ኢትዮ ህግ አገልግሎቶች /ethio legal services.

ኢትዮ ህግ አገልግሎቶች /ethio legal services. ጠቃሚ የህግ መረጃዎችን በነፃ ያግኙ

23/02/2026
17/02/2026

የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት የሕግ ማዕቀፍ

መግቢያ
መጠለያ የሰው ልጆች ከሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው። በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት የቃል ኪዳን ሰነዶች እንዲሁም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ዜጎች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ ንብረት የማፍራት መብታቸው እውቅና ተሰጥቶታል። እንደመኖሪያ ቤት የመሳሰሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እና ከአንዳንድ የንብረት መብት አይነቶች ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ዜጎች ከውጭ አገር ዜጎች ጋር ሲነፃፀር ላቅ ያለ መብት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ መዋለ ነዋያቸውን፣ እውቀታቸውን እና ሙሉ ጊዜያቸውን በዚች አገር ላይ የሚያፈሱ የውጭ አገር ዜጎች የአገሪቱን ዜጎች መኖሪያ ቤት የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ እንደመኖሪያ ቤት ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን የሚያገኙበትን የሕግ ማዕቀፍ መኖር ጠቃሚ በመሆኑ በአገራችን የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት የሕግ ማዕቀፍ በአዋጅ ቁጥር 1388/2017 ተደንግጓል። በዚህ ጽሑፍ የውጭ አገር ዜጋ ምንነት፣ የውጭ አገር ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ የውጭ አገር ዜጋ መብቶች እንዲሁም የተጣሉ ገደቦች እና ግዴታዎችን በአጭሩ እንዳስሳለን።

የውጭ አገር ዜጋ ማን ነው?
በአዋጅ ቁጥር 1388/2017 አንቀጽ 2(1) መሠረት የውጭ ዜጋ ማለት ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋን (ትውልደ ኢትዮጵያዊ) ሳይጨምር ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ወይም የሌላ አገር ዜግነት ያለው ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት ነው። ከዚሁ የአዋጁ ትርጓሜ እና የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 270/1994 ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሰዎች ምንም እንኳን የሌላ አገር ዜግነት ቢኖራቸውም እንኳን ለዚህ አዋጅ ዓላማ ሲባል እንደውጭ አገር ዜጋ የማይቆጠሩ ሲሆን በተጨማሪም የውጭ ዜጋ የሚለው ሐረግ የተፈጥሮ እና የሕግ ሰዎችን የሚያጠቃልል ነው።

