የህግ ክሊኒክ / Legal Clinic

የህግ ክሊኒክ / Legal Clinic Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from የህግ ክሊኒክ / Legal Clinic, Lawyer & Law Firm, Addis Ababa.

የመኪናው ባለቤት ወይም የሹፌሩ ጥፋት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በሌላ ሰዉ መኪና በነፃ ተሳፍሮ የሚሄድ ግለሰብ መኪናዉ ተገልብጦ ጉዳት ቢደርስበት የጉዳት ካሣ ሊጠይቅ የማይችል ስለመሆኑ  የሰ/መ...
22/12/2025

የመኪናው ባለቤት ወይም የሹፌሩ ጥፋት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በሌላ ሰዉ መኪና በነፃ ተሳፍሮ የሚሄድ ግለሰብ መኪናዉ ተገልብጦ ጉዳት ቢደርስበት የጉዳት ካሣ ሊጠይቅ የማይችል ስለመሆኑ

የሰ/መ/ቁ.24818

06/10/2025

ወሳኝ የውርስ ኬዝ
============
አውራሹ በህይዎት እያለ በስጦታ፣በመተዳደሪያ ንብረት የተቀበለ ወራሽ አውራሹ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የዉርስ ሀብት ክፍፍል ላይ ለመሳተፍ የሚፈልግ ከሆነ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 113247፣ 160761፣ 162475 እና በሌሎች መዝገቦች በሰጣቸዉ አስገዳጅ ዉሳኔዎች መሠረት አስቀድሞ በስጦታ የተቀበላቸዉን መመለስ አለበት።

ነገር ግን አስቀድሞ የወሰደውን ንብረት ወደ ውርሱ ለመመለስ ፍቃደኛ ካልሆነ ከቀሪዉ የዉርስ ሀብት ክፍፍል ዉጭ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
የሰ/መ/ቁ, 249367 ጥር 28 ቀን 2017

05/09/2025

የሰበር መዝገብ ቁጥር 74950
የብድር ገንዘብ መመለሻ ጊዜ በግልጽ ዉል ላይ ከሰፈረ ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልግም:-
---------------------------------------------------

ከብድር ውል ጋር በተገናኘ፣ የመመለሻ ጊዜው በግልጽ ተለይቶ የተሰጠን የገንዘብ ብድር በተመለከተ አበዳሪው በውሉ የተመለከተው ጊዜ ካለፈ በኋላ ተበዳሪው የብድሩን ገንዘብ እንዲመለስ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ የለበትም።

የብድሩ ገንዘብ መክፈያ ጊዜው በተወሰነ የብድር ውል ስምምነት ገንዘብ የተበደረ ወገን የመክፈያ ጊዜው ካለፈበት (ካበቃበት) ጊዜ ጀምሮ ወለድ ለመክፈል ስምምነት ያልተደረገ ቢሆንም፣ ብድሩን ከነሕጋዊ ወለዱ ለመክፈል ይገደዳል።

22/08/2025

የሙስና ወንጀል

መግቢያ

የሙስና ወንጀል ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል ወንጀል ነው። ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በሀገራችን ወንጀሉን ለመከላከል ህግ ከማውጣ በተጨማሪ ተቋማትን በማቋቋምም ወንጀሉን ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህም ባሻገር የወንጀሉ ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እና የተወሰደውን የመንግሰት እና የህዝብ ሀብት ለማስመለስ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በዚህ አጭር ጽሁፍም በሙስና ወንጀሎች አዋጅ 881/2007 የተካተቱ የሙስና ወንጀሎች ምንነትን እና የሚያስከትሉትን የህግ ተጠያቂነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የሙስና ወንጀል ምንነት
እንደ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት የቃሉ መሰረት ግእዝ ሲሆን ትርጉሙም ጥፋት፣ መበስበስ፣ መፍረስ፣ በመጥፎ ድርጊት መተዳደር ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ታዋቂው አለማቀፍ ድርጅት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ትርጉም ሙስና በአደራ የተሰጠን ስልጣን ለግል ጥቅም ማዋል ማለት ነው፡፡ ብላክስ ሎው የህግ መዝገበ ቃላትም ሙስና ከህጋዊ ሀላፊነት እና ከሌሎች ሰዎች ጥቅም በመጻረር ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የሚፈጸም ድርጊት ነው በማለት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡

