17/02/2024
የማታለል ወንጀሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
ወንጀል በሰው ልጆች አካል፣ ክብር ወይም ንብረት ላይ ሊፈፀም የሚችል እኩይ ተግባር ሲሆን የተለያዩ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል አንደኛው እና ዋናው የፍትህ አካላት እና የህብረተሰብ ሀላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞ ሲገኝ ደግሞ ተገቢውን ህጋዊ የእርምት እና የቅጣት እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም የወንጀል ህግ ወንጀል ናቸው ብሎ እንዳይፈፀሙ የከለከላቸውን ወይም ደግሞ ያለመፈፀም ወይም ያለማድረግ የወንጀል ሀላፊነት እንደሚያስከትል የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ማክበር ግድ ይላል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ ለንብረት ጥበቃ ከሚያደርጉእና በንብረት ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎች ከሚዘረዝሩ ድንጋጌዎች መካከል የአታላይነት ወይም የማታለል ወንጀል አንዱ ነው፡፡ የተለያዩ የማታለል ድርጊቶችን በመፈፀም የሰዎች ንብረት የአታላዮች ሲሳይ ሲሆን መስማት በእለት ተእለተ እንቀስቃሴችን ውስጥ የሚያጋጥመን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ አጭር የንቃተ ህግ ፅሁፍየማታለል ወንጀል ምንነት፣በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ የተካተቱ የአታላይነት ወንጀሎች፣ ስለ ከባድ አታላይነት እንዲሁም ወንጀሎቹ የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት ይዳሰሳሉ፡፡
• የማታለል ወንጀል ምንነት
ማታለል ሆን ብሎ ሰውን በማጭበርበር ዋጋ ያለውን ነገር በአብዛኛው የገንዘብ ጥቅምን ለማግኘት የሚፈፀም ተግባር ነው፡፡ በአጠቃላይ ማታለል የሚፈጸመው ለማሳሳት ወይም ለማታለል የታሰበ የሀሰት መግለጫዎችን ወይም ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በመጠቀም ሲሆን በንብረት ላይ ጉዳት የማስከተል ውጤት ይኖረዋል፡፡ የማታለል ድርጊት የወንጀል እና ፍትሐ ብሄር ሀላፊነትን የሚያስከትል ሲሆን የፍትሐ ብሄር ሀላፊነት ንብረቱን የማስመለስ ወይም ካሳ ማስከፈልን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል የወንጀል ተጠያቂነት የእስራት እና የገንዘብ መቀጮ ቅጣቶችን የሚያስከትል ሲሆን በመቀጠል በወንጀል ህጉ የአታላይነት ምንነት ለመረዳት የሚጠቅመንን የህግ ድንጋጌ እንመለከታለን፡፡
በ1996 ዓ/ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 692 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለጽ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም፣በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው አታልሎ የራሱን ወይም የሶስተኛ ወገንን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ አድራጎት እንዲፈፀም ያደረገ እንደሆነ የአታላይነት ወንጀል እንደተፈፀመ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ይህ ወንጀል በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነትከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
ከድንጋጌው መገንዘብ እንደሚቻለው የአታላይነት ወንጀልን ለማቋቋም አራት መሰረታዊ ማቋቋሚያዎች ያሉ ሲሆን እነሱም፡-
ወንጀለኛውበአንቀፁ የተዘረዘሩትን ተግባራት ሆን ብሎ የፈፀመ እንደሆነ ፣
በዚህ ድርጊት የተነሳ ተበዳዩ ከተታለለ ወይም በአጥፊው ወይም በወንጀለኛው የተገለፀውን አምኖ የተቀበለ እንደሆነ(ለምሳሌ ስለሞያው ወይም ስለስራው የተሳሳተ ንግግር ተበዳዩ ያመነ እንደሆነ፣የሀሰት ውክልና አሳይቶ ያንን ውክልና ያመነ እንደሆነ)፣
