01/12/2021
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በንግድ ሕጉ
(በላይሁን ይርጋ)
1. መግቢያ
በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 መሰረት የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሕግ መሰረታዊ ለውጥ ካመጣባቸው የህጉ ክፍል መካከል መፀሀፍ ሁለት የንግድ ማህበርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል፡፡ በበፊቱ የንግድ ሕግ ውስጥ ከተካተቱት ስድስት የንግድ ማህበራት አይነቶች መካከል ተራ የሽርክና ማኅብር በመባል የሚታወቀው እና ከአንጽፅ 227 እስከ 270 ባሉት ድንጋጌዎች ሥር የተመለከተው የንግድ ማኅበር የሚቋቋምበት ዋና ዓላማ የንግድ ሥራ ለመሥራት አለመሆኑ በግልፅ የተደነገገ ሲሆን በተግባርም በሥራ ላይ ውሎ የማይገኝ በመሆኑ ከሕጉ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን በምትኩ ሁለት አዳዲስ የንግድ ማኅበር ዓይነቶችን አካቶ በጠቅላላ ሰባት የንግድ ማህበር አይነቶችን ይዞ መጥቷል፡፡
በሕጉ እንደ አዲስ ከተካተቱት ሁለት የንግድ ማህበር አይነቶች መካከል አንዱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር /Limited Liability Partnership LLP/ በመባል የሚታወቀው አንዱ ሲሆን ይህ ዓይነቱ የሽርክና ማኅበር ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የሙያ ለሙያ ደጋፊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያቋቁሙት የማኅበር አይነት ነው ። ሌላው በተቀረው ዓለም እየተለመደ የመጣው አዲስ አደረጃጀት ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት (One Man Company) ሲሆን በዚች አነስተኛ ፅሁፍ ስለዚሀ ማህበር ባህርያትና መሰል ጉዳዮች ዘርዘር አድርገነ ለማየት እንሞክራለን።
2. የባለ አንድ አባል ኃለፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር አስፈላጊነት
በአገራችን የንግድ ሕግ መሠረት የንግድ ማህበር ወይም ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የአባላት ቁጥር ቢያንስ ሁለት መሆን ይኖርበታል ፡፡ ነገር ግን ይህ መስፈርት የንግድ ማኅበራት ከሚቋቋሙበት ዓላማ፤ አሁን አገሪቱ ከምትከተለው ነጻ የገበያ ሥርዓትና በወቅቱ ተቀባይት እያገኘ ከመጣው ዓለም አቀፍ የንግድ አሠራር ልምድ ጋር በሚከተሉት ምክንያቶች የሚጣጣም አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ባለሀብቶች በንግድ ማኅበር ተደራጅተው እንዲሠሩ የተደረገበት ዋናው ዓላማ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ በሚለው ብሂል የንግድ ሥራው የሚያስፈልገውን አዋጭ የንግድ ሐሳብና ካፒታል በጋራ አመንጭተው ወደ ንግድ ሥራ ቢገቡ ውጤታማ ይሆናሉ በሚል እሳቤ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ በወጣበት በ1952 ዓ.ም በሀገሪቱ ያሉ ባለሀብቶች ያላቸው የካፒታል መጠን ብቻቸውን ማህበር ለመመስረት የሚያስችላቸው አይደለም የሚል አስተሳሰብ ስለነበረና በተጨባጭም በወቅቱ የነበረው የካሽ ገንዘብ እንቅስቃሴ አነስተኛ ስለነበረ ህጉ ይህ ታሳቢ አድርጎ እንደወጣ መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይህ አስተሳብ ሕጉ በወጣበት ዘመን ተቀባይነት ያለው ቢሆንም በቂ የንግድ ሐሳብና ካፒታል ያላቸው ባለሀብቶች ከፍላጎታቸው ውጭ ከሌሎች ጋር የግድ እንዲጣመሩ ማስገደዱ ባለሀብቶች በነጻነት በመረጡት የንግድ መስክ ተሠማርተው ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን እንዳይጠቅሙ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡
አሁን በተግባር እየታየ እንዳለው የሕጉን አነስተኛ የአባላት ቁጥር ግዴታ ለማሟላት እና ሌላ ሰው በሚያቋቁመው የንግድ ኩባንያ ውስጥ ላለማስገባት ሲሉ ምንም የንግድ ሐሳብም ሆነ የገንዘብ አስተዋጽኦ ያላደረጉ የቤተሰብ አባላትንና ሌሎች የቅርብ ሰዎቻቸውን አባል አያደረጉ ማህበር ይመሰርታሉ፡፡ ይህም በአንድ በኩል ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸውን ሰዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች የተመሠረቱ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች አባላት ቁጥር በተለያየ ምክንያት ለምሳሌ ያህል በባለትዳሮች፣ በቤተ ዘመዳሞችና በጓኛሞች ወዘተ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር አንዱ አባል ከማኅበሩ የሚወጣበት ሁኔታ ሲከሰት ኩባንያው ውጤታማ ቢሆንም በህጉ በአንድ አባል መቀጠል ስለማይቻል እንዲፈርስ ይደረጋል ፡፡ ግለሰብ ባለሀብቶች ከፍላጎታቸው ውጭ ከሌሎች ሰዎች ጋር የንግድ ማኅበር እንዲያቋቁሙ መገደዳቸው የሚያስከትለው ሌላው ችግር የንግድ ማኅበር ከሌላ ሰው ጋር ላለማቋቋም ሲሉ ወደ ግል ንግድ እንዲያተኩሩ አድርጓል፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በአገራችን ከኩባንያዎች ቁጥር ይልቅ የግለሰብ ንግድ ከፍተኛውን ቁጥርና የገበያ ድርሻ ይዞ ይገኛል ፡፡ ይህ አሠራር የተለያዩ ችግሮችን ማስከተሉ ይነገራል፡፡ አንደኛ ለንግድ ሥራ የሚመድቡትን ሀብት ከግል ንብረታቸው ነጥለው በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ለማስተዳደር የሚኖራቸውን ዕድል የሚዘጋ ነው፡፡ ሁለተኛው በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አቋቁመው ከኩባንያው በላይ የሚመጣ ዕዳን ወደ ግል ሀብታቸው እንዳይተላለፍ የሚገድበውን ዕድል ያሳጣል፣ በዚህም የተነሣ በዕዳ እንዳይጠየቁ ንብረታቸውን የሚያሸሹበት ሁኔታ ስለሚፈጥር ሕገ ወጥነትንን ያበረታታል፡፡
ሌላው ችግር በግላቸው ኩባንያ መሥርተው ከጊዜ በኋላ የኩባንያውን ዕድገትና ውጤት እያዩ ሌሎች ግለሰቦችን በመሳብ ተጨማሪ ካፒታል እንዳያሰባስቡና የንግዱን ሥራ ለማስፋፋት ጥረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም በአገራችን የንግድ ኩባንያዎች እንዳይስፋፉ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከመንግሥት ቁጥጥር አኳያም ሲታይ ከኃላፊነታቸው የተወሰኑ የግል ኩባንያዎች በተለየ ሁኔታ የግለሰብ ንግድ የተደራጀ አመራርና የኦዲት እንዲሁም ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ስላልተጣለባቸው አሠራራቸው ሕግን የተከተለ ለመሆኑ መንግሥት ለማረጋገጥ የሚያስችልበት ሁኔታ በጣም የጠበበ ነው፡፡
አንድ ሰው ብቻውን ኩባንያ እንዲያቋቋም መፍቀዱ የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በአንድ ሰው ብቻ ኩባንያ እንዲያቋቋም መፈቀዱ ወደፊት የሚቋቋሙትን ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ተቋቁመው በተለያዩ ምንያቶች የአባላቱ ቁጥር ወደ አንድ ዝቅ በማለቱ ብቻ በሕጉ አንቀጽ 511 መሠረት እንዲፈርሱ የሚደረጉትን ከመፍረስ ይታደጋቸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለሀብቶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ለማቋቋም የሕጉን ግዴታ ለማሟላት ሲሉ ብቻ ከማይፈልጉት ባለሀብት ጋር የሚጣመሩበትን ዕድል ይቀንሳል፡፡ ሦስተኛ ባላሀብቶች ከግለሰብ ንግድ ይልቅ ኩባንያ እንዲያቋቁሙ ስለሚያደርግ የኩባንያዎች ዕድገት በአገሪቱ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል፡፡ አራተኛ ባለሀቶች ኩባያዎችን ሲያቋቁሙ መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ አዲሱ የንግድ ሕግ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንደ አንድ የንግድ ማህር አይነት እውቅና የሰጠበት ሁኔታ አለ፡፡