የአገራችን ህግ ለሙስና ወንጀል መቋቋም መሰረታዊ የሆኑ ነጥቦችንም በማመልክት ስለ ሙስና ምንነት ያመለከተ ሲሆን ይሄውም በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሰረት ሙስና ወንጀል የሀሳብ፣ የህግ እና የድርጊት ፍሬ ነገሮችን ደንግጎ ይገኛል፡፡ የሀሳብ ክፍሉን ያየን እንደሆነ በአዋጁ ወንጀሎቹን የሚያቋቁሙ አንቀጾች ወንጀሉ የሚፈጸምበትን አላማ ሲገልጹ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም ሌላውን ሰው ለመጉዳት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ይደነግጋሉ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀጽ 3 ላይ ይሄው ተድንግጎ ይገኛል፡፡ የሙስና ተግባር መነሻው በቅጥርም ይሁን በሹመት የተገኘ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ሀላፊነት ሲሆን ይህም የአዋጁ ዋነኛ ትኩረት ስለመሆኑ ከልዩ ልዩ ድንጋጌዎቹ መረዳት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዋጁ አንቀጽ 4(2) ላይ የሙስና ወንጀልን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትርጉም እናገኛለን። በዚህም “ማንኛውም የመንግስት ወይም መንግስታዊ ድርጅት ሰራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባውን ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጠው ሀላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ ወይም የጠየቀ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት የተሰጠውን ስልጣን ወይም የህዝብ አደራ ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፣ ጥቅም ለራሱ ለማገኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ለመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንደሆነ ወይም በአግባቡ ለተፈጸመ ወይም በአግባቡ ለወደፊቱ ለሚፈጸም የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የመንግስት የልማት ድርጅት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሥራ የማይገባ ጥቅም ለማንኛውም ሰው የሰጠ ወይም ከማንኛውም የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የተቀበለ እንደሆነ በሙስና ወንጀል ፈፃሚነት ተጠያቂ ይሆናል” በማለት ሰፊ የወንጀል ድርጊቶችን አካቷል። ከዚህም እንደምንረዳው በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ለመሆን ፈፃሚው የመንግሰት ሰራተኛ፣ የመንግሰት የልማት ድርጅት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ወይም ተሿሚ መሆን እንዳለበት ነው። ከመንግሰት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛነት ባለፈም ሌሎች ሰዎች ከነዚሁ ሰዎች ጋር በመተባበር በነዚሁ ድርጅቶች ላይ የሙስና ወንጀል ከፈጸሙም የሚጠየቁበት የህግ አግባብ እንዳለ ከአዋጁ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች የምንረዳው ነው፡፡

የሙስና ወንጀል አይነቶች
በአዋጅ 881/2007 በርካታ የሙስና ወንጀል ተግባራት የተካተቱ ሲሆን ለዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ ሲባል የተወሰኑትን ብቻ ለማሳያነት በሚከተለው አግባብ በአጭሩ እንመለከታለን።