የውጭ አገር ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች
በአዋጁ አንቀፅ 7 መሠረት የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆነው የሚከተሉትን ቅድመ-ሁኔታዎች ሲያሟላ ነው፡-
ስም፣ ዜግነት እና ሌሎች ማንነትን የሚገልፁ ሕጋዊ ሰነዶችን ማቅረብ፣
የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስፈልግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለማሟላት የሚያስችል በቂ አቅም ያለው መሆን፡- ከአዋጁ አንቀጽ 6(1) መረዳት እንደሚቻለው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በዚህ አዋጅ መሠረት የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሊዝ ሙሉ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው አነስተኛ የገንዘብ መጠን ከ150,000 (አንድ መቶ ሀምሳ ሺ) የአሜሪካን ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት የውጭ ባለሀብት ተብሎ የተቆጠረ ማንኛውም ሰው ከፍ ሲል የተገለፀውን አነስተኛ የገንዘብ መጠን መመደብ ሳይጠበቅበት የአንድ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የሚችል ሲሆን ነገር ግን ከአንድ በላይ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የሚችለው ከፍ ሲል የተገለፀውን የሊዙን ሙሉ ዋጋ ጨምሮ በሕጉ የተገለፀውን አነስተኛ የገንዘብ መጠን መመደብ ሲችል ብቻ እንደሆነ ከአዋጁ አንቀጽ 5(2) ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል። ሌላው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን፣ የከተሞች የመኖሪያ ቤቶች አማካይ ዋጋን፣ የውጭ አገር ዜጎች በመኖሪያ ቤቶች ገበያ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እና የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ሌሎች ምክንያቶችን እንደአስፈላጊነቱ መሠረት በማድረግ እንዲሁም የክልሎችን እና ከተሞችን የእድገት እና ልማት ደረጃ ታሳቢ በማድረግ በዝርዝር ጥናት ላይ በመመስረት የአነስተኛ ገንዘብ መጠኑን ከፍ ወይም ዝቅ የሚያደርግ፣ የእያንዳንዱን የሊዝ ቦታ ወይም ቤት ስፋት እንዲሁም የሊዝ ይዞታዎችን ወይም ቤቶችን አጠቃላይ ቁጥር የሚወስን መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 6(3) እና (4) ተደንግጓል።
የወንጀል ታሪክ የሌለው መሆን፡- በአዋጁ መሠረት የመኖሪያ ቤት ባለቤት ከመሆን የሚከለክሉ ወንጀሎች እንዲሁም ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ ከአገር ሰላም፣ ደኅንነት፣ ጸጥታ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ምንጭ ወይም ዝውውር ጋር የሚያያዙ የክልከላ ገደቦች ዝርዝር የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል።
ከአገር ሰላም፣ ደኅንነት፣ ጸጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ የክልከላ ገደብ የሌለበት መሆን፣
ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ፍቃድ ማግኘት፡- ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃድ እንዲሰጠው የሚፈልግ የውጭ አገር ዜጋ የፈቃድ ይሰጠኝ ማመልከቻውን በአካል ወይም ሚኒስቴሩ በሚያደራጀው የድረ-ገጽ ሥርዓት አማካኝነት ለሚኒስቴሩ ማቅረብ አለበት (አንቀጽ 13/2/)፡፡ ሚኒስቴሩም የቀረበለትን ማመልከቻ በመመርመር ማመልከቻው በቀረበ በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ያልተሟሉ ጉዳዮች እንዲቀርቡ ከወሰነም ይህንኑ እንዲፈፅም ለአመልካቹ በ5 የሥራ ቀናት ውስጥ መግለፅ አለበት፡፡ በዚህም መሠረት ተሟልቶ በቀረበ ማመልከቻ ላይ ማመልከቻው ተሟልቶ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል (አንቀጽ 14)፡፡

የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ የውጭ አገር ዜጋ መብቶች
በአዋጁ አንቀጽ 8(1) መሠረት የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት የመኖሪያ ቤት ባለመብት ለሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተሰጡ የንብረት መብቶች ይኖሩታል፡፡ ሆኖም ለግለሰብ ወይም ለቤተሰብ መኖሪያነት የማከራየት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ መኖሪያ ቤቱን ለንግድ ዓላማ ማዋል የተከለከለ ነው። በተጨማሪም ራሱ እና ቤተሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስችል አግባብነት ባለው አካል የሚሰጥ የመኖሪያ ፈቃድ መብት፣ ለራሱ እና ለቤተሰቡ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ መመላለስ እንዲችሉ የሚያደርግ አግባብነት ባለው አካል የሚሰጥ እስከ 5 ዓመት የሚያገለግል የብዙ ጊዜ መመላለሻ ቪዛ የማግኘት መብት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ እና አሠራር መሠረት ከመኖሪያ ቤቱ በሕጋዊ መንገድ የሚያገኘውን የኪራይ ወይም የሽያጭ ገቢ በወቅቱ ተመን በውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ አገር የማስተላለፍ መብት ይኖሩታል። በሌላ በኩል ደግሞ አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት ለኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ቤት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ የመስጠት ኃላፊነት ያለው ተቋም በዚህ አዋጅ መሠረት በሚኒስቴሩ ፈቃድ ለተሰጠው እና ሕጋዊ ውል ለፈፀመ የውጭ አገር ዜጋ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ የመስጠት ግዴታ አለበት (አንቀጽ 17)፡፡

የመኖሪያ ቤት ባለቤት በሚሆን የውጭ አገር ዜጋ ላይ የተጣሉ ገደቦች እና ግዴታዎች
በአዋጁ አንቀጽ 10 ስር የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነትን በተመለከተ የተጣሉ ገደቦች ተዘርዝረዋል። በአዋጁ አንቀጽ 10(1) መሠረት የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የማይችልባቸው ልዩ ቦታዎች እና የድንበር አካባቢዎች የድንበር ላይ ሕዝብን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከግምት በማስገባት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይወሰናል። ሌላኛው ገደብ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በመንግሥት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን የማይችል ሲሆን ነገር ግን ይህ ገደብ የፌደራል ወይም የክልል መንግሥት በግል እና መንግሥት አጋርነት ወይም በተመሳሳይ የቤቶች ልማት ማእቀፍ፣ ወይም ለትርፍ ዓላማ ገንብቶ ለሽያጭ የሚያቀርባቸውን ቤቶች አያካትትም (አንቀጽ 10(2) እና(3))። ሌላው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ አይችልም (አንቀጽ 10/4/)። በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በማናቸውም ሁኔታ በአንድ ጊዜ የሚኖረው የመኖሪያ ቤት ቁጥር አንድ ሲሆን ሚኒስቴሩ ከአገር ጥቅም አንፃር አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ይህን ቁጥር በመመሪያ ማሻሻል ይችላል (አንቀጽ 6/2/)፡፡

የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ የውጭ አገር ዜጋ ግዴታዎችን በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 9(1) መሠረት የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሆነ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ አግባብነት ባላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች በኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ የተጣሉ ግዴታዎች ይኖሩበታል፡፡ በተጨማሪም ባለመብት ለመሆን የሚያስፈልግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ማሟላት፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስፈልጉ የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ ወይም የመጀመሪያው ዓመት ተያያዥ የመንግሥታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ገንዘብ እኩል ምንዛሪ ብቻ መክፈል፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በሊዝ መሬት የሚያገኝ ከሆነ አጠቃላይ የሊዝ ዋጋውን በአንድ ጊዜ የመክፈል ግዴታዎች አሉበት (አንቀጽ 9/2/)፡፡
ከፍ ሲል የተጠቀሱት መብትና ግዴታዎች እንዲሁም ገደቦች ቢኖሩም ከመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተለየ መብትና ግዴታን ከሚያስቀምጡ አገራት ለሚመጡ የውጭ ዜጎች በእንካ-ለ እንካ (Reciprocity) መርህ መሠረት በአዋጁ ላይ ከተመለከተው የተለየ መብት የሚሰጥ ወይም ግዴታን የሚያስቀምጥ አሠራር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ሊወሰን እንደሚችል በአንቀጽ 11 ስር ተደንግጓል፡፡
መተጨማሪም አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት በመኖሪያ ቤት ላይ የሚኖር መብት ቀሪ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች እና አሠራሮች እንደአግባብነቱ በዚህ አዋጅ መሠረት የውጭ አገር ዜጋ በመኖሪያ ቤት ላይ በሚኖረው የባለቤትነት መብት ላይም ተፈፃሚ ይሆናሉ (አንቀጽ 12)፡፡

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ አዋጁ የውጭ አገር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የቤት ባላቤት የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ረገድ ከሚኖረው ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ባሻገር የውጭ አገር ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ሕገወጥ መንገድ እንዳይከተሉ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

12/02/2026
12/02/2026

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዐት በኢትዮጲያ

መግቢያ
የአንዲት አገር ዜጎች ከልደት እስከ ህልፈተ-ህይወት የሚከሰቱ ወሳኝ ኩነቶች ማለትም እንደ ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ያሉ ክስተቶች የአንድን አገር ቀጣይ የልማት አቅጣጫ የመወሰን አቅም አላቸው፡፡ እነዚህን ክስተቶች በቋሚነትና በአስገዳጅነት መመዝገብ ለሕግ፣ ለአስተዳደርና ለስታቲስቲክስ ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረውን የሕግ ማቀፍ በማሻሻል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1370/2017 አፅድቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ ይህ ጽሁፍ በአዋጁ የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦችን በአጭሩ የሚዳስስ ይሆናል፡፡

የወሳኝ ኩነት ምንነት
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ወሳኝ ኩነት ሲባል በዋናነት የሚታወቁት ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አዲሱ አዋጅ 1370/2017 አድማሱን በማስፋት ከአራቱ መሠረታዊ ኩነቶች በተጨማሪ ጉዲፈቻ፣ ልጅነትን መቀበል እና አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅ እንደ ወሳኝ ኩነት እንደሚቆጠሩ አንቀጽ2(2) ደንግጓል፡፡ ሲቪል ምዝገባም እነዚህኑ ህብረተሰቡን የሚመለከቱ ወሳኝ ኩነቶች እና ባህሪያቸው በቋሚነት፣ በቀጣይነት፣ በአስገዳጅነት፣ ሁሉንአፍነትና ሚስጥራሚነትን በጠበቀ ሁኔታ መመዝገብ ነው፡፡