3. የማህበሩ ምንነት እና የተጠያቂነት ስርዓት
ባለ አንድ አባል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለት አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት የተቋቋመ የንግድ ማኅበር ነው ሲሆን ማኅበሩ ከአባሉ የተለየና የተነጠለ የራሱ የሕግ ሰውነት ያለው ነው ፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ብቻ የሚመሰርተው የንግድ ማሀበር ሲሆን ይህ ማህበር ኃላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማኅበር (private limited company) ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። ከተጠያቂነትም አንቀፅር አባሉ ወይም መስራቹ የራሱን መዋጮ ሙሉ በሙሉ እስከ ከፈለ ድረስ ማኅበሩ ላይ ለሚፈለገው ዕዳ በግሉ ተጠያቂ አይሆንም ፡፡ የማህበሩ ባህርይ ኃላፊነቱ የተወሰነ በመሆኑ ማለትም የሚመጣ ተጠያቂነት በማህበሩ ሀብት ላይ ብቻ የተገደ በመሆኑ አባሉ ኃላፊነቱን ከተወጣ ማለትም መዋጮውን ሙሉ በሙሉ እና በወቅቱ እሰከከፈለ ድረስ ኃላፊነት የለበትም ማለት ነው፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው ይህ ማህበር በአንድ ሰው የሚመሰረት በመሆኑ የምስረታ እና የአስተዳደር ስርዓቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ስለዚህ በመርህ ደረጃ አባሉ መዋጮውን በወቅቱ ከከፈል ለሚመጣው ተጠያቂነት በግሉ ኃላፊነት የለበትም ቢባልም፣ ተጠያቂ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ግን አሉ፡አባሉ ማኅበሩን፣ ወይም የማኅበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ጉዳት ላይ የሚጥል ህገ-ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ ከፈፀመ፤ የባለ አንድ አባል ማኅበር ንብረትን ከራሱ ንብረት ጋር ከቀላቀለ፤ የባለ አንድ አባል ማኅበርን እና የራሱን ማንነት ካልነጣጠለ፤ ስለ ማኅበሩ የፋይናንስ አቋም የማኅበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ካወጣ፤ ያለ ተመጣጣኝ ክፍያ የማኅበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገኞች የግል ጥቅም ካዋለ፤ በሕግ ሊከፈል ከሚችለው በላይ የትርፍ ክፍያ ከፈጸመ፤ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ከፈጸመ ማንኛውም ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አባል ወይም ማኅበሩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ያለው ሌላ ሰው ከማኅበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ እንደሚሆን ህጉ በግልፅ ደንግጓል ፡፡
እንደሚታወቀው ኃላፊነታቸው የተወሰኑ ኩባንያዎች ዋነኛ ባህርይ ዕዳቸው በኩባንያው ሀብት ላይ የተወሰነና ወደ አባላቱ ሀብት የማይሸጋገር መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የቁጥጥር ሥርዓቱ ደካማ ከሆነ የኩባንያው ብቸኛ ባለሀብት መሆኑን በመጠቀም በዕዳ ከመጠየቅ ለመሸሽ ሲባል የኩባንያውን ሀብት ወደ ግል ሀብት የማሸሽ አጋጣሚን ሊያሰፋ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የኩባንያ መረጃዎች በአንድ ሰው ቁጥጥር ሥር ያሉ በመሆኑ በሦስተኛ ወገኖች ሊተላለፉና ሊታወቁ የሚገቡ መረጃዎች እንዳይታወቁ ሊደረግ የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት ያለ በመሆኑ ነው እንዲህ አይነት የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈለገው፡፡
