Berhan Bank Labor Union, የብርሃን ባንክ ሰራተኞች ማህበር

Berhan Bank Labor Union, የብርሃን ባንክ ሰራተኞች ማህበር Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Berhan Bank Labor Union, የብርሃን ባንክ ሰራተኞች ማህበር, Labor & Employment Lawyer, Addis Ababa.

ይህ የማህበራችን ትክክለኛ የፌስቡክ ገፅ ነዉ።
‼በመብቱ ጉዳይ አዉቆ የተኛን ፤ በራሱ ጊዜ ነቄ ካልሆነ በስተቀር ፤ ህጉ ራሱ ህያው ሆኖ ቆሞ ሊቀሰቅሰዉ (ሊያነቃዉ) አይችልም‼
የማህበሩ Telegram channel https://t.me/Berhanbanklaborunion ለመልዕክትዎ፦ [email protected]

በመደበኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታገዱ!የማህበራችን ብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር ነባር ማህተም እያለ ፤ ከማህበራችን ዕዉቅና እና አሠራር ዉጪ ( የኢ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 364 እ...
28/08/2026

በመደበኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታገዱ!

የማህበራችን ብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር ነባር ማህተም እያለ ፤ ከማህበራችን ዕዉቅና እና አሠራር ዉጪ ( የኢ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 364 እንዲሁም ያልታተመዉ የሰ/መ/ቁ 145996) ስድስት ግለሰቦች አዲስ ማህተም በማስቀረፅ በማህበራችን ስም በመንቀሳቀሳቸው እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በመ/ቁ 053/3/17 እና 034/1/17 ሲታዩ የነበሩ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሠራተኞችን የሚመለከተው ከጥር/2015 እስከ ሐምሌ/2017 ድረስ የቤት አበል ዉዝፍ ክፍያ ክርክር ጉዳይ "....ለሠራተኛው ተፈፅሟል ፤ በስምምነት ተፈቷል...." በማለት የክስ መዝገቡ በሚገርም ሁኔታ በነሐሴ 08/2018 ለማዘጋት ጭምር ችለዋል።

ማህበራችን የእነዚህ ግለሰቦች ተግባር በተመለከተ ሙሉ ማጣሪያ አድርጎ እና ማስረጃ አደራጅቶ ክስ እስኪመሰርት ድረስ የቅድመ ክስ የእግድ ትዕዛዝ (የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.154/2 እንዲሁም በቅፅ 25 የታተመዉ የሰ/መ/ቁ.191402) እንዲሰጥለት ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በፅሁፍ አቤቱታ ጠይቋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አቤቱታችን ተመልክቶ እነዚህ ግለሰቦች ከነሐሴ 20/2018 ጀምሮ የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበርን በመወከል ማንኛውም ተግባር እንዳይፈፅሙ ፣ አዲስ ያስቀረፁት ማህተም እንዳይገለገሉ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ግለሰቦቹ የግል ፍላጎታቸው ለማሳካት ከማህበራችንም ሆነ አባል ሠራተኛዉ ዕዉቅና ዉጪ የፈፀሙት ዝርዝር ተግባር በተመለከተ ዉጤቱን በቀጣይ ጊዜ የምናሳዉቃችሁ ይሆናል። ህጋዊ ዉክልና ሳይኖር የተፈፀመ ተግባር ሁሉ እንዳልተደረገ የሚቆጠር በመሆኑ ጉዳዩን በትጋት ተከታትለን የምናሳዉቃችሁ ይሆናል።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩ እና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር ፤ የዘወትር ድምፅ!






ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም.

ዉሸት በገነነበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ እዉነተኛ የሆኑ ሁሉ ስቃይ ይበዛባቸዋል!✊ የሠራተኛው መብትና ጥቅም እንዲከበር ፤ ግልጽ አሠራር እና ጤናማ የሠራተኛ አያያዝ በባንካችን እንዲተገበር የምት...
16/08/2026

ዉሸት በገነነበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ እዉነተኛ የሆኑ ሁሉ ስቃይ ይበዛባቸዋል!

✊ የሠራተኛው መብትና ጥቅም እንዲከበር ፤ ግልጽ አሠራር እና ጤናማ የሠራተኛ አያያዝ በባንካችን እንዲተገበር የምትተጉ ሠራተኞች በዘወትር አቋማችሁ ፀንታችሁ ከእኛ ጋር ለመቀጠል እንድትችሉ ዛሬም መልዕክታችን ይህ ነዉ።

በደራሲ በዓሉ ግርማ «የቀይ ኮከብ ጥሪ» መጽሐፍ ላይ የተገለፀዉ የግብዝነት እና የግል ጥቅም ማስቀደም ጭምብል ዛሬም በማህበራችን ዙሪያ በሚገኙ አካላት በሰፊዉ ይንፀባረቃል።

በግል ጥቅም በመነዳት የማህበራችን እና የአባል ሠራተኛዉ እውነተኛ ድምፅ ለማፈን ጥረት ቢደረግም በተከተልነው የስሜት ብልህነት እና ህጋዊ አካሄዳችን የተነሳ የታሰበዉን ያህል ፍሬ ሳያፈራ ከሽፏል።

የማህበራችን አቋም የሁሉም ሠራተኛ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲሰፍን ነዉ።

የሠራተኛ ማህበር እና አመራሩ ለእውነት ሲቆም የሚከፍለው ዋጋ ከምስረታችን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተግባር ታይቷል።

ከእኛ ጋር በጊዜያዊ ወኔ ወይም ዘላቂነት በሌለዉ የስሜት ተነሳሽነት የጀመሩ ጥቂቶች "...ለእዉነት መቆም በዚህ ዘመን አያዋጣም..." ብለዉ ተለይተዉናል። ተለይተውን ሳያበቁ እኛ በአቋም ስለፀናን ብቻ ዋጋ ሊያስከፍሉን የጥቅም ተልዕኮ ወስደዉ ሐሰተኛ መረጃ በማህበራችን እና በአመራሩ ላይ እያሰራጩ ይገኛሉ።

በሐምሌ 19/2018 በማህበራችን ጠቅላይ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ የተገኙ አባላቶች ላይ በቀጥታ በማነጣጠር ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ከራሳቸዉ መረጃ ተረድናተናል።

ሠራተኛው ከመደበኛ የሥራ ሰዓቱ ዉጪ ህጋዊ ስብሰባ ወይም የመረጠውን የትኛውም ህጋዊ ተግባር ማካሄድ መብቱ ነዉ።

ሀይማኖት የግል እንደሆነዉ ሁሉ የሠራተኛ ማህበር አባልነት እና ተሳትፎም የሠራተኛው የግል ምርጫ ነዉ።

"...በሠራተኛ ማህበር ስብሰባ በመገኘታችሁ እርምጃ ሊወሰድባችሁ ስለሆነ አልተገኘሁም ብላችሁ ፈርሙ..." በማለት ሠራተኛውን መደለል ህገወጥ ተግባር ብቻ ሳይሆን የወንጀል ፍሬ ነገር የሚያቋቁም ጭምር ነዉ ብለን እናምናለን።

ህገወጥ ተግባር በማህበራችን እና በአባላቱ ላይ እየፈፀሙ የሚገኙ ሁሉም አካላት መርህ አልባ የሆነዉ ትብብራቸዉ ዋና ዓላማ የማህበራችን የሥራ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ አለፍ ሲልም ከተቻለ ማህበሩን ለማፍረስ ነዉ። አሁን ላይ ጭምብላቸዉ የገለጡ በርካታ ናቸው።

ለህገወጥ ተግባር ሰለባ ከሆኑ አባል ሠራተኞች ጋር በመቆም ፤ በዚህ ተግባር ላይ በተሳተፉ ሁሉም አካላት ላይ ህጋዊ ምርመራ እንዲደረግልን እንጠይቃለን።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩ እና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር ፤ ድምፅ !

ነሐሴ 10 ቀን 2018 ዓ.ም.