በስልጣንን አላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል

የተሰጠን የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ስልጣን አላግባብ መጠቀምን አስመልክቶ ህጉ የሚከተሉትን ዝርዝር ክልከላዎችን በግልጽ አስፍሯል። በዚህም “ማንኛውም የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እዲደርስ ለማድረግ በማሰብ፣
• የተሰጠውን ሹመት፣ ስልጣን ወይም ሀላፊነት በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፣
• በግልፅ ከተሰጠው ስልጣን ወይም ሀላፊነት አሳልፎ የሠራ እንደሆነ ወይም
• ስልጣኑ ወይም ሀላፊነቱ የማይፈቅድለትን ጉዳይ በተለይም ስልጣን ወይም ሀላፊነት ሳይኖረው ወይም ከሥራው ከታገድ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ ወይም ስልጣኑን ወይም ሀላፊነቱን ከተወ በኋላ የሰራበት እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከእንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከአስር ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተመላክቷል። ይህ እንዳለ ሆኖ የተፈጸመው ወንጀል ያደረሰው የጉዳት መጠን፣ የወንጀል ፈፃሚው ሀላፊነት ወይም በድርጊቱ የተገኘው ጥቅም ግምት ውስጥ ገብቶ እንደወንጀሉ ክብደት ቅጣቱ ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት እስራት እና ከአስር ሺ እስከ አንድ መቶ ሺ ብር በሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡

እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ የእስራት ቅጣቱ እስከ ሀያ አምስት ዓመት የገንዘብ መቀጮው ደግሞ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር ሊደርስ ይችላል።

ጉቦ መቀበል (Bribery)

ሌላኛው በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅቶች ሰራተኞች የሚፈጸም የሙስና ወንጀል ጉቦ መቀበል ሲሆን በአዋጅ 881/07 አንቀጽ 10 ላይ ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች ተዘርዝረዋል። በዚህም “ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በሀላፊነቱ ወይም በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ ወይም ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲሰጥ የጠየቀ፣ የተቀበለ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከአርባ ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

እዚህም ላይ የወንጀል ፈፃሚው ሀላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ፣ ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ የእስር ቅጣቱ ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ከፍ ሊል ይችላል። በተጨማሪም የገንዘብ ቅጣቱ እንዲሁ ከአስር ሺ እስከ መቶ ሺ ሊደርስ እንደሚችል ተመላክቷል። እንዲሁም እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ ቅጣቱ እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ አስራት እና እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር መቀጮ ድረስ ከፍ ሊል ይችላል።

የማይገባ ጥቅም መቀበል (Acceptance of Undue advantage)

በአዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀጽ 11 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት ማድረግ የሚገባውን ተግባር ለማከናወን ሲል ይህንኑ ተግባር ከመፈጸሙ በፊት ወይም ከፈጸመ በኋላ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ፣ ያገኘ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከሃያ ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል። እንዲሁም በተፈጸመው ወንጀል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኋላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ የወንጀሉን አፈፃጸም ከባድ አድርጎት እንደሆነ የእስር ቅጣቱ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከአምስት ሺ በማያንስ ስልሳ ሺ ብር በማይልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል።

ሥራን በማይመች ሁኔታ መምራት
በዚህ የሙስና ወንጀል ዘርፍ የሚወድቁት ድርጊቶች ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀጽ 13 ስር እንደተመላከተው ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ስልጣኑን ወይም ሀላፊነቱን ተጠቅሞ
• በንግድ ወይም በሌላ ሥራ፣ በግዢ ወይም በሽያጭ ወይም ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ በማናቸውንም የሥራ ግንኙነት ማንኛውም ጥቅም የወሰደ ወይም ይህንን ጥቅም የሚያገኝበትን ውል የተዋዋለ ወይም ሌላ ዘዴ የፈጠረ
• አግባብ ባለው ባለስልጣን ከተወሰነው በላይ ዋጋ የእቃ ማቅረብ ውል፣ የሥራ መቋረጥ፣ ወይም ማናቸውንም የሥራ ውል የተዋዋለ ወይም በውል ከተመለከተው ዕቃ ወይም አገልግሎት ውጭ የተቀበለ እንደሆነ እንዲሁም
• በሥራው ምክንያት በአደራ የተቀበለውን ወይም ሊጠብቀውና ሊከላከለው የሚገባውን የመንግስት መስሪያ ቤት፣ የልማት ድርጅት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በማናቸውም ዘዴ የፈጸመ እንደሆነ
እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከመቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል። የጥፋተኛው ሀላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ፣ ግዴታው የተጣሰበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ ቅጣቱ ከሰባት አመት እስከ አስራ አምስት አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከአስር ሺ ብር በማያንስ እና ከሁለት መቶ ሺ የማይበልጥ መቀጮ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲሁም እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ ቅጣቱ ከአስር አመት እስከ እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ አስራት እና ከሀያ ሺ ብር እስከ አራት መቶ ሺ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል።