በሀሰት የተገለፀውን በማመን የፈፀመው ተግባር ያለ እንደሆነ (ለምሳሌ ገንዘብ፣ጌጣ ጌጥ፣ንብረት የሰጠ እንደሆነ፣በቂ ገንዘብ የሌለውን ቼክ በመቀበል ግብይት ፈፅሞ እንደሆነ)፣
እንደዚሁም ተበዳዩ በመታለሉ የተነሳ የራሱ ወይም ሶስተኛ ወገን ያጣው የገንዘብ ወይም ዋጋ ያለው ነገር ጥቅምመኖር መቻል ያለበት መሆኑ ናቸው ፡፡
ከባድ አታላይነት
አንድ የማታለል ወንጀል በከባድ አታላይነት የሚያስቀጣው ፡-
o አድራጊው የማህበር፣ የባንክ፣ የንግድ፣ የአክሲዮን ገበያ ወይም የኢንዱስትሪ መስሪያ ቤት አክሲዮን፣ የእዳ ሰነድ፣ የቦንድ ወይም ማናቸውንም የዋስትና ሰነድ በማውጣት ከህዝብ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥሪ ያደረገ ወይም ለራሱ ወይም ለድርጅቱ ወይም አድራጊው የአክሲዮን ባለድርሻ ለሆነበት ድርጅት የሸጠ እንደሆነ ወይም
o ወንጀሉን የፈፀመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ እንደሆነ ከአስር አመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትናእስከ ብር ሃምሳ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 696 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል የማታለል ወንጀል የተፈፀመው በየመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ከሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሶስት ሺህ ብር እስከ ሰላሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32/1 ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም በማታለል ወንጀሉ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛ ወይም በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅት ወይም በህዝብ ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከሆነ፣ በወንጀል አድራጊው የስልጣን ደረጃ የወንጀሉ አፈፃፀም ከባድ አድርጎት እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከአስር ሺህ ብር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ የአዋጁ እንቀፅ 32/2 ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም ወንጀሉ የተፈፀመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከላይ ከተመለከቱት ቅጣቶች በአንዱ እንደሚቀጣ በአዋጁ እንቀፅ 32/3 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ማታለልን ያካተቱ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት ቅጣት
የተለያዩ የማታለል ወንጀሎች በተበዳዮች ላይ ሲፈፀሙ እንሰማለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የራስን እውነተኛ ማንነት በመደበቅ በማህበራዊ ሚዲያ ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጡ በመግለፅ፣ የፍቅር ጓደኝነት በመመስረት ከተግባቡ በኋላ ወደ ወጪ ሀገር እንደሚወስዱ በመግለፅ በተለያየ መንገድ በማሳመን ገንዘብ መቀበል፣ ፈጣን ሎተሪ ደርሶት ገንዘቡን ለመውሰድ መታወቂያ ስለሌለው በተበዳይ መታወቂያ እንዲያወጣ በማሳመን ለመያዣነት ስልክ፣ ገንዘብ፣ ኮምፒውተር፣ ገንዘብ እና የመሳሰሉትን በመቀበል መሰወር ፣ በባንክ ደብተር ውስጥ በቂ ገንዘብ ሳይኖር ገንዘብ እንዳለ በማሳመን ግብይት መፈፀም፣የስልክ ቁጥሩ የሎተሪ አሸናፊ እንደሆነ በመግለፅ ገንዘቡ እንዲላክላቸው የሞባይል ካርድ እንዲሞሉ ወይም የባንክ አካውንት ውስጥ ገንዘብ እንዲያስገቡ በማሳመን ገንዘብ መቀበል ለአብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የማታለል ወንጀሎች ናቸው፡፡
