕላስቲክ ምርቶች/ፌስታሎች/ የአካባቢ ስነ ምህዳር ብሎም የሰዎች እና የእንስሳት ጤና ጠንቅ ናቸው። ይህንን ጉልህ የሆነ የጤና ጠንቅ ለመከላከል በምርቶቹ ላይ ክልከላ እና ተጠያቂነትን የሚደነግግ ሕግ ማውጣት አንዱ ዘዴ ነው። ኢትዮጵያም ፌስታል መጠቀምን የሚከለከል ህግ አውጥታ ተግባራዊ አድርጋለች። ስለሆነም ህብረተሰቡ እነዚህን ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶችን ባለመጠቀም አጠቃላይ የስነ ምህዳር ጤንነትን በማስጠበቅ ሂደት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ስልጠና የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

11/02/2026

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በተዋረድ የለሚ ኩራ ክ/ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ጽ/ቤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016
መሰረት ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል፡--
የለሚ ኩራ ክ/ከተማ አስተዳደር የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የሚያደርጉት አስተዳደራዊ ውል እንደ አስፈላጊነቱ በመመርመር ሕጋዊነታቸውን ማረጋገጥ፤ አፈፃፀማቸውን በመከታተል፤ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ወይም መውሰድ፤የክ/ከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላት የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ከህግ ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋጥ፤ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ወይም እንዲወስዱ ማድረግ፤
የራሳቸውን የሕግ አገልግሎት እንዲኖራቸው የተፈቀደላቸው አስፈፃሚ አካላት የህግ አገልግሎቶች ዕቅድ እና ወቅታዊ ሪፖርት እንዲቀርብለት በማድረግ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤ የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ፤ እና የከተማው አስተዳደር ያወጣቸው ሕጎች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን መከታል፤ መቆጣጠር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
04/062018ዓ.ም

27/01/2026
16/01/2026
13/01/2026

በመዲናዋ በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ በፍርድ ቤቶች በተደረጉ ክርክሮች ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም ማስከበር ቻለ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ክርክር የፍርድ ቤት ውሳኔ ካገኙ 1 ሺህ 491 መዝገቦች ውስጥ 1 ሺህ 382 መዝገቦች ለአስተዳደሩ ተወስኗል።

በዚህም 3 ቢሊየን 212 ሚሊየን 856 ሺህ 60 ብር እንዲሁም 101 ቤቶች፣ 19 መስሪያ ቦታ ሼዶች እና 178 ነጥብ 62 ሄክታር መሬት የሕዝብ መብትና ጥቅም ማስከበር መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ክርክር በፍርድ ቤቶች የመርታት አቅም ወደ 94 ነጥብ 7 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ 92 ነጥብ 7 በመቶ በማሳካት አፈፃፀሙም 98 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል፡፡

5 ሺህ 416 የግል አቤቱታ እና 981 የደንብ መተላለፍ በጥቅል 6 ሺህ 397 የወንጀል መዛግብት በመመርመር የማጥራት ሥራ መሰራቱን ገልጸው÷ ምርመራቸው ከተጠናቀቀባቸው የግል አቤቱታ ወንጀል መዝገቦች ውስጥ 4 ሺህ 639 መዛግብት በእርቅ እልባት አግኝቷል ብለዋል።

በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶ ውሳኔ ካገኘባቸው 1 ሺህ 314 የወንጀል መዛግብት በ1 ሺህ 307 መዝገቦች ላይ ማስቀጣት መቻሉንና 7 መዛግብት በነፃ መዘጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም 6 የነባር ሕጎች ማሻሻያ እና 30 አዳዲስ ሕጎች የማርቀቅ ተግባር ባለፉት ስድስት ወራት መከናወኑንም አቶ ተክሌ አስረድተዋል።

በአድማሱ አራጋው

👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ያግኙ:-

Address

Addis Ababa

Opening Hours

Saturday 09:00 - 17:00
Sunday 09:00 - 17:00

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ለሚ ኩራ ፍትህ ጽ/ቤት-Lemi Kura Justice Office posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share

Category