ከባድ እምነት ማጉደል
እምነት መጉደል አስቀድሞ የተሰጠን አምነት አለአግባብ መጠቀምን ያመለክታል፡፡ በዚህም ከባድ እምነት ማጉደል ሲባል በአዋጅ 881/07 አንቀጽ 31 መሰረት ያልተገባ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግሰት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን እቃ ወይም ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ማድረግ፣ ለሌላ ሰው ማድረግ፣ መውሰድ መሰወር፣ ለራሱ ወይ ለሌላ ሰው አገልግሎት ማዋል እና መሰል ድርጊቶችን መፈጸም ሲሆን ከሶስት እስከ ሰባት አመት ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺ ብር እስከ ሀምሳ ሺ ብር መቀጮ እንደሚያስቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣የጥፋተኛው የስልጣን ደረጃ፣የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛነት እየታየ ቅጣቱ ከሰባት እስከ ሀያ አምስት አመት ጽኑ እስራት እና ከሀምሳ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጮ ድረስ ሊቀጣ ይችላል።

ከባድ አታላይነት

በአዋጁ አንቀጽ 32 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ተገቢ ያልሆነን ብልጽግና ለራሱ ማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣ የራሱን ማንነት በመሰወር፣ መግለጽ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቅም፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው በማታለል የተታለለው ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው የንብረት ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገው ከሆነ ከሶስት እስከ አስር አመት በሚድርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በሌላ በኩል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የስልጣን ደረጃ፣ የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛነት እየታየ ቅጣቱ ከአምስት እስከ አስራ አምስት አመት ጽኑ እስራት እና ከአስር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጮ ሊቀጣ ይችላል።

ማጠቃለያ

በጥቅሉ የሙስና ወንጀል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሶስተኛ ሰው ለማስገኘት ታስቦ በመንግስት፣ በመንግስት የልማት ድርጅት እና በህዝባዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሲሆን በመንግስት እና ህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም ወንጀሉን ለመከላከልና ተፈፅሞም ሲገኝ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገጽን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701 ...
LinkedIn
https://www.linkedin.com/.../ministry-of-justice.../about/
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externa

19/08/2025

በአጭር ሥነሥርዓት በሚቀርብባቹ ክስ ላይ አስቀድማቹ ስለምታቀርቡት የመከላከያ ማስፈቀጃ፣
---------------------
በአጭር ሥነ ሥርዓት ታይቶ እንዲወሰን ክስ በሚቀርብበት ጊዜ ተከሳሹ ክሱን ለመከላከል እንዲፈቀድለት በቃለመሐላ አስደግፎ ክሱ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በሚቆጠር አስር ቀን በፊት የክስ መልሱን እንዲያቀርብ ከታዘዘበት ቀነ ቀጠሮ አስቀድሞ የማስፈቀጃ አቤቱታውን በቃለመሐላ አስደግፎ የሚቀርብበት ነው።
ክሱን ለማስተባበል የሚያስችል በቂ መከላከያ እንዳለው ብቻ ከመግለፅ ባለፈ የተከሰሰበት ጉዳይ የማያስጠይቀው ስለመሆኑ የሚያስተባብሉ የሰነድ ማስረጃዋች ካሉ መግለፅ እና ክሱን የሚያስተባብሉ ምክንያቶች ፍ/ቤቱ ሊረዳው በሚችል መልኩ በግልፅ በማስፈቀጃ ላይ ሊቀርቡ ይገባል።ይህም ማስፈቀጃው ወደ ፍሬ ነገር ክርክር ለመግባት በቂ ስለመሆኑ ፍ/ቤቱ በቀላሉ እንዲመዝን የሚረዳ ነው።
በአጭር ሥነ ሥርዓት እንዲታይ በሚቀርብ ክስ አመራር ሥርዓት ተከሳሽ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በፍ/ቤቱ አግኝቶ የተጠየቀውን ገንዘብ ላለመክፈል በቂ ምክንያት መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው ፍ/ቤቱ ከአጭር ሥነ ሥርዓት ወደ መደበኛ የክርክር ሥነ ሥርዓት ውስጥ በመግባት ግራ ቀኙን በአግባቡ በማስረጃ ካከራከረ በኋላ ነው፡፡
ለምሳሌ ፣የፈቃድ ጥያቄ ደረጃ ላይ የቼክ ባሕርይ ሳይሆን መታየት ያለበት ተከሳሽ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ምክንያት ፈቃድ የሚያሰጥ መሆን አለመሆኑን ነው፡፡ የፍሬ ነገር ክርክር ከፈቃድ በኋላ የሚታይ ነው፡፡ሲል የፌደራል ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ. 43315 ያልታተመ፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 284-286 አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።
ለበለጠ👇https://t.me/Taree14