የሠራተኛው ጥያቄ ላይ ፈጣን እልባት ለማሰጠት ዉይይት  #መተኪያ የሌለዉ ሁነኛ መፍትሄ ነዉበዚህም የተነሳ ማህበራችን ለዉይይት ሁልጊዜም የቅድሚያ ቅድሚያ ይሰጣል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሞክ...
15/08/2026

የሠራተኛው ጥያቄ ላይ ፈጣን እልባት ለማሰጠት ዉይይት #መተኪያ የሌለዉ ሁነኛ መፍትሄ ነዉ

በዚህም የተነሳ ማህበራችን ለዉይይት ሁልጊዜም የቅድሚያ ቅድሚያ ይሰጣል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሞክረናል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ከማኔጅመንቱ ጋር ለማስማማት በሰኔ 25 ቀን 2017 በጠራው ስብሰባ ክሶቻችን አቋርጠን ከማኔጅመንቱ ጋር ለመወያየት ፈርመናል።

ሆኖም በማግስቱ በሰኔ 26/2017 የባንካችን ማኔጅመንት ስምምነቱን በማፍረስ በማህበራችን ፕሬዝዳንት ላይ አግባብነት የሌለዉ የወንጀል ጥቆማ በማቅረብ ከሥራ ቦታው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ አቧሬ ቅርንጫፍ ተይዞ ወደ ሀዋሳ ከተማ ተወስዶ እንዲታሰር ሆነ።

ፕሬዝዳንታችን በእስር ላይ ሆኖ ማኔጅመንቱ በሰኔ 27/2017 በተፃፈ ደብዳቤ ክሶቻችሁ አዘጉ እና ለሐምሌ 02/2017 በዋና መ/ቤት ለስብሰባ ቅረቡ ብሎ ጠየቀን።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሰኔ 25/2017 ስምምነት በእስሩ ምክንያት እንዳይፈርስ ብሎ እስር ላይ ሆኖ መልዕክት በመላኩ በጉዳዩ ላይ ተወያይተንበት በሒደት የነበሩ ክሶቻችን በሙሉ አቋርጠን ለሐምሌ 02/2017 ስብሰባ ዝግጁ መሆናችን ለባንኩ ማኔጅመንት በሐምሌ 01/2017 በደብዳቤ አሳወቅን።

ሁሉንም ልዩነቶች በዉይይት ለመፍታት ጉጉት ነበረን። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከእስር ተፈቶ በቀጠሮዉ መሰረት የባንኩ ዋና መ/ቤት በሐምሌ 02/2017 ለዉይይት ቀረብን።

ለዉይይት ስንቀርብ ግን ያላሰብነዉን ክስተት ገጠመን። ለዉይይት የጠራን ማኔጅመንት የማህበራችን ፕሬዝዳንት በሠራተኛ ማህበሩ ማህበራዊ ገፆች የባንኩ ስም አጉድፈሃል ብሎ የስንብት ደብዳቤ በስብሰባዉ መድረክ ሰጠዉ። ለሌሎቻችንም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እና የ20% የደመወዝ ቅጣት ደብዳቤ ተሰጠን። የጓጓንለት ዉይይት በዚህ ምክንያት ሳይካሄድ ቀረ።

ለካ! ማኔጅመንቱ የዉይይት ደብዳቤ በፃፈልን ሰኔ 27/2017 ተመሳሳይ ቀን የዲስፕሊን ኮሚቴ ተሰብስቦ "....የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር እና የሥራ አስፈፃሚ አመራሮች የዲስፕሊን ግድፈት..." የሚል ቀጥተኛ አጀንዳ ይዞ እና ተወያይቶ በእኛ ላይ ቅጣት ወስኗል። ከዛ በኋላ የሆነው ሁሉ ሆኖ አሁን ላይ ደርሰናል።

በባንኩ የዲስፕሊን ኮሚቴ የተያዘዉ 5 ገፅ ቃለጉባኤ ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 26 እና 14 እንዲሁም ሀገራችን ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቻቸዉ የዓለም የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን ቁጥር 87 አንቀፅ 3 እና 4 በተጨማሪም ኮንቬሽን ቁጥር 98 አንቀፅ 1 እና 2 አንፃር እንዲመረመርልን ጉዳዩ ለፍ/ቤት አቅርበነዉ በሒደት ላይ ይገኛል።

ሆኖም እኛ ክስ የመጀመሪያ አማራጭ ነዉ ብለን በፍፁም አናምንም። አሁንም ለዉይይት ዝግጁ ነን።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩ እና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር

ነሐሴ 09 ቀን 2018 ዓ.ም.




በመሪነቴ እቀጥላለሁይህ ከማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክት ነዉ።ዉድ አባል ሠራተኞች በባንካችን ታሪክ ቀዳሚ የሆነውን የሠራተኛ ማህበሩ ለማቋቋም ተነሳሽነት መዉሰድ ብቻ ሳይሆን ከተቋቋመ ...
09/08/2026

በመሪነቴ እቀጥላለሁ

ይህ ከማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክት ነዉ።

ዉድ አባል ሠራተኞች በባንካችን ታሪክ ቀዳሚ የሆነውን የሠራተኛ ማህበሩ ለማቋቋም ተነሳሽነት መዉሰድ ብቻ ሳይሆን ከተቋቋመ በኋላም የሚገጥሙትን ፈተናዎች ለመቀነስ ዉይይቶችን ጨምሮ ሁሉንም ጥረቶች አድርጌያለሁ። አሁንም ድረስ ከማኔጅመንቱ ጋር በመካከላችን ያሉ ልዩነቶች በዉይይት ለመፍታት ጥረቴን አላቋረጥኩም።

ከባንኩ ማኔጅመንት ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበረኝ ማሳያዉ በ2016 ዓመታዊ የማኔጅመንት ስብሰባ ወቅት አጠቃላይ የባንኩ ሠራተኛ በመወከል ተገኝቻለሁ። የባንካችን ክቡር ዋና ሥራ አስፈፃሚ በማኔጅመንቱ ዓመታዊ ስብሰባ ሠራተኛዉን በመወከል ለመገኘት እንድችል ላደረጉልኝ አክብሮታዊ ጥሪ አመሰግናለሁ። እሳቸው በግላቸዉ መልካም ስብዕና እንዳላቸው በሚገባ እረዳለሁ።

ዉድ አባል ሠራተኞች ፦ የማህበራችሁ መሪ እንደመሆኔ በዚህ ወቅት የተፈጠሩ የማደናገሪያ መረጃዎችን እያጠራሁ እና እየተከላከልኩ እገኛለሁ። በፍትህ ሒደት የሚገኙ ሦስት ጉዳዮችን ልክ እንደ ማህበሬ እኔም በግልፀኝነት ላሳዉቃችሁ እወዳለሁ።

¹ በሠራተኛ ማህበር ህጋዊ ሥራ ምክንያት የተወሰደብኝ ስንብት ህገወጥ ተብሎ ወደ ሥራዬ እንድመለስ በመስከረም 20/2018 ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ችሎት አቅርቤ በክርክር ሒደት እገኛለሁ። ቢዘገይም የፍትህ ሒደቱን አከብራለሁ ፤ እታገሳለሁ።

² የባንካችን ማኔጅመንት የራሱን የስንብት እርምጃ በመጥቀስ እኔን ከፕሬዝዳንትነት ለማስነሳት ለማህበራችን በህዳር 05/2018 እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ በጥር 01/2018 የፃፈዉ ደብዳቤ ህገወጥ እንዲባል ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ችሎት አቅርቤ በክርክር ሒደት እገኛለሁ።

³ የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ከባንካችን ማኔጅመንት በጥር 01/2018 የቀረበለትን አቤቱታ ተቀብሎ በአሠሪ የተሰናበተ ሠራተኛ ማህበሩን ለመምራት ስለማይችል በ1 ወር ጊዜ እርምት እንዲያደርግ አልያም ማህበሩ የሚታገድ ስለመሆኑ በየካቲት 04/2018 የፃፈዉ አስገዳጅ የቁጥጥር መመሪያ በተመለከተ በራሱ የዉስጥ አስተዳደር እርምት እንዲደረግበት ማህበራችን የይግባኝ ቅሬታ ለቢሮዉ ኃላፊ አቅርቦ መፍትሔ ሳያገኝ ሲቀር የደብዳቤ ትዕዛዙ የእኔ መብት ጭምር የሚነካ በመሆኑ ለከፍተኛ ፍ/ቤት የአስተዳደር ጉዳዮች ችሎት የክለሳ አቤቱታ በግሌ አቅርቤ በክርክር ሒደት እገኛለሁ። ለክለሳ የቀረበዉ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ የቢሮዉ የደብዳቤ ትዕዛዝ እንዲታገድልኝ ጠይቄ ከመጋቢት 01/2018 ጀምሮ የቢሮዉ ትዕዛዝ በከፍተኛ ፍ/ቤት ታግዶ ይገኛል።

የመረጠኝ ሠራተኛው በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሚያዚያ 21/2018 በሰ/መ/ቁ 294319 እኔን በተመለከተ በሰጠው አስገዳጅ ዉሳኔ መሰረት በመሪነቴ የሠራተኛ ማህበሩን በትጋት ማገልገሉን እቀጥላለሁ።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ!

ነሐሴ 03 ቀን 2018 ዓ.ም.