እነዚህ እና ሌሎች የማታለል ድርጊቶች በወንጀል ህጉ ያላቸውን ሽፋን እና የሚያስከትሉትን ቅጣት እንደሚከተለው እናያለን፡፡
የሚያዝበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ማውጣት በወንጀል ህጉ እንቀፅ 693/1/ እና 2 ስር የሚስጠይቅ ሲሆን ማንም ሰው ቼክ በሚያወጣበት ወይም ለባንክ በሚያቀርብብት ጊዜ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ ቼክ ያወጣወይም የሰጠ እንደሆነ በቀላል እስራት (ከአስር ቀን እስከ 3 ወር) ወይም እንደነገሩ ከባድነት ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም በቼክ የማታለል ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኝነት(ለምሳሌ ተከሳሹ በአካውንቱ ውስጥ በቂ ገንዘብ ያለው መስሎት ያለውን የገንዘብ መጠን ሳያረጋግጥ የፈረመ) እንደሆነ በገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
በተጭበረበረ ሁኔታ የአክሲዮን ገበያን ንግድ ማካሄድ ሌላው በወንጀል ህጉ የተካተተ የማታለል ወንጀል አይነት ሲሆን ማንም ሰው በአክሲዮን ገበያ ወይም በሌላ ገበያ አማካኝነት የአክሲዮን ወይም የአክሲዮን የገቢያ ዋጋ በሚመለከት የህዝብ አክሲዮን ንግድ እንዳለ የሚያስመስል ሀሰተኛ ወይም አሣሣች መልክ ለመፍጠር በማሰብ፡-
o በአክሲዮን ባለቤትነት ላይ ምንም ጠቃሚ ለውጥ የማያመጣ የአክሲዮን ንግድ ያካሄደ እንደሆነ፣
o አክሲዮኖቹ በተጠየቁት ተቀራራቢ መጠን ፣ተቀራራቢ ጊዜ እና በተቀራራቢ ዋጋ በዚያው ሰው ወይም በሌላ ሰው እንደተገዛ ወይም ለዚያው ሰው ወይም ለሌላ ሰው የገዢው ጥያቄ እንደቀረበ ወይም እንደሚቀርብ እያወቀ አክሲዮኖቹን ለመግዛት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ወይም፣
o አክሲዮኖቹ በተጠየቁት ተቀራራቢ መጠን፣ተቀራራቢ ጊዜ እና ተቀራራቢ ዋጋ በዚያው ሰው ወይም በሌላ ሰው እንዲሸጡ ወይም ለዚያ ሰው ወይም ለሌላ ሰው የሽያጭ ጥያቄ እንደቀረበ ወይም እንደሚቀርብ እያወቀ አክሲዮኖችን ለመሸጥ ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
በአክሲዮኖች ወይም በሸቀጦች መቆመር ፡- ማንም ሰው በሀገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የተመዘገቡ ወይምያልተመዘገቡ ኩባንያዎች ወይም ሌሎች የንግድ ድርጅቶች አክሲዮኖች ወይም ማናቸውም ዕቃዎች ወይም ሸቀጦች ዋጋቸውን ዝቅ ወይም ከፍ ማለቱን ምክንያት በማድረግ ገቢ ወይም ትርፍ ለማግኘት በማሰብ አክሲዮኖቹን ወይም ዕቃዎቹን ወይም ሸቀጦቹን የራስ የማድረግ እውነተኛ ሀሳብ ሳይኖረው እነዚህን ነገሮች የሚሸጥ ወይም የሚገዛ በማስመሰል ማናቸውንም ዓይነት ውል በፅሁፍም ሆነ በቃል ያዘጋጀ ወይም የፈረመ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በአንቀፅ 695 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ኢንሹራንስ በሚመለከት የሚፈፀም የአታላይነት ድርጊት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 698 መሰረት የሚያስቀጣ ሲሆን ማንም ሰው የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፡-
o ኢንሹራሱን የተገባበትን አደጋ በመፍጠር ወይም
o በውል ውስጥ በተገለፀው ጥቅም ላይ ተፅዕኖ በሚያደርግ አኳኃን የኢንሹራንሱን ገንዘብ ልክ፣ የውሉን ዘመን፣ ወይም የኢንሹራንሱን ተጠቃሚዎችን የሚመለከት ፍሬ ነገር በመደበቅ፣በማሳሳት፣በማረጋገጥ ወይም ይህንኑ በሚመለከት ሀሰተኛ መግለጫ በመስጠት አንድ የኢንሹራንስ ማህበርን ካታለለ፣