18/08/2025

በሥር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ወይም በመ/ደ የወንጀል ሥልጣኑ በከፍተኛ ፍ/ቤት ዋስትና የተከለከለ የወንጀል ተጠርጣሪ/ተከሳሽ አንድ የይግባኝ ማቅረቢያ መብት አለው—ይግባኝ ሰሚ ችሎት (ከፍተኛ ወይም ጠቅላይ ፍ/ቤት) ክልከላውን ካጸናበት ጉዳዩን ወደ ሰበር ከሚያቀርብ በቀር 2ኛ የይግባኝ ማቅረቢያ መብት የለውም::

ነገር ግን በሥር "የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት" የተፈቀደለት ዋስትና በመርማሪ ወይም በዐ/ሕግ ይግባኝ ባይነት በከፍተኛ ፍ/ቤት ከተሻረበት ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ለጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ የይግባኝ ማቅረቢያ መብት አለው::

[ሰ.መቁ. 146727 (ቅ. 22) የአነጋገር ለውጥ ተደርጎ የቀረበ]👴🏽
telegram......

10/08/2025

"ውልን ባለመፈፀም ስለ ወለድ ህጉ ምን ምን ይላል?
=================================
ከውል አለመፈፀም ጋር ተያይዞ ሕጋዊ ወለድ መሰላት የሚጀምረው ክስ ከቀረበበት ቀን ነው ? ወይስ ቀሪ ከፍያው መፈፀም ከነበረበት ቀን ነው ? የሚለውን ለመወሰን/ለማስላት ማስጠንቀቂያ መስጠት ያለው ጠቀሜታ።
ሰመቁ 13323 ጥቅምት 29 ቀን 2010 የተሰጠ።
በውሉ ባይመለከትም እንኳ ህጋዊ ወለድ አንድ ሰው ግዴታውን ባለመፈፀሙ/ በመዘግየቱ የተነሳ የሚከፍለው ካሳ እኩያ ነው። ጥያቄ ስሌቱ የሚጀምርበት ቀን ነው።
ማስጠንቀቂያ መስጠት ግዴታው ተጠያቂ ከሆነበት ቀን ጀምሮ/ ቀሪ ከፍያውን መፈፀም ከነበረበት ዕለት አንስቶ የሚታሰብ 9% ወለድ እንዲሰላ የሚያደርግ መሆኑ።
አስድቀሞ ማስጠንቀቂያ አለመስጠት ግን ቀሪ ክፍያ ክስ ከቀረበበት ዕለት አንስቶ ህጋዊ ወለድ 9% እንዲሰላ የሚያደርግ ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.133203 በቀን ጥቅምት 29/2010 ዓ/ም በዋለው ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል"
👇👇
https://t.me/taree14

09/08/2025

በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በክረምት በከፊል የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች

የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 38 ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት ከመደበኛ የፍርድ ቤት የስራ ጊዜ ውጭ አስቸኳይ ጉዳዮች እንደሚስተናገዱ ይገልጻል፡፡