ለ3,000 ያህል ሠራተኞች ለእያንዳንዳችን ብር 24,000 የ30 ወራት በድምሩ ብር 72,000,000.00 (ሰባ ሁለት ሚሊየን ብር) የቤት ኪራይ አበል ዉዝፍ እንዲከፈለን ያቀረብነው የዳኝነት...
05/08/2026

ለ3,000 ያህል ሠራተኞች ለእያንዳንዳችን ብር 24,000 የ30 ወራት በድምሩ ብር 72,000,000.00 (ሰባ ሁለት ሚሊየን ብር) የቤት ኪራይ አበል ዉዝፍ እንዲከፈለን ያቀረብነው የዳኝነት ጥያቄ ለማስቆም ማህተማችን በሐሰት እስከማስቀረፅ ድረስ ህገወጥ ተግባር ተፈፅሞብናል።

በሁለትዮሽ ዉይይት (Social dialogue) ሳይፈቱ ቀርተዉ በህግ የተያዙ ጉዳያችሁ የደረሰበትን ሙሉ ሒደት አባል ሠራተኞች የማወቅ ሙሉ መብት ፤ እኛም ለእናንተ የማሳወቅ የዉዴታ ግዴታ አለብን። እናንተ ወካይ እኛ ደግሞ ተወካያችሁ ነንና።

ዉድ ሠራተኞች በጥር/2015 ዓ.ም. ለሌሎች ባልደረቦቻችን የኑሮ ዉድነት መደጎሚያ ተብሎ የተከፈለው የቤት ኪራይ አበል በተለምዶ የባንኩ አጠራር በፅህፈት መደብ ያልሆኑት ከደረጃ 1 እስከ 4 የሥራ መደብ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ሳይከፈላቸዉ መቅረቱ በሠራተኞች መካከል በአሠሪ የሚፈፀም የአድሎ ተግባር በመሆኑ ከባንካችን ማኔጅመንት ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም በሦስትዮሽ መድረክ ለመፍታት ጥረት ብናደርግም መፍትሔ ባላማግኘታችን ጉዳዩ ለዳኝነት አካላት አቅርበን እስከ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም. ድረስ ክርክር ስናደርግበት መቆየታችን ይታወሳል።

መጀመሪያ ክሱን አቅርበንለት የነበረዉ የአዲስ አበባ ከተማ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ጉዳዩን ለማየት የዳኝነት ስልጣን የለኝም ብሎ በሚያዚያ 03 ቀን 2015 ዓ.ም. በመ/ቁ 035/15 በብይን የዘጋብን በመሆኑ በመጨረሻም ጉዳዩ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ በየካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰ/መ/ቁ 263727 ጉዳዩን የማየት የዳኝነት ስልጣን የአዲስ አበባ ከተማ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ እንጂ የመደበኛ ፍ/ቤቶች አይደለም ተብሎ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ከተሰጠበት በኋላ ወደ ወሳኝ ቦርድ ተመልሰን የቤት አበሉ ለሌሎች ሠራተኞች ከተከፈለበት ከጥር/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥር ወደ 3,000 ለምንጠጋ Non-Clericals ሠራተኞች እንዲከፈለን እንዲወሰንልን ክሳችን በመጋቢት 25/2017 በድጋሚ ልናቀርብ ችለናል።

ክሳችን በድጋሚ የተመለከተዉ የአዲስ አበባ ከተማ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በሐምሌ 30/2017 በመ/ቁ 034/1/17 ብርሃን ባንክ አ.ማ. ለኑሮ ዉድነት መደጎሚያ ብሎ ለሌሎች ሠራተኞቹ የቤት አበል ከብር 800 እስከ ብር 10,000 ሲከፍል በፅህፈት መደብ ላይ ላልሆኑት ሠራተኞች አለመክፈሉ በሠራተኞች መካከል የአድሎ ተግባር ፈፅሟል በማለት ዉሳኔዉ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ የቤት ኪራይ አበሉ እንዲከፈለን የወሰነልን በመሆኑ ፤ የባንኩ ማኔጅመንት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 341141 ይግባኝ አቅርቦ ዉሳኔዉ ስለፀናበት በዉሳኔዉ አግባብ አሁን ላይ በደመወዝ ፔሮላችን ተተክሎልን በየወሩ እየተከፈለን ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ዉሳኔ ከሰጠበት ቀን ጀምሮ የቤት ኪራይ አበሉ ቢወስንልም ረክተን አልቆምንም። ይልቁንም የቤት ኪራይ አበሉ ለሌሎች ሠራተኞች ከተከፈለበት ከጥር/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በውዝፍ እንዲከፈለን በማለት የጠየቅነዉን ዳኝነት የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በዝምታ አልፎብናል በማለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 346511 የይግባኝ ቅሬታ አቅርበን ፤ ይግባኛችን ተቀባይነት አግኝቶ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በዝምታ ያለፈው ጉዳይን ብቻ እንደገና አጣርቶ ዉሳኔ እንዲሰጥበት ከከፍተኛ ፍ/ቤት ጭብጥ ተለይቶ በትዕዛዝ ተላከለት።

የባንኩ ማኔጅመንት በዉዝፍ ክፍያዉ ላይ ለዉይይት ከእኛ ጋር ይቀመጣል ብለን ስንጠብቀዉ እያለ ጭራሹን ባልተመለደ ሁኔታ የከፍተኛ ፍ/ቤት ትዕዛዝ እራሱ ወጪ በማድረግ ለአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ አቅርቦ መዝገቡን ስለመንቀሳቀሱ መጥሪያ አመጣልን። በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.343 ድንጋጌ አግባብ በይግባኝ ተወስኖልኛል ብሎ ወደ ስር ፍ/ቤት በመቅረብ መዝገቡን ማንቀሳቀስ ያለበት በመርህ ደረጃ በይግባኝ ዉሳኔዉ ተጠቃሚ የሆነው ተከራካሪ ወገን ነዉ። የዉሳኔዉ ተጠቃሚ ያልሆነ ወገን የስር ፍ/ቤት መዝገብ ይንቀሳቀስልኝ ብሎ ሲጠይቅ የባንካችን ማኔጅመንት የመጀመሪያ ነዉ ብንል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም እንደዚህ አይነቱ Scenario በጭንቅ ቢገኝ ነዉ። የባንኩ ማኔጅመንት ተግባር በወቅቱ አስገርሞናል። ተጠቃሚ ያልሆነበት መዝገብ ለማንቀሳቀስ የፈለገበት ምክንያት በተመለከተም የራሳችን ግምት ነበረን።

መዝገቡ ተንቀሳቅሶ የፌድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በቤት አበል ዉዝፍ ጉዳይ ላይ ለይቶ በያዛቸው ጭብጦች ላይ ከሳሽ እና ተከሳሽ አስተያየት እንድንሰጥበት ዕድል ተሰጥቶን በመጋቢት 02/2018 አስተያየት ከሰጠን በኋላ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ጉዳዩን መርምሮ ዉሳኔ ለመስጠት ለመጋቢት 16/2018 ቀጠረን። የባንኩ ማኔጅመንት ለእሱ ጥቅም ያልተወሰነለትን የይግባኝ ዉሳኔ ተከትሎ በወሳኝ ቦርድ መዝገቡ ይንቀሳቀስልኝ ብሎ ጠይቆ መጥሪያ ሲያመጣልን አስቀድሞ እንደገመትነው ለዉሳኔ በተቀጠረ ቀጠሮ ቀን አዲስ የሠራተኛ ማህበር ነን የሚሉ ቡድኖች የጣልቃገብነት አቤቱታ አቀረቡ።

የጣልቃገብነት አቤቱታው ዋናዉ ይዘት በክርክሩ ገብተን እንከራከር የሚል ሳይሆን የቤት አበል ጉዳይ ስለተቋጨ እና ለሠራተኛው የቤት አበል ስለተከፈለዉ ክርክሩ እንዲቀጥል የሠራተኛው ፍላጎት አይደለም የሚል ነበር።

የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ለመጋቢት 16/2018 የቀጠረውን የዉሳኔ ቀጠሮ ተለዋጭ በማድረግ የጣልቃገብነት አቤቱታዉ ላይ አስቀድሜ ብይን መስጠት አለብኝ ብሎ አስተያየት እንድንሰጥበት ለግራ ቀኝ ወገኖች እድል ከሰጠን በኋላ በሚያዚያ 14/2018 የጣልቃገብ አመልካቾች በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ለመግባት መብት የላቸውም ብሎ አባረራቸዉ። ወሳኝ ቦርዱ በቤት አበል ዉዝፉ ላይ ዉሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 30/2018 ቀጠረን።

ከጣልቃገብነት በብይን በመባረራቸዉ ቅር በመሰኘት የጣልቃገብ አመልካቾች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 359485 ይግባኝ አቅርበዉ የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ በቤት አበል ዉዝፍ ጉዳይ ዉሳኔ ከሰጠ ጥቅማችን ይጎዳል ብለዉ የእግድ አቤቱታ በማቅረብ የዉሳኔ ቀጠሮዉ አሳገዱት። አሁን በከፍተኛ ፍ/ቤት እየታየ የሚገኘው የእነሱን ጣልቃገብነት ጉዳይ በተመለከተ ብቻ ነዉ።

አዲስ የሠራተኛ ማህበር ነን የሚሉ ቡድኖች በጠበቃ ተወክለዉ ነዉ እንግዲህ ይህን የቤት አበል ዉዝፍ ክፍያ ጉዳይን ጨምሮ በደንብ ልብስ እና ሌሎችም የአባል ሠራተኛ ጉዳዮች ላይ በጣልቃገብነት ክርክር እያደረጉ የሚገኙት።

እኛ ነባሩ የሠራተኛ ማህበር በፕሬዝዳንታችን ተወክለን ነዉ ክርክር እያደረግን የምንገኘው። "ወረቀቱ በእኛ ፤ ፀሐፊዉ አይቸግረን..." አይነት የእኛ ጉዳይ ሲሆንበት ጊዜ ፤ የባንካችን ማኔጅመንት በፕሬዝዳንታችን ላይ አነጣጠረ። "...እረኛውን ምታ ፤ መንጋዉ ይበተናል..." የሚባል ብሂል አለ አይደል?