o በማናቸውን ሌላ መንገድ ከኢንሹራንስ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የአታላይነት ድርጊት ከፈፀመ በቀላል እስራት ወይም ሁኔታዎች ይበልጥ ከባድ ሲሆኑ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከብር ሀምሳ ሺ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በህዝብ እምነት በመጠቀም ማታለል፡- ማንም ሰው ለራሱ ብልፅግና ለማግኘት አስቦ መንፈስ እጠራልሃለሁ፣ጋኔን እስብልሃለሁ፣ ደንቃራ እጥልልሃለሁ፣ እጠነቁልልሃለሁ፣ ዕድልህን እነግርሃለሁ፣ ነገርን እገልፅልሃለሁ፣ ኮከብህን እቆጥርልሃለሁ፣ ህልምን እፈታልሃለሁ፣ የወደፊት ዕድልህን አውቅልሃለሁ፣ ወስጥ እጅህን አነብልሃለሁ፣ ከሞተ ሰው ጋር አነጋግርሃለሁ በማለት፣ ወይም በሰው እምነት ያለአግባብ መገልገል በሚያስችል በማናቸውም ሌላ መንገድ ሰውን ያታለለ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት አፈፃፀሙ በደንብ መተላለፍ ድንጋጌዎች የሚያስቀጣ ካለሆነ (ቀላል ካልሆነ) በቀር በመቀጮ ወይም የተደጋገመ ወንጀል በፈፀመ ጊዜ በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት እንደሚያስቀጣ የወንጀል ህጉ እንቀፅ 700 ይደነግጋል፡፡
በተጨማሪ ማንም ሰው ከባድ በሽታ ወይም ጉድለት አለብኝ ወይም ከፍተኛ አካላዊ ወይም ስነ- ልቦናዊ ጉዳት ወይም የገንዘብ ወይም ሌላ ማቴሪያላዊ ኪሳራደረሰብኝ በማለት የሀሰት ንግግር በማድረግ ወይም የሰዎችን ሀዘኔታ ስሜት በሚስብ በማናቸውም ሌላ የማታለል ዘዴ በመጠቀም ከግለሰብ ወይም ከሕዝብ ገንዘብ ወይም ማቴሪያላዊ ነገር የሰበሰበ እንደሆነ እንዲሁም ከላይ ከተዘረዘሩትነገሮች አንዱ በሌላ ሰው ላይ የደረሰ አስመስሎ የተባለውን ሰው ለሕዝብ በማቅረብ በመለመኛነት የተገለገለበት እንደሆነና ይህንኑ ለመርዳት ነው በማለት ከግለሰቦች ወይም ከሕዝብ ገንዘብ ወይም ማቴሪያላዊ ነገር የሰበሰበ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡እንዲሁም ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ ከላይ ለተመለከተው ዓላማ የተጠቀመበት እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በሌላ በኩል ማንም ሰው ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ ወይም ሰብዓዊ ጉዳዮችን ወይም ማናቸውንም ሌላ ዓላማ ምክንያት በማድረግ በህግ ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን ተፈቅዶለትም ሆነ ሳይፈቀድልት ከግለሰብ ወይም ከህዝብ ላይ ገንዘብ ወይም ማናቸውንም ማቴሪያላዊ ነገር ሰብስቦ ይህንኑ ገንዘብ ወይም ማቴሪያላዊ ነገር በሙሉ ሆነ በከፊል ከሰበሰበበት ዓላማ ውጪ ያለአግባብ ያዋለ እንደሆነ ገንዘብ ያለፍቃድ ስለመሰብሰብ የተመለከተው የወንጀል ህጉ አንቀፅ 862 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከሰላሳ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በአጠቃላይ የሰዎችን እምነት በመጠቃም ወይም በተለያዩ ንግግሮች እና ድርጊቶች ሰዎችን በማሳሳት የገንዘብ ወይም ዋጋ ያለው ነገርን ለራስ ማድረግ በአታለይነት ወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ማህበረሰቡ ንብረቱ የአታላዮች ሲሳይ እንዳይሆን በወንጀለኞች የሚደረጉ ንግግሮችን እና ድርጊቶች ከማመኑ በፊት መጠራጠር እና ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ የበለጠም ጥቅምና ንብረቱን መጠበቅ እንዲሁም ንብረቱን ከመስጠቱ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ፣ ነገሮችን ማጣራትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የማታለል ድርጊቶቹ ተፈጽማውሲገኙም ለሚመለከተው የህግ አካል በማቅረብ አጥፊዎች እንዲቀጡ ሌሎችም እንዲማሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምንጭ:- በኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር በንቃተ ህግ፣ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