በዚህም መሰረት መሰረታዊ የመብት ጥሰት የሚያስከትሉ በባህሪያቸው ጊዜ የማይሰጡ መደበኛ የፍርድ ቤቱ የስራ ጊዜ እስኪጀመር አፋጣኝነታቸው ታይቶ ዉሳኔ ካልተሰጠባቸው የመብት መጣስን ሊያስከትል የሚችሉ እና ሊካስ የማይችል ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን አይቶ መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆኑባቸው ጊዜ ማለትም ከነሃሴ 01 ቀን እስከ መስከረም 30 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ በተረኛ ችሎት በወንጀል እና በፍታብሄር ጉዳዮች መደበኛ የፍርድ ቤት የስራ ጊዜን የማይጠብቁ ጉዳዮች አስቸኳይ ጉዳዮች ሲቀርቡ የሚታዩ ይሆናል በዚሁ መሰረት፡-

በፍታብሄር ከሚቀርቡ ጉዳዮች ፡-

➢ አስቸኳይ የእግድ አቤቱታዎች
➢ የልጅ ቀለብ
➢ አካል ነጻ ለማውጣት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች
➢ እንቅስቃሴን ገዳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች
➢ ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው ላይ የሚያቀርቡት የደመወዝ ክፍያ የሚመለከቱ አፈጻጸም ጉዳዮች
➢ ከግልግል ዳኝነት ትዕዛዞች ጋር ተያይዞ አስቸኳይ የማህተም አገልግሎት ጥያቄዎች (ለእግድ, መጥሪያ ለማድረስ..)
➢ አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጡ መደበኛ የፍርድ ቤቱን የስራ ጊዜ መጠበቅ የማይችሉ በተረኛ ችሎቱ ዳኛ የሚወሰኑ ሌሎች የፍታብሄር ጉዳዮች

በወንጀል ከሚቀርቡ ጉዳዮች፡-

➢ ዋስትና
➢ አመክሮ
➢ አርቲዲ (እስረኛ ያለባቸው የሚቀርቡ የወንጀል መዛግብት )
➢ በተሰብሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎች
➢ ጊዜ ቀጠሮ(አራዳ ምድብ ችሎት)
➢ ለመሰየም የሚቀርብ አቤቱታ
➢ እስረኛ ያለባቸው መዝገቦች
➢ አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጡ መደበኛ የፍርድ ቤቱን የስራ ጊዜ መጠበቅ የማይችሉ በተረኛ ችሎቱ ዳኛ የሚወሰኑ ሌሎች የወንጀል ጉዳዮች

ባጠቃላይ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆንባቸው ጊዜያት መደበኛ የፍርድ ቤቱን የስራ ጊዜ የማይጠብቁ ጊዜ የማይሰጡ እና አጣዳፊ የሆኑ የወንጀል እና የፍታብሄር ጉዳዮች በተረኛ ችሎት የሚስተናገዱ መሆኑን በማረጋገጥ ሁሉም የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ እንዲሁም ተገልጋዩ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲወጣ እናሳውቃለን፡፡
https://t.me/taree14

06/08/2025

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚደረግ የሰራተኞች ቅነሳ እና ውጤቱ

መግቢያ
አንድ ሀገር በኢኮኖሚ እድገት የሚያሳየው ዜጎች በትጋት ሥራቸውን መስራት ሲችሉ እና መብትና ጥቅማቸው በህግ አግባብ መከበር ሲችል ነው። በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማስተዳደር ሁለቱንም አካል ሊገዛ የሚችል የህግ ማዕቀፍ መኖር የግድ ነው።

በመሆኑም መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶችንና ግዴታዎችን ለመጠበቅ እንዲቻል የአሰሪና ሰራተኛ ህግ በኢትዮጵያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በዚህ ጽሁፍም በግል በተቋቋሙ ድርጅቶችና መንግስታዊ በሆኑ የልማት ድርጅቶች ተቀጥረው በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ተፈጻሚነት ባለው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ ተደንግጎ የሚገኘውን የሰራተኞች ቅነሳ እና ውጤቱን በአጭሩ እንመለከታለን።