የሲቪል ምዝገባ መርህ
የሲቪል ምዝገባ ሥርአት የራሱ መርሆዎች እንዳሉት በአዋጁ አንቀጽ 17 ተመልክቷ፡፡ ይኸውም
ማንኛውም ምዝገባ ለሕጋዊ፣ ለአስተዳደራዊና ለስታትስቲክስ ዓላማዎች አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን መያዝ
ምዝገባው በአስመዝጋቢው መደበኛ የመኖሪያ ቦታ ወይም በተከሰተበት ቦታ መመዝገብ
ማንኛውም ምዝገባ ከአንድ ጊዜ በላይ ያለመመዝገብ
ማንኛውም አስመዝጋቢ ለማስመዝገብ በክብር መዝገብ ሹም ፊት በአካል መቅረብ
የክብር መዝገብ ሹሙ መረጃዎችን በክብር መዝገብ ቅጽ ካሰፈረ በኋላ ስለተመዘገበው መረጃ ትክክለኛነት አስመዝጋቢው እንዲያረጋግጥ የማድረግ እና
ከአቅም በላይ በሆነ ችግር የሲቪል መዝጋቢው ምዝገባውን ማከናወን ባልቻለ ጊዜ አገልግሎቱ በሚያወጣው የምዝገባው ጊዜ ምዝገባው መከናወን ናቸው፡፡

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቦታ እና ጊዜ
• በአዋጁ አንቀጽ 28 መሠረት የልደት ምዝገባ በወላጆች፣ በሞግዚት፣ በአሳዳሪ መደበኛ መኖሪያ ቦታ በሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽ/ቤት ወይም ልደቱ በተከሰተበት ቦታ በሚገኝ ሲቪል ምዝገባ ጽ/ቤት ወይም የጤና ተቋም የሚከናወን ሲሆን፤ የጉዲፈቻ፣ ልጅነትን መቀበል እና አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅ ምዝገባ ቦታ ስምምነቱን ባፀደቀው ወይም ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት አቅራቢያ በሚገኝ ሲቪል ምዝገባ ጽ/ቤት ወይም በአስመዝጋቢዎቹ መደበኛ መኖሪያ ቦታ በሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽ/ት ቤት ሊሆን እንደሚገባው ተከታዩ አንቀጽ 29 በግልጽ ይደነግጋል፡፡
• የጋብቻ ምዝገባ ቦታን በተመለከተ ጋብቻው በተፈፀመበት ቦታ፣ ከተጋቢዎቹ አንዱ ይኖርበት በነበረ መደበኛ መኖሪያ ቦታ ወይም ከተጋቢዎቹ የአንደኛው ወላጆች ወይም አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት በተደነገገውን የዝምድና ደረጃ መሠረት በቅርብ ዘመዶች መደበኛ መኖሪያ ቦታ በሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽ/ት ቤት ምዝገባው መደረግ እንዳለበት የአዋጁ አንቀፅ 33 ይገልፃል፡፡
• የፍቺ ምዝገባን በተመለከተ በአዋጁ አንቀፅ 37 መሠረት ፍቺው በተፈፀመበት አቅራቢያ በሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽ/ቤት ወይም በተፋቺዎች ወይም በተፋቺው መደበኛ መኖሪያ ቦታ በሚገኝ የሲቪል ምዝገባ ጽ/ ቤት ሊሆን እንደሚገባው ይደነግጋል፡፡
• የሞት ምዝገባን በተመለከት ምዝገባ የሚከናወነው በሟቹ መደበኛ መኖሪያ ቦታ ወይም ሞቱ በተከሰተበት ቦታ አቅራቢ በሚገኝ የሲቪል ምዝጋባ ጽ/ቤትወይም የጤና ተቋም ሲሆን ሟች ማንነቱ የማይታወቅ የሆነ እንደሆነ ደግሞ አስክሬኑ በተገኘበት ቦታ አቅራቢ በሚገኝ ሲቪል ምዝገባ ጽ/ቤት እንደሚሆን በአዋጁ አንጽ 44 ተመልክቷል፡፡
ሌላው የምዘገባ ጊዜ ሲሆን መረጃዎች በጊዜው ሳይመዘገቡ ጊዜ በገፋ ቁጥር የሕጋዊነት ዋጋቸው እና የመረጃ ጥራታቸው ስለሚቀንስ ሕጉ በአንቀጽ 18 አስገዳጅ የጊዜ ገደቦችን አስቀምጧል፡፡ በድንጋጌው መሠረትም ማንኛውም የልደት ክስተት ህፃኑ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ባሉት 90 ቀናት ውስጥ መመዝገብ ያለበት ሲሆን የሞት ኩነት ደግሞ በተከሰተ በ50 ቀናት ውስጥ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረግ አለበት፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያሉት እንደ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሌሎች ኩነቶች ክስተቱ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ መመዝገብ እንዳለባቸው ሕጉ ያዛል፡፡ ይህ የጊዜ ገደብ የተቀመጠው የዜጎችን መብት በፍጥነት ለማረጋገጥ እና የመረጃ ጥራትን ለመጠበቅ ነው፡፡

የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ፋይዳ
ወሳኝ ኩነቶችን ማስመዝገብ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ምዝገባ የሕጋዊ ማንነት መሠረት ነው፡፡ የልደት ማስረጃ የሌለው ህፃን ትምህርት ለመማር፣ የህክምና አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የጉልበት ብዝበዛ ለመጠበቅ ይቸገራል፡፡ በጋብቻ እና በሞት ጊዜም ቢሆን ሕጋዊ የምስክር ወረቀት መያዝ የንብረት ውርስን በሕጋዊ መንገድ ለመፈፀም፣ የኢንሹራንስ እና የጡረታ መብቶችን ለማከበር ብቸኛው ዋስትና ነው፡፡ በአገር ደረጃም ቢሆን መንግሥት ትክክለኛ የህዝብ ቁጥርን እና ስብጥርን አውቆ ፍትሃዊ የሆነ የልማት እቅድ ለማውጣት፣ ትምህርት ቤቶችን እና ጤና ጣቢያዎችን የት መገንባት እንዳለበት ለመወሰን የሚችለው ዜጎች ኩነቶችን በአግባቡ ሲያስመዝግቡ ብቻ ነው፡፡

ያለመመዝገብ ሕጋዊ ውጤት
በአዋጁ አንቀጽ 18(2) ስር እንደተመለከተው የሲቪል ምዝገባ በድንጋጌው በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተፈፀመ እንደሆነ አስመዝጋቢው የዘገየበትን በቂ ምክንያት በማስረጃ በማስደግፎ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል ፡፡

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1370/2017 ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ለመገንባት የተዘረጋ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ወሳኝ ኩነቶችን መመዝገብ ለአገር ልማት ግብአት ከመሆን ባሻገር ለእያንዳንዱ ዜጋ የሕግ ጥበቃ እና የማኅበራዊ አገልግሎት ጠቃሚ ነው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ በህይወቱ የሚከሰቱ ለውጦችን በወቅቱ በማስመዝገብ ለራሱ መብት መከበር እና ለአገሩ እድገት የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይረክቶሬት የተዘጋጀ

የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_external

09/02/2026

በፍቺ የፈረሰ ጋብቻ፣ ጥንዶቹ እንደገና አብረው ስለኖሩ ወይም "እንደ ባልና ሚስት" ስለታዩ ብቻ በሕግ ፊት ጋብቻ ተመሠረተ ሊባል አይችልም ጋብቻ የለም; የሚጠየቅ የንብረት ክፍፍል ዳኝነት ተቀባይነት የለውም
➨ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም
➨በመዝገብ ቁጥር 804/2016
ጠበቃ አደም ሰይድ ከማል
🔺🔺🔺🔺🔺🔺🔺🔺🔺🔺
✅ የጉዳዩ መነሻ (Background)
​ተከራካሪዎች፦ አመልካች አቶ ዘመዴ ጀማነህ እና ተጠሪ ወ/ሮ አልማዝ አሰፋ።
​የክርክሩ ምክንያት፦ ጥንዶቹ በ1957 ዓ.ም ተጋብተው በ2001 ዓ.ም በፍርድ ቤት በይፋ ተፋተዋል። ሆኖም ከፍቺው በኋላ በ2004 ዓ.ም "አብረን እንኑር" በሚል የእርቅ ስምምነት አድርገው አብረው መኖር ቀጥለዋል።
​መሠረታዊ ጥያቄ፦ ተጠሪ (ወ/ሮ አልማዝ) ይህ "የእርቅ ስምምነት" እና ተከታዩ አብሮ መኖር እንደ አዲስ ጋብቻ ተቆጥሮ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግላት ጠይቃለች።
​✅ የታችኛው ፍርድ ቤቶች ውሳኔ
​የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፦ ቀደም ሲል በነበረው የሰበር ውሳኔ (መዝገብ ቁጥር 23021) ላይ በመመስረት፣ "ጥንዶች ተፋተው እንደገና አብረው መኖር ከጀመሩ ጋብቻው እንደቀጠለ ይቆጠራል" በሚል ድምዳሜ ወ/ሮ አልማዝ የንብረት መብት አላት ሲል ወስኖ ነበር።
​አቶ ዘመዴ ቅሬታ፦ ይህ ውሳኔ የሕገ-መንግሥቱን የንብረት መብትና የሕግ አውጭውን ሥልጣን ይጋፋል በማለት ለሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ አቅርበዋል።
​✅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትንተና
​ምክር ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አስቀምጧል፦
➨​የጋብቻ መመዘኛ፦ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ መሠረት ጋብቻ የሚፈጸመው በሦስት መንገዶች (በሲቪል፣ በሃይማኖት ወይም በባህል) ብቻ ነው። እነዚህም የራሳቸው የሆነ የሥነ-ሥርዓት መስፈርት አላቸው።
➨​አብሮ መኖርና ጋብቻ፦ ጥንዶች አብረው ስለኖሩ ወይም "እንደ ባልና ሚስት" ስለታዩ ብቻ በሕግ ፊት ጋብቻ ተመሠረተ ሊባል አይችልም።
➨​የሕግ አውጭነት ሥልጣን፦ ፍርድ ቤቶች "አብሮ መኖር እንደ ጋብቻ ይቆጠራል" የሚል ትርጉም መስጠታቸው፣ በሕጉ ላይ የሌለ አዲስ የጋብቻ ዓይነት መፍጠር ነው። ይህ ደግሞ የሕግ አውጭውን (የፓርላማውን) ሥልጣን መጋፋት ነው።
​የውሳኔው ተፈጻሚነት፦ ቀደም ሲል በፍርድ ቤት የፈረሰ ጋብቻ፣ እንደገና በሕግ መሠረት የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ሳይፈጸም "እንደቀጠለ" ተደርጎ መወሰዱ ስህተት መሆኑን ገልጿል።
​✅የመጨረሻ ውሳኔ (Order)
​የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የሚከተለውን ወስኗል፦
​የሰበር ውሳኔው ውድቅ ሆኗል፦ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት "ጋብቻው ሳይቋረጥ ቀጥሏል" በማለት የሰጠው ውሳኔ የሕገ-መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገውና ስህተት ሆኖ ተገኝቷል።
​ጋብቻው ፈርሷል፦ በ2001 ዓ.ም በፍርድ ቤት የተሰጠው የፍቺ ውሳኔ የጸና ነው። ከዚያ በኋላ የተደረገው አብሮ መኖር በሕግ ፊት "ጋብቻ" ተብሎ ሊታወቅ አይችልም።
ጠበቃ አደም ሰይድ ከማል

​ንብረትን በተመለከተ፦ ጥንዶቹ በ2001 ዓ.ም ሲፋቱ በነበረው የንብረት ክፍፍል ውሳኔ መሠረት ብቻ ይፈጸማል። ከፍቺው በኋላ ያለው አብሮ መኖር አዲስ የጋብቻ ንብረት መብት አያስገኝም።
​ማሳሰቢያ፦ ይህ ውሳኔ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ "በሁኔታዎች የሚመሠረት ጋብቻ" (Constructive Marriage) በፍቺ ለፈረሰ ጋብቻ እንደማያገለግል በግልጽ አስቀምጧል።

06/02/2026

"እየሞከርኩ ነው" ጠበቃ ሙሉጌታ በላይ
=========================
ጥቅም ባጠቆረውና እውነት በሐሰት መጋረጃ በተጋረደበት በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብቸኛ የብርሃን ነጥብ ቆሜያለሁ። ስሜ "ፍትህ" ነው፤ ሙያዬ ደግሞ የመከራ ቀን ጋሻ።

በየችሎቱ ደጃፍ መብታቸውን ባለማወቅ የሰለሉ ዓይኖችን ስመለከት የሕግን አንቀጽ እንደ ሰይፍ መዝዤ በበደል ላይ ለመዝመት እየሞከርኩ ነው።

