18/05/2026
📢 በህክምና ዘርፍ ለተሰማራችሁ ሃኪሞች፣ የህክምና እና ማስታወቂያ ድርጅቶች ጠቃሚ መረጃ 🇪🇹 አዲስ የጤና አገልግሎት መመሪያ ወጣ - መመሪያዉን መጣስ የብቃት ማረጋገጫ እስከ ማገድ የሚያደርስ ቅጣት ጨምሮ ሌሎች ቅጣትም የያዘ ነው -
የጤና ሚኒስቴር “የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ መመሪያ ቁጥር 1134/2018” አውጥቷል ። መመሪያው በጤና ተቋማት፣ በማስታወቂያ አዘጋጆች እና በስርጭት መንገዶች (ማህበራዊ ሚዲያ፣ ቴሌቪዥን፣ ቢልቦርድ ወዘተ) ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ።
ዋና ዋና ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው፡
1. የማስታወቂያ ይዘት እና ስነ-ምግባር
• መያዝ ያለባቸው መረጃዎች፦ ማስታወቂያው የጤና ተቋሙን ስም፣ ደረጃ፣ የሚሰጠውን አገልግሎት እና አድራሻ በግልፅ ማካተት አለበት ።
• የተከለከሉ ቃላት፦ “ተቀዳሚ ምርጫ”፣ “የሁሉም ምርጫ” እና መሰል ሰዎችን የሚያሳስቱ ቃላትን መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ ነው ።
• የባለሙያዎች ክብር፦ የሌሎችን ተቋማት አገልግሎት ማሳነስ ወይም በተቋሙ ያሉ ባለሙያዎችን ከሌሎች በተለየ “ላቀ ያለ እውቀት አላቸው” ብሎ ማቅረብ ክልክል ነው ።
• የተጋነኑ መግለጫዎች፦ ተቋሙ “ልዩ ንጥረ ነገር” እንደሚጠቀም ወይም “የተለየ ፈውስ” የሚገኝበት ብቻ አስመስሎ መግለጽ አይቻልም ።
• አካታችነት፦ ማስታወቂያው ግልጽ፣ የሙያ ቃላት ያልበዙበት እና የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ያገናዘበ መሆን አለበት።
2. የምስክርነት (Testimony) ገደቦች
• ማስታወቂያ ላይ ምስክር የሚያሳትፍ ከሆነ ምስክርነቱ ስለ ተሰጠው ክሊኒካዊ ሕክምና (ህክምናው እንዴት እንደተከናወነ) መሆን የለበትም ።
• ምስካሪው በትክክል አገልግሎቱን ያገኘና በጽሁፍ ፈቃዱን የሰጠ መሆን አለበት ።
• ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ወይም የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ከሆኑ የሰነድ ፈቃዱ ከወላጅ ወይም ከሕጋዊ ሞግዚት መገኘት አለበት ።
3. የማሰራጫ አካላት (የመገናኛ ብዙሃን/ዲጂታል ሚዲያ) ግዴታ
• ማስታወቂያውን የሚያስተላልፈው አካል የጤና ተቋሙ ሕጋዊ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት (License) ያለው መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት ።
💰 የአስተዳደራዊ ቅጣት
መመሪያውን ጥሶ የተገኘ አካል ጥፋቱን በ3 ወር ውስጥ ካልከፈለ የብቃት ማረጋገጫው ይታገዳል ። የገንዘብ መቀጮዎቹም፦
• የይዘት እና ስነ-ምግባር ድንጋጌዎችን መጣስ፦ ከ15,000 እስከ 50,000 ብር ።
• ያለጽሁፍ ፈቃድ ወይም አገልግሎቱን ያላገኘን ሰው በምስክርነት መጠቀም፦ ከ20,000 እስከ 50,000 ብር ።
• ሕፃናትን/ውሳኔ መስጠት የማይችሉ ሰዎችን ያለወላጅ ፈቃድ ማሳተፍ፦ ከ50,000 እስከ 100,000 ብር ።
• ግዴታውን ያልተወጣ ማስታወቂያ አስተላላፊ (ሚዲያ/አሳታሚ)፦ ከ10,000 እስከ 30,000 ብር ።
ሙሉ መመሪያዉን በቴሌግራም ቻናላችን ያገኙታል