የሰራተኞች ቅነሳ ምንነት
በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 29 መሰረት የሥራ ቅነሳ የሚባለው የአንድን ድርጅት ድርጅታዊ አቋም ወይም የሥራ እንቅስቃሴ በሚመለከት በሚከተሉት ምክንያቶች የሥራ ውል ሲቋረጥ ነው፡፡ እነዚህም
• ሠራተኞች የተሰማሩባቸው ሥራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና ለዘለቄታው የሚያስቆም የሥራ ውል መቋረጥ የሚያስከትል ሁኔታ ሲከሰት
• በአዋጁ አንቀጽ 18 መሰረት ከአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የድርጅቱን ሥራ በሙሉም ሆነ በከፊል የሚያቋርጥ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት እና የአሠሪው ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ከአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የድርጅቱን ሥራ የሚያቋርጥ ያልታሰበ የገንዘብ ችግር የሥራ ውል መቋረጥና ከሥራ ውል የሚመነጩ መብቶችና ግዴታዎች ለጊዜያዊ የሚታገዱበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አሠሪው በሚያመርታቸው ምርቶች ወይም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተፈላጊነት መቀነስ ምክንያት የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ ወይም ትርፍ እየቀነሰ በመሄዱ የሥራ ውል ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ
• የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል የሚደረግ የሥራ ውል መቋረጥ የሚያስከትል ውሣኔ ሲኖር ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሰራተኞች ቅነሳ ነው ሊያስብል የሚችለው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚቀነሱት ሰራተኞች ቁጥር ከቅነሳ እርምጃው በፊት ባለው አስራ ሁለት ወራት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ከነበሩ ሰራተኞች አማካይ ቁጥር ውስጥ ቢያንስ ከመቶ አሥር የሚያህለውን ወይም የሠራተኞች ቁጥር ከሀያ እስከ ሀምሳ በሆነበት ድርጅት ቢያንስ አምስት ሠራተኞችን የሚመለከት ከአሥር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የሚቆይ የሥራ ውል መቋረጥ ሲከሰት እንደሆነ በአስሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 29 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።

የሠራተኞች ቅነሳ ሂደት
በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት የሰራተኞች ቅነሳ ሲደረግ አሰሪ በራሱ ጊዜ የፈለገውን ሰራተኛ መቀነስ የማይችል ሲሆን ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የሰራተኞች ቅነሳ ሲደረግ በመጀመሪያ አሠሪው ከሠራተኞች ማኅበር ወይም ተወካይ ጋር በመመካከር የሥራ ችሎታ ያላቸውና ከፍተኛ የምርት ውጤት የሚያሳዩ ሠራተኞች በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ያደርጋል ወይም ከማይቀነሱ ሰራተኞች መካከል ይሆናሉ። ነገር ግን በድርጅቱ ውስጥ ተመሳሳይ የሥራ ችሎታ ያላቸውና ተመሳሳይ የምርት ውጤት የሚያመርቱ ሠራተኞች በሚኖሩ ጊዜ የሰራተኞች ቅነሳ የሚደረገው በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ይሆናል፡፡

1. በድርጅቱ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሠራተኞች
2. አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጥገኞች ያሏቸው ሠራተኞች
3. ከተራ ቁጥረ (4) እስከ (7) ከተዘረዘሩት የሠራተኛ ክፍሎች ውጭ የሆኑ ሠራተኞች ቅነሳው በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከታቸው ይሆናል፡፡
4. አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሠራተኞች
5. በድርጅቱ ሳሉ በሥራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች
6. የሠራተኞች ተጠሪዎች
7. ነፍሰጡር ሠራተኞች ወይም ከወለዱ እስከ 4 ወር ድረስ የሆናቸው ሴት ሠራተኞች፡፡