ዓለም በጉልበት ልታዘመኝ ስትቃጣ እኔ ግን ሚዛኑን ቀጥ አድርጌ ለመያዝ በጽናት እየሞከርኩ ነው።

ተለቁ ብዬ አላንስም ፊቴ የቆሙት ግዙፍ ተቋማት ቢሆኑም እኔ ከሰው ሁሉ በላይ መሆኔን አውቃለሁና በትዕቢታቸው ፊት እንደ ዓለት ለመቆም እየሞከርኩኝ ነው ።

አበጡ ብዬ አልጉበጥም በኃብት ያበጡ ወገኖች እኔን በብር ሊገዙኝ ሲሉ እኔ ግን የድሃውን እንባ ላለመሸጥ ሕሊናዬን በጽናት ለማጠር እየሞከረኩ ነው።

ባለማወቅ ጨለማ ውስጥ ለጠፉት ብርሃን ለመሆን
በመብት ረገጣ ለደከሙት ምርኩዝ ለመሆን
እየሞከርኩ ነው... አዎ እየሞከርኩ ነው።

እኔን በሳንቲም ለምትመዝኑና ሕግን ለተንኮል ለምትተረጉሙ "ተኩላዎች" መልእክቴ ግልጽ ነው።

እናንተ ሥልጣንን እንደ ጅራፍ ብትጠቀሙም፣ በገንዘባችሁ ከዳኛ ጋር ብትሸቅጡም ህሊናችሁ ቆሹሿልና ለህሊና ፍርድ ትቻችሁ እየሞከርኩ ነው።

እናንተ ጨለማን ስትጋርዱ እኔ ሻማ ሆኜ ለመብራት እየሞከርኩኝ ነው።

በመጨረሻም የሚሸነፈው የእናንተ ክፋት እንጂ የእኔ ጽናት አይደለም። እኔ የዘገየሁ እመስል ይሆናል እንጂ አልቀርም። እናንተን መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን ዓለሙን መለወጥ እስክችል ድረስ በጽናት እየሞከርኝ ነው።

የተሰበረው ሚዛን ዳግም እስኪስተካከል፣ እውነት ከሐሰት በላይ እስክትወጣ ድረስ መሞከር አልተውም!
የታሰሩት ካቴናዎች እስኪፈቱ፣ የታፈነው ድምፅ እስኪሰማ ድረስ መሞከር አልተውም!
•የተቀደዱት የሕግ መጻሕፍት እንደ አዲስ እስኪታተሙ፣ ሕግ ለሁሉም እኩል እስኪሆን ድረስ መሞከር አልተውም!
በግብዝነትና በሙስና የጨለመው ዓለም በብርሃኔ እስኪበራ ድረስ መሞከር አልተውም!

05/02/2026

በጋብቻ ውስጥ የሚገኙ የግል ንብረቶች
የተሻሻለው የቤተሰብ አዋጅ ቁጥር 213/1992

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው 0929101037,0983337690

1. የዚህች ጽሁፍ አጭር ይዘት

በኢትዮጵያ ጋብቻ ስረአት ሶስት አይነት ሲሆኑ እነዚህም በሀይማኖት፣በማዘጋጃ፣ በባህል ናቸው። ሆኖም እነዚህ የጋብቻ ስረአቶች በመንግስት ተቋም ስልጣን ያለው ተቋም በመሄድ መመዝገብ አለባቸው።የጋብቻ ሰርተፍኬትም ለተጋቢዎች የሚሰጣቸው ይሆናል። ይሄንን አልን እንጂ የዚህ ጹሁፍ ይዘት አላማ በጋብቻ ውስጥ የሚገኙ የተጋቢዎች የግል ንብረቶች በተመለከተ "ህጉ ምን ይላል?" የሚለውን ወደ እናንተ ለማውሳት ነው።

2. በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መሠረት የተጋቢዎች የግል ንብረቶች ምን ምን ናቸው?