ታድያ የቤት አበል ዉዝፍ ክርክሩን ለማስቆም ፦

✍ በአዲስ የሠራተኛ ማህበር በኩል ተሞከረ ፤ አልተሳካም።

✍ የባንኩ ማኔጅመንት ለማህበራችን በህዳር 05/2018 በተፃፈ ደብዳቤዉ ያሰናበትኩት ሠራተኛ ማህበሩን ወክሎ በፕሬዚዳንትነት ችሎት በመቅረብ በስማችሁ ህገወጥ ተግባር እየፈተፀመ ስለሆነ ማብራሪያ ስጡኝ ብሎ የጠየቀ ሲሆን የባንኩ ማኔጅመንት በተናጠል የወሰደው የስንብት እርምጃ የማህበሩ ፕሬዝዳንት በሠራተኛው ከተሰጠው ኃላፊነት ሊያስነሳዉ አይችልም ፤ ማህበሩን መወከሉን ይቀጥላል በማለት በህዳር 08/2018 የደብዳቤ ምላሽ ሰጠን። ማኔጅመንቱ በማህበራችን በኩል ፕሬዝዳንቱን ለማስነሳት ያደረገው ጥረት ፍሬ ለማፍራት አልቻለም።

✍ የሠራተኛ ማህበሩ በተሰናበተ ፕሬዝዳንት እየተመራ የሚገኝ በመሆኑ እርምጃ ይወሰድበት ብሎ በጥር 01 ቀን 2018 የተፃፈ ደብዳቤ የባንካችን ማኔጅመንት ለአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት አቤቱታ አቀረበ። የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ሁኔታ ቁጥጥር የባንኩ ማኔጅመንት አቤቱታ ተቀብሎ የሠራተኛ ማህበሩ ከባንኩ በተሰናበተ መሪ እየተመራ በመሆኑ የሠራተኛ ማህበሩ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ እርምት ካላደረገ ማህበሩን አግዳለሁ ብሎ በየካቲት 04 ቀን 2018 የቁጥጥር ትዕዛዝ ፃፈልን።

የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ሁኔታ ቁጥጥር በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 176-178 የአሠሪ ድርጅት የሥራ ሁኔታዎች ላይ ቁጥጥር ከማድረግ አልፎ የሠራተኛ ማህበር የዉስጥ አስተዳደርን የሚመለከት ጉዳይ ላይ ጣልቃገብቶ ቁጥጥር ለማድረግ በህግ ስልጣን እንዳልተሰጠው እንዲሁም ሀገራችን ከተቀበለቻቸው የዓለም የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን ቁጥር 87 አንቀጽ 3 እና 4 እንዲሁም ኮንቬሽን ቁጥር 98 አንቀጽ 1 እና 2 አንፃር ሲታይ በሠራተኛ ማህበር ሥራ ላይ የመንግስት ጣልቃገብነት ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ እንዲታረምልን ለቢሮው ኃላፊ ይግባኝ አቀረብን። ቅሬታችን ተቀባይነት አላገኘም።

የተሰጠን የአንድ ወር ጊዜዉ እየተቃረበ በመሆኑ የማህበራችን ፕሬዝዳንት ማህበሩ ከሚታገድ ጊዜያዊ የመፍትሔ አካል ልሁን ብሎ ለማህበሩ አመራር የጠየቀ በመሆኑ በቢሮዉ ትዕዛዝ ላይ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪመጣ ድረስ ከፕሬዝዳንትነት ተነስቶ ምክትል ፕሬዝዳንቱ እሱን ተክቶ እንዲሰራ በየካቲት 23/2018 የማህበሩ አመራር ተሰብስቦ በቃለጉባኤ የተደገፈ ዉሳኔ አሳልፎ ለሥራና ክህሎት ቢሮ ፕሬዝዳንቱን በጋራ ስምምነት አንስተናል ብለን በሸኚ ደብዳቤ ቃለጉባኤዉ ዕዉቅና እንዲሰጠዉ ገቢ አደረግን።

የማህበራችን ፕሬዝዳንት ማህበሩ እንዳይታገድ ካደረገ በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ የተሰጠው ትዕዛዝ በተመለከተ የክለሳ አቤቱታ በግሉ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአስተዳደር ጉዳዮች ችሎት በመ/ቁ 351419 አቅርቦ በመጋቢት 01/2018 የቢሮዉ ትዕዛዝ አሳገደዉ። ተለዋጭ ትዕዛዝ የመጣ በመሆኑ ፕሬዝዳንታችን ለማስነሳት ለሥራና ክህሎት ቢሮ ገቢ ያደረግነው ደብዳቤ ቀሪ አደረግን። የእግድ ትዕዛዙ እስካሁን ድረስ ፀንቶ ይገኛል።

✍ እነዚህ ሁሉ የማኔጅመንቱ ጥረቶች የማህበራችን ፕሬዝዳንት ከኃላፊነት ለማስነሳት አላስቻሉም። ቀጥሎም ማኔጅመንቱ የራሱን የስንብት እርምጃ በመጥቀስ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ስላሰናበትኩት በቤት አበል ውዝፍ ክርክር ችሎት ሊቀርብ አይችልም ብሎ በወሳኝ ቦርድ መቃወሚያ ቢያቀርብም በሚያዚያ 14/2018 በመ/ቁ 034/1/17 በተሰጠ ብይን ተቀባይነት አላገኘም። ለፌድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 359555 ይግባኝ አቀረበ፤ ዉድቅ ሆነበት።

✍ ቀጥሎም ማኔጅመንቱ የሠራተኛ ማህበሩ ፕሬዝዳንት ይታገድልኝ ብሎ 5 ዳኞች ለሚሰየሙበት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 294319 የእግድ አቤቱታ በማቅረቡ ምክንያት ለሚያዚያ 30/2018 የተቀጠረዉ መደበኛ ቀጠሮ ተሰብሮ በሚያዚያ 21/2018 ተመረመረ። "...ሠራተኛ ሆኖ በሠራተኛ ይሁንታ የተመረጠ የሠራተኛ ማህበር ፕሬዝዳንት በአሠሪ ስለተሰናበተ ብቻ ዉክልናዉ ቀሪ አይሆንም..." ተብሎ በአስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰበር አቤቱታው እንዲሁም የእግድ ጥያቄዉ አንድ ላይ ዉድቅ ተደረገበት። ይህ በአምስት ዳኞች የተሰጠው የሰበር ዉሳኔ ወደፊት በተመሳሳይ ጉዳይ የጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰባት ዳኞች እንደገና በመሰየም እስካልሻሩት ድረስ በየደረጃው በሚገኙ ሁሉም የሀገሪቱ ፍ/ቤቶች ዘንድ አስገዳጅነት ያለዉ ዉሳኔ ሆኖ ይቀጥላል።

የባንኩ ማኔጅመንት ያዉም በራሱ አነሳሽነት አስገዳጅ የህግ ትርጉም አሰጥልን። የእኛን ሥራ እግረ መንገዱ/በአቋራጭ ሰራልን ማለትም አይደል?

✍ #በመጨረሻም የዉስጥ አመራርን የመከፋፈል እቅድ ታቅዶ በ6 ግለሰቦች አማካኝነት ህገወጥ ተግባር በማህበራችን ላይ ተፈፀመ። 6 ግለሰቦች በሰኔ 15/2018 የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከኃላፊነት ያስነሱበትን ቃለጉባኤ ለባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገቢ ስላደረጉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት በቤት አበል ዉዝፍ ክርክር ችሎት ሊቀርብ አይችልም ብሎ ማኔጅመንቱ በሐምሌ 08/2018 የዉሳኔ ቀጠሮ ዕለት መቃወሚያ አቀረበ።

በቀረበው መቃወሚያ ላይ አስተያየታችንን በሐምሌ 14/2018 አቀረብን። ማህበሩ በሰኔ 15/2018 ምንም ስብሰባ እንዳላደረገ እንዲሁም በተለመደው አሠራራችን አግባብ የማህበሩ ፕሬዝዳንት የተመለከተ አጀንዳ በማህበራችን ዉይይት እንዳልተደረገበት ፣ ቃለጉባኤዉ የማህበሩ አቋም አለመሆኑን በመግለፅ ማህበራችን ለፍ/ቤቱ የፅሁፍ አስተያየቱ አቀረበ። የማህበራችን ጠቅላይ ም/ቤት በሐምሌ 19/2018 አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ከማህበሩ አቋም ተቃራኒ የሆነ መንገድ የተከተሉ እና የማህበሩን ህልውና ለማናጋት ከተልዕኮ ሰጪ አካል ጋር የተመሳጠሩ ስድስቱ ግለሰቦች ከማህበሩ ኃላፊነታቸው በማሰናበት በቦታቸው ተተኪ አመራር በሉዓላዊ ስልጣኑ በማሟያ ምርጫዉ የመረጠ በመሆኑ ፤ የምክር ቤታችን ዉሳኔ በተጨማሪ ማስረጃነት ለከፍተኛ ፍ/ቤት አቀረብን።

✍ የትላንት ሐምሌ 28/2018 የችሎት ቀጠሮ በጉጉት ይጠበቅ ነበር። ነገር ግን ቀጠሮው ለማስለወጥ ከማህበራችን ዕዉቅና ዉጪ የደብዳቤ ሔዲንግ በማዘጋጀትና ማህተማችን በማስቀረፅ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከኃላፊነት እንዳስነሳው ተጨማሪ ማስረጃዎች ይታዩልን በማለት የሰኔ 15ቱ ግለሰቦች አቤቱታ አቀረቡ። ፍ/ቤቱ የፅሁፍ አስተያየት እንድንሰጥበት ለሐምሌ 30/2018 ቀጥሮናል።

የማህበራችን ማህተም እስከ ማስቀረፅ የዘለቀ የህገወጥነት ጥግ⁉🎯። ሀገራችን ለእንደዚህ አይነቱ ህገወጥ ድርጊቶች የሚሆን አግባብነት ያለዉ የህግ ማዕቀፍ ያላት በመሆኑ ጉዳዩ በህግ አግባብ ይታያል።

ማህበራችን ህጋዊ ሰዉነት ያለዉ ተቋም በመሆኑ ህጋዊ መብቱን እንዲሁም የአባል ሠራተኞች ጥቅምን በህግ አግባብ ለማስከበር እንደወትሮዉ ዝግጁ ነዉ።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ!

ሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም.




ዉድ ሠራተኞች የማህበራችን አመራሮች በተመለከተ አሁን ላይ በስፋት እየተሰራጨ በሚገኘዉ ሐሰተኛ መረጃ እንዳትደናገሩ ፤ የማህበራችሁ እዉነት ይህ ነዉ።እሱም የማህበራችሁ አመራር ልክ ያልሆነውን...
01/08/2026

ዉድ ሠራተኞች የማህበራችን አመራሮች በተመለከተ አሁን ላይ በስፋት እየተሰራጨ በሚገኘዉ ሐሰተኛ መረጃ እንዳትደናገሩ ፤ የማህበራችሁ እዉነት ይህ ነዉ።

እሱም የማህበራችሁ አመራር ልክ ያልሆነውን የማኔጅመንቱ የሠራተኛ አያያዝ (የሥራ ሁኔታ) እንዲታረም እና እንዲሻሻል ከመወትወት ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖ (Positive influence) ከመፍጠር ዉጪ ማኔጅመንቱ እንደሚለዉ ባንካችን (ቤታችን) አንቃወምም።

ሁሉም የማህበራችን አመራር የባንካችን ብርሃን ባንክ አ.ማ. ነባር ተቋማዊ ባህልን ይወዳል። ታድያ ነባሩን ተቋማዊ ባህሉን እንዳይጠፋ ነዉ ትጋታችን።

አዎ! ትላንትም ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት በየደረጃዉ የሚገኙ የማህበራችን አመራሮች ህገ-ደንባችን የማክበር ግዴታ ስላለባቸዉ ከማህበራችን ዓላማ እና እሴት ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሊፈፅሙ አይችሉም።

ይህ ሆኖ ሳለ ሠራተኛው ለማህበራችንና ለአመራሩ ያለው አመለካከት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር ተዋንያን በመቀየር አሁን ላይ እንደ አዲስ እየተሰራጨ የሚገኘው ሐሰተኛ መረጃ በተመለከተ በማስረጃ ለማጥራት ተገደናል። አዎ! ማህበራችንም ሆነ አመራሩ በባንካችን እንዲሁም በማኔጅመንቱ ላይ የጥላቻ ንግግር እንዲሁም የሁከት ተግባር አልፈፀመም ፤ ሊፈፅምም አይችልም። የዘወትር የሥራ እንቅስቃሴዎቻችን ህጋዊነትን የተከተሉ ናቸው።

ባንካችን በዋና መ/ቤቱ በኩል በብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር እና 6 አመራሮች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ በቀን 2/11/2017 የተፃፈ አቤቱታ ለፍትህ ሚኒስቴር አቅርቧል። አቤቱታዉም ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋራት ሥራችን እንዳንሰራ የሁከት ተግባር ፈፅመዋል የሚል ነበር።

የፍትህ ሚኒስቴርም የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ "...በሠራተኛ ማህበሩ ሶሻል ሚዲያ የተሰራጨዉ መልዕክት ይዘት የባንኩ ማኔጅመንት ሃይማኖትን መሰረት አድርገው ተደራጅተዋል አይልም ፤ ማኔጅመንቱ ከማህበሩ ጋር (በሰኔ 07/2017) ባደረገው ስብሰባ በባንኩ አመራሮች ተደረገ የተባለውን ንግግር አምኖ ይህን የሚያደርጉ የባንኩ አመራሮች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድና እንደሚያርም እራሱ ካቀረበዉ ማስረጃ ስለተረጋገጠ የወንጀል ምርመራ አላጣራም..." ብሎ በሐምሌ 22/2017 ዓ.ም. ለባንኩ አሳዉቋል።

ከዚህ ዉሳኔ በኋላ በድጋሚ የባንካችን የደቡብ ዲስትሪክት ኃላፊዎች በግላቸው ተመሳሳይ የወንጀል አቤቱታ ለሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አቀረቡ። የማህበራችን አመራሮች በቋሚነት ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ተይዘዉ ወደ ሀዋሳ ከተማ ተወስደዉ መታሰራቸዉ ህጋዊ አይደለም ብለን ለፍትህ ሚኒስቴር አቤቱታ አቀረብን።

ፍትህ ሚኒስቴርም በድጋሚ የተከፈተው የወንጀል ምርመራ መዝገብ ከሀዋሳ ከተማ ፖሊስ በትዕዛዝ በማስቀረብ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግ ቁጥር 42 አግባብ የወንጀል መዝገቡ በህዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም. እንዲዘጋ ዉሳኔ አሳልፏል።

የፍትህ ሚኒስትር እንደ ቃሉ ለህግ ፣ ለፍትህ እና ለርትዕ በመቆም ፈጣን ምላሽ እንዲሁም አግባብነት ያለው ፍትህ ስለሰጠን እናመሰግናለን። የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ የማህበራችን አመራሮች የእስር ቆይታቸው ሁኔታ ጥሩ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ለተወጣዉ ህጋዊ ኃላፊነቱ እናመሰግናለን። የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት የማህበራችን አመራሮች በወንጀል ሥነሥርዓት ህግ ቁጥር 64 አግባብ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በግል ያቀረቡት ማመልከቻ ተቀብሎ የዋስትና መብታቸውን እንዲጠበቅላቸው እና ዉጪ ሆነዉ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወዲያውኑ በመፍቀዱ እናመሰግናለን።

ማህበራችን እና አመራሩ የሀገሪቱን ህጎችን ዘወትር አክብሮ ሥራውን ያከናውናል። ህጋዊነትን ተከትለን የአባል ሠራተኞች ህጋዊ መብት እና ጥቅም በሁለትዮሽ ወይም በሦስትዮሽ ዉይይት እንዲሁም በሌሎችም ህጋዊ አማራጮች የማስከበር ትጋታችን ግን ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ሁልጊዜም እኛ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጠዉ የሁለትዮሽ ዉይይትን ነዉ። ስለዚህም ለባንካችን ማኔጅመንት አሁንም ጥሪ አለን። የባንካችን ነባር ተቋማዊ ባህሉ ሠራተኛን ማሸማቀቅ እና ማሰቃየት አይደለም። ይልቁንም ሠራተኛው አጥፍቶ ሲገኝ እንኳን በይቅርታ ከጥፋቱ እንዲታረም እድል የሚሰጥ ባንክ ነዉ።

በመሆኑም ከግንቦት/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን የማህበሩ አመራር በእስር (4 አመራር) ፣ በስንብት (1 አመራር) ፣ በዲስፕሊን ቅጣት (5 አመራር) ፣ በቦታ ዝዉዉር (2 አመራር) ፣ ለአመራሩ የደረጃ እድገት እና የማትጊያ ቦነስ በመከልከል ፣ የማህበር ሥራ ፈቃድ በመከልከል... የማህበራችን አመራር ለማሸማቀቅ እንዲሁም በሠራተኛው መካከል የክፍፍል አጀንዳ ለመፍጠር በተደጋጋሚ የሚፈፀም ያልተገባ ተግባርን በመተዉ ፤ ልዩነታችን በዉይይት እንድንፈታዉ እና በትብብር አብረን ለመስራት እንድንችል ለባንካችን ማኔጅመንት ጥሪያችን በድጋሚ እናቀርባለን።

ባንኩ እና ሠራተኛዉ ሊነጣጠል የማይችል የጋራ ግብ እና ራዕይ ያለን መሆኑን የባንካችን ማኔጅመንት ተረድቶ ከእኛ ጋር በአብሮነት ለመስራት ዝግጁ መሆን አለበት ብለን እናምናለን። እኛ ለዉይይት ዝግጁ ነን።

ዉድ የባንካችን ሠራተኞች እንደሰማችሁትም ፤ በማኔጅመንቱ አነሳሽነት በአሁኑ ወቅትም የማህበራችሁ አመራር በድንገት እየታሰረ እና በፍ/ቤት ትዕዛዝ ከእስር እየተፈታ ይገኛል። በሠራተኛ ማህበር ሥራ ምክንያት ተደጋጋሚ እስር በማህበሩ አመራር ላይ መፈፀሙ በየጊዜዉ የሚያሳዝነን ክስተት ቢሆንም በሒደት የሚገኙ ጉዳዮች በተመለከተ የፍትህ አካላት የሥራ ነፃነትን በማክበር ዝርዝሩን ከማቅረብ መቆጠብን እንመርጣለን።