ልዩ ሁኔታ
በልዩ ሁኔታ የኮንስትራክሽን ሥራው ማለትም ሕንጻ፣ መንገድ፣ የባቡር ሐዲድ፣ የባሕር ወደብ፣ የውሃ ግድብ፣ ድልድይ፣ የመሣሪያ ተከላና ሌላም ተመሳሳይ ሥራ የመሥራት የመለወጥ፣ የማስፋፋት፣ የማደስና የመጠገን ሥራ በተከታታይ እያለቀ ሲሂድ የሥራው መጠን በመቀነሱ ምክንያት ተቀጥረው በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ ቅነሳ ሲደረግ አሠሪው በዚህ ከላይ የተመለከቱትን የሠራተኞች ቅነሳ ሥነ ሥርዓት መከተል አይጠበቅበትም፡፡ ነገር ግን ሰራተኞች የተቀጠሩበት ሥራ ከማለቁ በፊት ከሆነ የሰራተኛ ቅነሳ ሲደረግ በአዋጁ ላይ የተገለጸውን ሥነ-ሥርአት መከተል እንዳለበት ከአዋጁ አንቀፅ 30 መረዳት ይቻላል።

የሰራተኞች ቅነሳ ያለው ውጤት
አንድ የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሰራተኛ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 29 መሰረት በሰራተኞች ቅነሳ ምክንያት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ እና ሰራተኛው አግባብነት ባለው የጡረታ ህግ መሰረት የጡረታ አበል ለመቀበል ብቁ ካልሆነ በአዋጁ አንቀፅ 39(1)(ሐ) መሰረት የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው። የሥራ ስንብት ክፍያ መጠንን በተመለከተ ለመጀመሪያው የአንድ ዓመት አገልግሎት የሠራተኛው የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደመወዙ በ30 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በታች አግልግሎ ለተቀነሰ ሰራተኛ ግን እንደአገልግሎት ጊዜው እየተተመነ ተመጣጣኝ ክፍያ ያገኛል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎ በሰራተኛ ቅነሳ ምክንያት የሥራ ውሉ የተቋረጠበት ሠራተኛ ከላይ በተጠቀሰው ክፍያ ላይ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት ከላይ የተጠቀሰው ክፍያ አንድ ሦስተኛ እየታከለ ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ጠቅላላው ክፍያ ከሠራተኛው የ12 ወራት ደመወዝ መብለጥ የለበትም፡፡

በተጨማሪም በሰራተኞች ቅነሳ ምክንያት የሥራ ውሉ ተቋርጦ ከሥራ የተሰናበተ ሰራተኛ ከላያ ከተጠቀሰው የሥራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ የሠራተኛው የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደመወዝ በ60 ተባዝቶ እንደሚከፈለው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 40 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ማጠቃለያ
የሰራተኛ ቅነሳ በአንድ ድርጅት ድርጅታዊ አቋም ወይም የሥራ እንቅስቃሴ ላይ በሚገጥም የሥራ እንቅስቃሴ መዳከም ወይም የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚደረግ የሥራ ውል የማቋረጥ እርምጃ ሲሆን የሰራተኛውንም ሆነ የአሰሪውን ጥቅም በጠበቀ መልኩ እንዲፈፀም ህጉን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡

በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገጽን ይቀላቀሉ

Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701 ...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externa

06/08/2025

‎💩የቅርብ አለቃውን ሰብአዊ ክብርና ሞራል የሚነካ የስድብና ማዋረድ የፈጸመ እና በስራ ቦታ የጠብ አጫሪነትን የፈጠረ ሰራተኛ የሥራ ውሉ ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ የሚችል ስለመሆኑ ፣🎯

‎👨‍⚖️የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 18 በሰበር መዝገብ ቁጥር 110615 ላይ በተመሣሣይ ጉዳይ አስገዳጅነት ያለውን ውሣኔ ሰጥቷል።👨‍💻

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የህግ ክሊኒክ / Legal Clinic posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share