ይህንን ለማወቅ የፌደራል የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 57 ማየት አስፈላጊ ነው። የግል ንብረት ለማወቅ የጋራ ንብረት የሚባሉትን መለየቱ አስፈላጊ በመሆኑ እነዚህን በአጭሩ እናንሳ። በፌደራል የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መሠረት ተጋቢዎች አብረው እያሉ በጉልበታቸው፣በእውቀታቸው በማናቸውም ህጋዊ ምክንያት ያፈርዋቸው ንብረቶች የጋራቸው እንደሆነ ይቆጠራሉ። በተጨማሪም አብረው እያሉ በአንዱ የግል ንብረት ላይ የተጨመረ የታደሰ ንብረት ወይም የንብረት አካል እንኳን የጋራ እንደሆነ ይቆጠራል።

የግል ንብረቶች በባህሪያቸው የአንድኛው ተጋቢ ብቻ የሆኑ ናቸው። እነዚህን እየጠቀስን እናንሳ።

2.1 ከጋብቻ በፊት የአንዱ ተጋቢ ብቻ ከሆነ(57)

ንብረቱ ከጋብቻ በፊት የአንዱ ተጋቢ ከሆነ በጋብቻ ውስጥም የተጋቢው ብቻ ሆኖ ይቀጥላል። ነገር ግን በጋብቻ ውል ውስጥ ይህን የግል ንብረት የጋራችን ነው በማለት የጋራ ለማድረግ መስማማት ይቻላል።ይህ በተጋቢዎች ነጻ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ነው።(42)

2.2 በውርስ የተገኘ ንብረት ከሆነ

አንድኛው ወይም እያንዳንዳቸው በውርስ በኢትዮጵያ የውርስ ህግ መሠረት በጋብቻ ውስጥ እንኳን ቢሆን ያገኙት እንደሆነ የዚሁ ወራሽ ተጋቢ እንጂ የጋራ ንብረት አይሆንም።(57)

2.3 በስጦታ የተገኘ እንደሆነ

በስጦታ አንድኛው ተጋቢ ያገኘ እንደሆነ በጋብቻ ውስጥ እያሉ ቢገኝ እንኳን ስጣታ ያገኘው የግል ንብረት ይሆናል። (57)
3. አንድኛው ተጋቢ የግል ንብረቱን ሽጦ ሌላ ንብረት ከገዛ በኋላ የጋራ ይሆናል ወይንስ የግል ይሆናል? (58)

አንድኛው ተጋቢ የግል ንብረቱን ሽጦ ሌላ ንብረት ሲገዛ በል ሀብት የተገኘ፣ የራሱ መሆኑን በፍርድ ቤት ማስመዝገብ አለበት ይህንን ሳያደርግ ቢገዛ ቢለውጥ የግብይት ንብረቱ የጋራ ንብረት ይሆናል። የዚህ የግል ንብረት ተሽጦ የተገኘ በባንክ የሚገኝ ገንዘብ ግን የግል ሆኖ ይቆያል።

4. በግል ተጋቢ ቤት ላይ የተደረገ የጋራ እድሳት ውጤት ምን ይሆናል?

ቤቱ እና ይዞታው ቀድሞ የግል የአንድኛው ተጋቢ ሆኖ ነገር ግን በጋራ ወጪ ቤቱን ቢያድሱት በግቢው ሌሎች ቤቶች ቢሰሩ ይዞታው እና ቤቱ የቀድሞው ተጋቢ የግል ሲሆን የእድሳት ወጪ ፣ ተጨማሪ ቤቶች በተመለከተ የጋራ ናቸው።

5. የጋብቻ ውልን ማሻሻል ይቻላል?

የጋብቻ ውል እጅግ ቢዘገይ ጋብቻ ሲፈጸም ወይም ከመፈጸሙ በፊት የሚደረግ ሲሆን በአብዛኛው የጋብቻ የንበረት አስተዳደር በተመለከተ የሚይዝ ነው (42)። ይህንን ውል ማሻሻል የሚቻል ሲሆን ተጋቢዎች እንደ ስምምነታቸው ወይም እንደ ፍላጎታቸው የጋብቻ ውላቸውን በሂደት በጋብቻ ውስጥ እያሉ ማሻሻል ይችላሉ(47)።

6. የህግ ምክር

ተጋቢዎች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት የግል ንበረታቸውን በጋብቻ ውስጥ እንዴት እንደሚያስተዳድሩ ቀድመው ማወቅ ይኖርባቸዋል።
https://www.facebook.com

04/02/2026
04/02/2026
04/02/2026

Address

አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ኢትዮ ህግ አገልግሎቶች /ethio legal services. posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to ኢትዮ ህግ አገልግሎቶች /ethio legal services.:

Share

Category