በሰሞንኛ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዳትደናገሩ ግን ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ከባንካችን ማኔጅመንት ቀርቦብን የነበረዉ የወንጀል አቤቱታ በመመርመር ፍትህ ሚኒስቴር የሰጠዉ ዉሳኔ በቴሌግራም ገፃችን አቅርበናል። የፍትህ ሚኒስቴር ያቀረብንለትን የቅሬታ አቤቱታ ተመልክቶ በሁለት አጋጣሚዎች የሰጠን የደብዳቤ ምላሽ እናንተ ዉድ ሠራተኞች ግንዛቤ እንድታገኙበት ሲባል ከዚህ ፅሁፍ ጋር አያይዘን አቅርበናል። ይህ መረጃ ድንግዝግዝታ ያጠራል ብለን እናምናለን።

ስለማህበራችሁ እዉነት ለመረዳት የበለጠ ፍላጎት ያላችሁ ሠራተኞች የፍትህ ሚኒስቴር በ5 ገፅ የሰጠዉ ዉሳኔ ሙሉ ይዘት በአስተያየት መስጫ ሳጥን (Comment section) በተቀመጠው የማህበራችን የቴሌግራም ገፅ መስፈንጠሪያ (Link) ተጭናችሁ በመግባት በሐምሌ 23/2018 ከተላለፈው መልዕክታችን ለማንበብ ትችላላችሁ።

ሁሉም የባንካችን ሠራተኛ በአስተውሎት ሊያዉቀዉ የሚገባው ዋናው ቁም ነገር የማህበራችን አመራር እንዲሁም የባንካችን ማኔጅመንት ሁለታችንም ጊዜያዊ ነን። ህጋዊ ሰዉነት ያላቸው የሠራተኛ ማህበሩ እና ባንኩ ቀጣይነት (Organizational going concern) ያላቸው በመሆኑ የበለጠ በተቋማቱ ላይ የፀና እምነት ሊኖራችሁ ይገባል ብለን ለመምከር እንወዳለን።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ !

ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም.




የሠራተኛ ማህበር አመራር የሠራተኛ ድምፅ ለመሆን ቁርጠኛነት ወሰደ ማለት ፤ በተቀጣሪነት ለሚሰራበት ተቋም ጥላቻ ስላለዉ አይደለም።አዎ‼ የሠራተኛ ማህበር አመራር የሠራተኛ ድምፅ ለመሆን ቁርጠ...
25/07/2026

የሠራተኛ ማህበር አመራር የሠራተኛ ድምፅ ለመሆን ቁርጠኛነት ወሰደ ማለት ፤ በተቀጣሪነት ለሚሰራበት ተቋም ጥላቻ ስላለዉ አይደለም።

አዎ‼ የሠራተኛ ማህበር አመራር የሠራተኛ ድምፅ ለመሆን ቁርጠኛነት ወሰደ ማለት ፤ በተቀጣሪነት ለሚሰራበት ተቋም ጥላቻ ስላለዉ ወይም መልካም ስሙን ለማጉደፍ ፈልጎ ስላለመሆኑ ፤ ከእኛው ተሞክሮ እንዲሁም ከሌሎች ሁለት አንጋፋ ማህበራት ተሞክሮ አንፃር በምስል ማስረጃ ከዚህ ፅሁፍ ጋር አያይዘን ለግንዛቤ አቅርበናል።

የሠራተኛ ማህበራት የዉክልና ፍልሚያ (Berhan Bank Allowance Dispute Shifts from pay claim to Union standing Fight) በሚል ርዕስ ያዉም ያለማንም የመረጃዉ ባለቤትነት የታተመው የፎርቱን ጋዜጣ ዕትምን ምክንያት በማድረግ በየደረጃዉ የሚገኙ የባንካችን ጥቂት የማኔጅመንት አባላት አሁን ላይ በሠራተኛዉ መካከል ክፍፍል ለመፍጠር እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ተረድተናል።

እኛ ግን ባንካችን ብርሃን ባንክ አ.ማ. እንወዳለን። ልክ ያልሆነውን የማኔጅመንት አሠራር ወይም ህገወጥ የሠራተኛ አያያዝ ተግባር ካለ እንዲታረም ልክ ትላንት እንዳደረግነዉ ሁሉ ዛሬም ሆነ ወደፊት በየትኛውም አማራጭ መጠየቃችን ግን አናቆምም።

የሠራተኛ ማህበር አመራር እና የአሠሪ ማኔጅመንት ጊዜያዊ አለመስማማት ለሚዲያ ፍጆታ መዋሉ ወይም ለፍ/ቤት መቅረቡ የአሠሪ ተቋማዊ ባህልን ለብቻዉ እንደማይወክል እንዲሁም የሠራተኛ ማህበር አመራር የግል ጥፋት ተደርጎ እንደማይወሰድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዉስጥ ከ6 አመታት በፊት ተፈጥሮ ከነበረው ክስተት መረዳት ይቻላል።

የምስሎች ምንጭ ፦ ከዚህ መልዕክት ጋር ከተያያዙት ምስሎች እንደሚታየዉ፦ የሪፖርተር ጋዜጣ ሐምሌ 04 ቀን 2010 ዓ.ም. ዕትም ፣ የካፒታል ጋዜጣ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 30/2018 ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ. 212603 እና 213472 (ቅፅ 26 ዕትም) እንዲሁም የአዲስ ፎርችን ጋዜጣ እ.ኤ.አ June 14, 2026 በቅጽ 27 ቁጥር 1363 ዕትም‼

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ!

ሐምሌ 18 ቀን 2018 ዓ.ም.




በድምሩ ብር 72,000,000.00 በነፍስ ወከፍ ደግሞ ብር 24,000.00 በቁጥር ለ3,000 ሠራተኞች የ30 ወራት እንዲከፈለን ያቀረብነው የቤት አበል ውዝፍ ክፍያ ጉዳይ!በሁለትዮሽ ዉይይት...
24/07/2026

በድምሩ ብር 72,000,000.00 በነፍስ ወከፍ ደግሞ ብር 24,000.00 በቁጥር ለ3,000 ሠራተኞች የ30 ወራት እንዲከፈለን ያቀረብነው የቤት አበል ውዝፍ ክፍያ ጉዳይ!

በሁለትዮሽ ዉይይት (Social dialogue) ሳይፈቱ ቀርተዉ በህግ የተያዙ ጉዳያችሁ የደረሰበትን ሙሉ ሒደት አባል ሠራተኞች የማወቅ ሙሉ መብት ፤ እኛም ለእናንተ የማሳወቅ የዉዴታ ግዴታ አለብን። እናንተ ወካይ እኛ ደግሞ ተወካያችሁ ነንና።

አዲስ የሠራተኛ ማህበር ነን የሚሉት የጣልቃገብ አመልካቾች ከጥር/2015 እስከ ሐምሌ/2017 ጊዜ የሚመለከተው የቤት አበል ዉዝፍ ክርክር ላይ በወሳኝ ቦርድ ያቀረቡትን የጣልቃገብነት ማመልከቻ ዉድቅ ተደረገብን በማለት ለከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረቡትን የይግባኝ ቅሬታ መልስ ሰጪዎችን ያስቀርባል ተብሎ የመልስ መልስ ካቀረብን በኋላ በጉዳዩ ላይ ዉሳኔ ለመስጠት በተለዋጭ ለሐምሌ 08/2018 ዓ.ም. ተቀጥሮ ቆይቶ ነበር።

በቀጠሮዉ መሰረት በዕለቱ ዉሳኔ ለመስማት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ስንቀርብ የ2ኛ መልስ ሰጪ ባንክ ነገረፈጅ ዉሳኔዉ ከመሰማቱ በፊት የውክልና መቃወሚያ አለን በማለት 1ኛ መልስ ሰጪ የሆነው የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት በስድስት አመራሮች በሰኔ 15/2018 በተያዘ ቃለጉባኤ ከኃላፊነቱ ያስነሱት ስለመሆኑ ለባንኩ ቃለጉባኤዉን ገቢ ያደረጉልን በመሆኑ ማህበሩን ወክሎ ችሎት ሊቀርብ አይገባም ብሏል።

ይህን የሰማዉ ችሎቱም በበኩሉ ይህን መቃወሚያ ማቅረብ ያለበት ፕሬዝዳንቱን ከኃላፊነት አስነሳሁ የሚለው የሠራተኛ ማህበሩ አካል እንጂ አሠሪ ባንክ አይደለም ብሎ እርምት የሰጠበት ሲሆን ነገረፈጁም በምላሹ በቃለጉባኤዉ ከፈረሙት መካከል ሁለቱ የማህበሩ አመራሮች በችሎት አዳራሽ ስለሚገኙ ተነስተው ለችሎቱ ማስረዳት ይችላሉ ብሏል። ችሎቱም የማህበሩ ም/ፕሬዝዳንት ነኝ ከሚለው ግለሰብ ስለጉዳዩ ጠይቆ የተረዳ ሲሆን የዉሳኔዉ ቀጠሮ ተለዋጭ በማድረግ በቀረበው የዉክልና ተቃዉሞ ላይ አስተያየታችንን ለሐምሌ 14/2018 በፅሁፍ እንድናቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶናል።

በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት አዲስ የሠራተኛ ማህበር ነን የሚሉት ይግባኝ ባዮች የማህበራችን ፕሬዝዳንት ዉክልና በመቃወም እንዲሁም አሁን ከእኛ ወገን ያልሆኑ 6 ግለሰቦች በሰኔ 15/2018 ፈረምንበት የሚሉትን ቃለጉባኤን በመደገፍ በጠበቃ ተወክለዉ 2 ገፅ የፅሁፍ አስተያየት አቅርበዋል።

በእኛ በኩልም በማህበራችን ፕሬዝዳንት ተወክለን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በ3 ገፅ ባቀረብነው የፅሁፍ አስተያየት በዋናነት ያነሳናቸው ነጥቦች፦

✍ በሰኔ 15/2018 ዓ.ም. በ6 ግለሰቦች ተፈረመ በሚል ለፍ/ቤት የቀረበው ቃለጉባኤ የማህበራችን አቋም አለመሆኑን፤

✍ የማህበራችን ፕሬዝዳንት ተጠሪነቱ ለማህበሩ ምክር ቤት ስለሆነ 6 ግለሰቦች ተሰብስበው የብቻቸው የማህበሩን ምክር ቤትን በመወከል ፕሬዝዳንቱን ከኃላፊነት የማንሳት ስልጣን አልተሰጣቸውም ብለን የፕሬዝዳንቱ ተጠሪነት ለማን አንደሆነ የሚገልጸው የህገ-ደንባችን ክፍል በማስረጃነት አያይዘን አቅርበናል።

✍ የማህበራችን ህልውና እና የአባላት ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ከሌላ ተቃዋሚ አካል ለእኩይ ዓላማ በሚገባ ተቀምሞ በሰኔ 15/2018 የተዘጋጀው ቃለጉባኤ የማህበራችን አቋም በማስመሰል የፈረሙ የማህበራችን ም/ፕሬዝዳንትን ጨምሮ 6ቱም ግለሰቦች ከሰኔ 18/2018 ጀምሮ ከማህበራችን የታገዱና ለሐምሌ 19/2018 በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባዉ የማህበራችን ምክር ቤት በእግዱ ላይ ዉሳኔ እንደሚሰጥበት ፤

✍ የቃለጉባኤዉ ይዘት እና የቋንቋ አጠቃቀሙ ከዚህ በፊት በእኛ ማህበር ከተያዙት ቃለጉባኤዎች ፍፁም የሚለይ ስለመሆኑ እንዲሁም የማህበራችን ህጋዊ ማህተምም ሆነ ቁጥር የሌለው መሆኑን ሲታይ የእኛ ማህበር አቋም የማይወክል መሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል ብለናል።

✍ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት በሚያዚያ 21/2018 በሰ/መ/ቁ 294319 ስለማህበራችን ፕሬዝዳንት የውክልና ስልጣን በተመለከተ ከሰበር አጣሪ ችሎት ቀጥተኛ ጭብጥ ተይዞ የተላከለትን መነሻ በማድረግ "....የባንኩ ሠራተኛ ሆኖ በሠራተኛ ይሁንታ የተመረጠ የሠራተኛ ማህበር ፕሬዝዳንት በሒደት የሥራ ዉሉ መቋረጡ የፕሬዝዳንቱን ስልጣን እንዲሁ ቀሪ አያደርገዉም...." በማለት ከብርሃን ባንክ የቀረበዉ የሰበር አቤቱታ ተጠሪን መጥራት ሳያስፈልገዉ በትዕዛዝ ዉድቅ አድርጎ ዉሳኔ የሰጠ በመሆኑና ይህ ዉሳኔ በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ የበታች ፍ/ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ስላለው፤ ዉሳኔዉ በፌድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 7 የሰበር ዳኞች እንደገና ታይቶ እስካልተሻረ ድረስ ፕሬዝዳንታችን እኛን ወክሎ መከራከሩን ይቀጥላል ብለናል።

👉 በተመሳሳይ የቤት አበል ውዝፍ ክፍያ ጉዳይ አሠሪ ባንክ በግንቦት 06/2018 በተፃፈ ማመልከቻዉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት በአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ችሎት ለመሰየም ይችላል ተብሎ በሚያዚያ 14/2018 የተሰጠውን ብይን በመቃወም የይግባኝ ቅሬታ ለዚሁ ለፌድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 359555 አቅርቦ በሰኔ 24/2018 በዋለው ችሎት ይግባኙ ዉድቅ የሆነበት ስለመሆኑ በአስተያየታችን ሳንጠቅስ አላለፍንም።

አዲስ የሠራተኛ ማህበር ነን የሚሉት ይግባኝ ባዮች የማህበራችን ፕሬዝዳንት ዉክልና በመቃወም በጠበቃ ተወክለዉ ያቀረቡት 2 ገፅ አስተያየት ፤ እኛም በ3 ገፅ ያቀረብነው አስተያየት እንዲሁም ከአስተያየታችን ጋር አያይዘን ካቀረብናቸዉ ደጋፊ ማስረጃዎች መካከል 2ቱን በድምሩ 7 ምስሎችን ከዚህ መልዕክት ጋር አያይዘን ለእናንተ ጥልቅ ግንዛቤ ዓላማ አቅርበናል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በሐምሌ 28/2018 ዓ.ም. በመዝገቡ ላይ የመጨረሻ ዉሳኔ ይሰጥበታል ብለን እንጠብቃለን።

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ!

ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም.




በባንኩ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የሠራተኛ ማህበርን የማቋቋም እና የመምራት ፈተናዎች፦ከሠራተኛ ማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክትዉድ ባልደረቦቼ እስካሁን እኛ እንጂ እኔ በሚል አቋም ከማህ...
22/07/2026

በባንኩ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የሠራተኛ ማህበርን የማቋቋም እና የመምራት ፈተናዎች፦

ከሠራተኛ ማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክት

ዉድ ባልደረቦቼ እስካሁን እኛ እንጂ እኔ በሚል አቋም ከማህበራችን መልዕክት ተላልፎ አያዉቅም። ሆኖም ተዋንያን በመቀየር በዘመቻ መልክ የተፈፀመብኝ እና እየተፈፀመብኝ የሚገኘው Character assassination (ስብዕናን የማጉደፍ) ተግባር ለመከላከል ስለራሴ ከትላንት ጀምሮ ይህን ለሁለተኛ ጊዜ መፃፍ ግድ ሆነብኝ።

ማህበራችን ከሰኔ 14-15/2018 ባሉት ቀናት ዉስጥ ብዥታዎች ማጥራት በሚል በዘጠኝ የተለያዩ ክፍሎች ተከታታይ መልዕክት ለማስተላለፍ የተገደደው ትጋቱን ለማንኳሰስ የሚፈፀሙ ተግባራትን ለመከላከል ነበር። በእኔ የማህበሩ መሪ ላይ ተመሳሳይ ስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደብኝ ይገኛል። ስለዚህም እኔን የሚመለከቱ ብዥታዎችን ማጥራቱ አሁን ላይ በጣም አስፈላጊ ሆኖ አግንቼዋለሁ።

✅ በባንካችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነዉ የሠራተኛ ማህበር ከመሰረትን በኃላ ከማኔጅመንቱ ጋር አብረን ለመስራት የትዉዉቅ መድረክ ጠየቅን።

✅ ምላሹን እየተጠባበቅን ሳለ በቁጥር ወደ 3,000 የሚጠጉ በፅህፈት የሥራ መደብ ያልሆኑ (Non-clerical) ሠራተኞች ለኑሮ ዉድነት መደጎሚያ ለሌሎች ሠራተኞች የተከፈለ የቤት ኪራይ አበል አልተከፈለንም ብለዉ ከፍተኛ ቅሬታ አነሱ።

✅ በወቅቱ ገና 1 ወር ያልሞላን አመራር ብንሆንም ሠራተኛዉ ለስብሰባ ጠርተን ቁጣዉ አረገብን። "እመኑኝ አልከዳችሁም" ብዬ በስብሰባው መሐላ መፈፀሜን አስታዉሳለሁ።

✅ የቤት ኪራይ አበል ቅሬታ በሁለትዮሽ ዉይይት ለመፍታት ለባንካችን ማኔጅመንት እና ቦርድ ፅ/ቤት በተደጋጋሚ የደብዳቤ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አጣን። ብዙ ተሞከረ አልተሳካም።

✅ ክስ ለመመስረት ተገደድን። በዳኝነት ስልጣን ክርክር የተነሳ ተጓተተብን። በመጨረሻም ሰበር ችሎት በአስገዳጅ የህግ ትርጉም ወደ ወሳኝ ቦርድ መለሰን።

✅ በድጋሚ ለወሳኝ ቦርድ በመጋቢት 25/2017 ክስ አቀረብን። በዚህ ክርክር እያለሁ የባንኩ ማኔጅመንት በሰኔ 28/2017 በተፃፈ ደብዳቤ "የሠራተኛ ማህበር በመወከል የማከናዉነዉ ተግባር" ጠቅሶ ከባንኩ ተሰናብተሃል አለኝ። ደብዳቤው ከዚህ ፅሁፍ ጋር ተያይዟል። በጣም የሚገርመዉ የባንኩ የዲስፕሊን ኮሚቴ በሰኔ 27/2017 የያዘው ቃለጉባኤ አጀንዳ "...የብርሃን ባንክ መሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር እና የሥራ አስፈፃሚዎች የዲስፕሊን ግድፈት ይመለከታል..." የሚል መሆኑን ተያይዞ ከቀረበዉ የምስል ማስረጃ መረዳት ትችላላችሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ILO Convention 87 (1948) , ILO Convention 98 (1949) , ICESCR, (Article 8) , ICCPR (Article 22 ) ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በተቀበለችበት ሁኔታ ነዉ የባንኩ ማኔጅመንት በዚህ መልኩ በሰነድ አስደግፎ የሠራተኛ ማህበር የሥራ እንቅስቃሴ dictate በማድረግ ጣልቃገብነት ሊፈፅም ችሏል።