4. የማህበሩ አመሰራረት
እንደሌሎች ማህበሮች ሁሉ ባለ አንድ አባል ኃለፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር የሚቋቋመው በመመስረቻ ጽሑፍ ሲሆን በንግድ መዝገብ ውስጥ እንደተመገዘበ የህግ ሰውነት የሚያገኝ ሲሆን ፣ ማህበሩን ለመመስረት ዝቅተኛ ዋና ገንዘቡ ከብር 15,000 (አሥራ አምስት ሺ) ማነስ የለበትም ፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመሰረተው አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት ሲሆን አባሉ የሚሰጠው መግለጫ ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት መደረግና መግልጫውም በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት ያለበት ሲሆን መግለጫው የሚከተሉትን ነገሮች ማሳየት አለበት ማኅበሩ አንድ አባል ብቻ ያለው መሆኑን፤ የአባሉን ስም፤ዜግነትና አድራሻ፤ አባሉ የሞተ፣ የጠፋ ወይም በፍርድ የተከለከለ እንደሆነ ስለ ወራሾቹ ወይም ስለ አባሉ ሆኖ ሕጋዊ ተግባራትን እንዲፈጽም የታጨው የንብረት ጠባቂ ሰው ስም፤ ዕጩ ንብረት ጠባቂው ፍቃደኛ ሆኖ ኃላፊነቱን የተቀበለ መሆኑን፤ የማኅበሩን ስም፤ዋና መሥሪያ ቤት፤ ካሉትም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹን፤ የማኅበሩን የንግድ ዓላማ፤ የማኅበሩ ዋና ገንዘብ መጠንና፤ይኼው በሙሉ የተከፈለ መሆኑን የሚያሳይ መግለጫ፤ በዓይነት የተከፈለ መዋጮ ካለ ግምቱን፤ የሥራ አስኪያጁን ስምና ሥልጣን፤ ካለ ኦዲተሩን፤ ማኅበሩ የሚቆይበትን ጊዜ፤ ማኅበሩ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የሚያስታውቅበተን መንገድና ጊዜ እና ሌሎች በሕግ ወይም በአባሉ እንዲካተቱ የተወሰኑ ጉዳዮችን ፡፡
ሌላው የምስረታው አካል የሆነው ጉዳይ እጩ ንብረት ጠባቂን በተመለከተ ነው፡፡ የማህበሩ አባል ወይም መስራች አንድ ሰው በመሆኑ ግለሰቡ በተለያዩ ምክንያቶች ስራውን መስራት ባይችል በህግ በግልፅ የተመለከተ አባሉን ተtክቶ የሚሰራ ሰው ከሌለ የንብረት ብክነትና መሰል ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ በሶስተኛ ወገኖች ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር በአንድ ሰው የሚመሰረት በመሆኑ አመራሩን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ከላይ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም አባሉ በሌለ ጊዜ፣ ቢሞት፣ ቢጠፋ ወዘተ ለማህበሩ ሀላፊነት የሚወስድ ወይም የማህበሩን ንብረት የሚጠብቅ አካል ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በህጉ ዕጩ ንብረት ጠባቂ የሚባል አካል ወይም ሰው እንዲኖር አስገዳጅ ድንጋጌ የገባ ሲሆን ዕጩ ንብረት ጠባቂው ዕጩነቱን የተቀበለ መሆኑን ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት ካላረጋገጠ በስተቀር፤ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊመሠረት አይችልም እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለተለያዩ ባለ አንድ አባል ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት የንብረት ጠባቂ ሆኖ መመረጥ አይችልም ፡፡
የንግድ ስራዎች በግለሰብ ነጋዴነት ከሚሰሩ ይልቅ በማህበርነት መሰራታቸው ለነጋዴውም ለሶስተኛ ወገኖችም የተሻለ ጥበቃ ስለሚሰጥ ግለሰብ ነጋዴዎች ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር መለወጥ ስለሚችሉበት ሁኔታም በህጉ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ መሰረት ግለሰብ ነጋዴ የንግድ ሥራውን ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርነት መለወጥ ይችላል፤ ሆኖም ግን ግለሰብ ነጋዴው ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከመመሥረቱ በፊት ለገባበት ዕዳ ሁሉ ከማኅበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ኃላፊ ይሆናል ፡፡
5. የማህበሩ አመራር (Governance)
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲኖረው ሕጉ የሚያስገድድ ሲሆን አባሉ ራሱ ወይም ሌላ ሰው የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ይችላል ፤ ዋናው ሥራ አስኪያጁም አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ያለው ሥልጣን እና ተጠያቂነት ይኖረዋል ፡፡ እንዲሁም ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚኖረው ሲሆን፣ የማኅበሩ አባል የአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አባላት ጠቅላላ ጉባዔ ያለውን ሥልጣን ይኖረዋል፤ አባሉ በጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣኑ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ቃለ-ጉባዔ ስብሰባው በተደረገ ከሦስት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በጽሑፍ ተዘጋጅተው የማህበሩ ማህደር ውስጥ መቀመጥ ይኖርባቸዋል፤ በማኅበሩ ምሥረታ ጊዜ በተሰጠ መግለጫ ውስጥ የተካተቱትን ነገሮች የሚለውጥ ማንኛውም ውሳኔ ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት አለበት እንዲሁም የአባሉ ውሳኔዎች የዚህን አንቀጽ ድንጋጌዎች ያላሟሉ ቢሆኑ እንኳን በሕግ ፊት የጸኑ ናቸው፤ ሆኖም ጉድለቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አባሉና ማኅበሩ በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናሉ ፡፡
6. የማህበሩ መፍረስ
ማህበሩ እንደአግባብነታቸው በንግድ ሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተመለከቱት ለማህበራት መፍረሻ ምክንያቶች በሚያገጥሙበት ጊዜ ሊፈርስ የሚችል ሲሆን የፈረሰው ማህበር አባል ያለበትን ዕዳ በሙሉ የከፈለ ከሆነ የማኅበሩ ሀብት ሳይጣራና ባለበት ሁኔታ በጠቅላላው ለአባሉ ይተላለፋል ፤ ምክንያቱም ማህበራት ሲፈርሱ ኦዲት የሚደረጉት በሁለት ምክንያች ሲሆን አንደኛው የማህበራትን አባላት መበት ለመጠበቀ ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ የሶስተኛ ወገኖችን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ በባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ግን አባሉ አንድ ስለሆነ የአባላጥ ጥቅም የሚባለ ነገር የማይነሳ ሲሆን፣ ሶስተኛ ወገኖችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚለው ነጥብ ደግሞ እዳ እንደሌለበት መረጋገጥ እንዳለበት ህጉ ያስቀምጣል፣ ሆኖም በማናቸውም ምክንያት ማኅበሩ ከፈረሰ በኋላ ገንዘብ ጠያቂዎች የቀረቡ እንደሆነ አባሉ በግሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አባሉን ተጠያቂ ለማድረግ የሚቀርብ ክስ ገንዘብ ጠያቂው የማኅበሩን መፍረስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፤ የማኅበሩ ሀብት ለአባሉ ከተላለፈ ከአሥር ዓመት በኋላ ምንም ዓይነት ክስ ሊቀርብ አይችልም ፡፡ ማህበሩ በሚፈርስበት ጊዜ አባሉ አባሉ በራሱ ምርጫ መደበኛውን የሒሳብ ማጣራት ሂደት ለመከተል ይችላል ፡፡