በምስል ከተያያዘዉ ከዲስፕሊን ኮሚቴ የዉሳኔ ሐሳብ ክፍል ደግሞ "...የማህበሩ ፕሬዝዳንት የማህበሩ መሪ እንደመሆናቸው እና የማህበሩን ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚቆጣጠሩ በመሆኑ የባንኩ ገፅታ የሚያበላሽና የሚጎዳ መልዕክት እንዲሰራጭ ማድረጋቸው ፤ ለማስተካከል ፈቃደኛ ካለመሆናቸዉም ባለፈ ወደፊት ይህን ተግባር በመገናኛ ብዙሃን ጭምር እንደሚያስተላልፉ በመግለፅ የዛቱ መሆኑ ፤ ሌሎች አምስት አመራሮች ደግሞ የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ሆነዉ እያለ ህገወጥ የሆነ የባንኩን መልካም ስም እና ዝና ለማጥፋት እርምጃ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረጋቸውን ኮሚቴው ተረድቷል..." ይላል ቃል በቃል። የዲስፕሊን ኮሚቴው የሠራተኛ ማህበር ሥራ የሠራተኛዉ የግል አቋም አድርጎ ከመረዳቱም በላይ እኛን ሠራተኞቹን የመከላከል ዕድል ሳይሰጠን ነዉ እራሱ ስለጥፋቱ ተረዳሁ ያለው።

አሁንም በጣም የሚገርመዉ ጉዳይ ከዲስፕሊን ኮሚቴ አባላቱ መካከል ሰብሳቢዉ እንዲሁም ፀሐፊዉ አዲስ የሠራተኛ ማህበር በህገወጥ ድጋፍ በማቋቋም ተግባር ከሌሎች አምስት ከፍተኛ የሥራ መሪዎች ጋር በዛ ወቅት በማህበራችን ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ እና አሁን ላይ በዳኝነት ስልጣን ክርክር ጉዳዩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 303618 አማካኝነት በሒደት የሚገኝ ነዉ። አጀንዳው ቀድሞዉኑ ህጋዊነት የሌለዉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ገለልተኛ ለመሆንና የጥቅም ግጭት ለማስቀረት ከማህበሩ የተከሰሱ ሁለቱ አባላት ከኮሚቴው እራሳቸው ማግለል ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ።

✅ እንግዲህ ቀድሞዉኑ የታቀደበት ጉዳይ በመሆኑ ከስንብቴ በኋላ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከባንኩ ስለተሰናበተ ማህበሩን ወክሎ ለክርክር መቅረብ አይችልም በማለት ማኔጅመንቱ ዉክልናዬን ተቃወመ።

✅ ወሳኝ ቦርዱ ተቃዉሞዉን ተቀበለ። የሠራተኛ ማህበር መሪ በአሠሪ ስለተሰናበተ ብቻ በሠራተኛ ማህበር የሚኖረው ኃላፊነትም አብሮ የሚቀር ከሆነ የሠራተኛ ማህበር ማን መምራት እንዳለበት አሠሪ እንዲፈቅድ እድል መስጠት ነዉ ብዬ አምናለሁ። በጉዳዩ ላይ ባላምንበትም የፕሬዝዳንነቴ ጉዳይ ላይ ብቻ ክርክር በማቅረብ ሠራተኛዉ በጉጉት የሚጠብቀዉን የቤት ኪራይ አበል ክፍያ እንዳይጓተት በማሰብ ጊዜያዊ አማራጭን ተከተልኩኝ። የሠራተኛ ማህበሩ ፕሬዝዳንት ካልሆንኩ ቢያንስ የማህበሩ ጊዜያዊ ሠራተኛ መሆን እችላለሁ። በመሆኑም ወዲያውኑ የነገረፈጅነት ዉክልና ወስጄ ክርክሩን ቀጠልኩ። የቤት ኪራይ አበል በሐምሌ 30/2017 ዓ.ም. ለሠራተኛው ተወሰነ። ስለቴ ሰመረ!

✅ መታገስ ደግ እንደሚባለው ቀጥሎ ደግሞ የማህበሩ ፕሬዝዳንትነቴ ጉዳይ በህግ እልባት ሊያገኝ ነዉ።

ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም.

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ !




በባንክ ኢንዱስትሪ የሠራተኛ ማህበር ለማቋቋም የመጀመሪያዉ ተነሳሽነት የመዉሰድ ፈተናው ከእኔዉ ተሞክሮ ፤ለባንካችን ሠራተኛ ግንዛቤ ዓላማ ከማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክት ፦ዉድ ባልደረ...
21/07/2026

በባንክ ኢንዱስትሪ የሠራተኛ ማህበር ለማቋቋም የመጀመሪያዉ ተነሳሽነት የመዉሰድ ፈተናው ከእኔዉ ተሞክሮ ፤

ለባንካችን ሠራተኛ ግንዛቤ ዓላማ ከማህበሩ ፕሬዝዳንት የተላለፈ መልዕክት ፦

ዉድ ባልደረቦቼ እስካሁን ድረስ እኛ እንጂ እኔ በሚል አቋም ከማህበራችን መልዕክት ተላልፎ አያዉቅም። ሆኖም አሁን ላይ ተዋንያን በመቀየር በዘመቻ መልክ የሚፈፀምብኝ Character assassination (ስብዕናን ማጉደፍ) ለመከላከል ስለራሴ መፃፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድ ሆነብኝ። ማህበራችን ከሰኔ 13-15/2018 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ዉስጥ ብዥታዎች ማጥራት በሚል በተከታታይ ዘጠኝ ክፍሎች መልዕክት ለማስተላለፍ የተገደደው ትጋቱን ለማንኳሰስ የሚፈፀሙ አሉታዊ ተግባራትን ለመከላከል ነዉ። በእኔም የማህበሩ መሪ ላይ ተመሳሳይ ስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደብኝ ይገኛል። ስለዚህም ስለእኔ በአጭሩ መግለፁ አስፈላጊ ሆኖ አግንቼዋለሁ።

✅ በማኔጅመንት ለዉጥ ምክንያት እየተሸረሸረ የመጣው የባንካችን ተቋማዊ ባህል እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ባንኬን እወዳለሁ። በጥቂት ማኔጅመንት የግል ፍላጎት የሚፈፀም አሉታዊ ተግባር ባንኩን ይወክላል ብዬ አላምንም።

✅ ግዴታዬ ከመብቴ ጋር ሲነጥሉብኝ አልወድም። ሌሎች ሲበደሉ አይቼ ማለፍ አልችልም። የህግ ት/ቤት assertive ዜጋ አድርጎኛል ብዬ አምናለሁ። "A man who will not die for something is not fit to live"(የሚሞትለትን ነገር ያላገኘ ሰው ለመኖር ብቁ አይደለም) የሚለው የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር አቋም በፅኑ እጋራለሁ።

✅ ለመጀመሪያ ጊዜ በባንኩ ሥራ የጀመርኩት በ22 ገብርኤል ቅርንጫፍ በደንበኞች አገልግሎት መኮንን (CSO) መደብ ነዉ።

✅ በ2013 ዓ.ም. የቅርንጫፍ ባልደረቦቼን በባንካችን ዉስጥ ሠራተኛን የሚወክል ማህበር ብናቋቁም የሚል ሐሳብ አቅርቤላቸዉ የተወሰኑት ተስማሙ። የተወሰኑት አቅማሙ። ሌሎች ደግሞ ሥራዬ ማጣት አልፈልግም በሚል ሐሳቡ ተቃወሙ።

✅ የሠራተኛ ማህበር የማቋቋም እንቅስቃሴዬ በተመለከተ ወደ ማኔጅመንት ጆሮ ደርሶ፤ እሱ ማነው በሚል የሠራተኛ ማህደሬ ቼክ ተደርጎ "ከቀድሞ መ/ቤትህ መልቀቂያ እንድታመጣ በተደጋጋሚ ተጠይቀህ ለማምጣት አልቻልክም" በማለት በምስል እንደሚታየዉ በግንቦት 06/2013 ዓ.ም. ለስንብት ተዳረግሁ።

የሠራተኛ ማህበር ለማቋቋም በመንቀሳቀሴ የተወሰደ የስንብት እርምጃ በመሆኑ ከዉዝፍ ደመወዝ ጋር ወደ ሥራዬ እንድመለስ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ አቅርቤ ከውዝፍ ደመወዝ ጋር እንድመለስ በ2014 ዓ.ም. ተወሰነልኝ።

ወደ ሥራዬ እንድመለስ ያቀረብኩት የአፈፃፀም ክስ ጨምሮ የባንካችን ማኔጅመንት በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩ እስከ ፌድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ፅሁፍ ጋር በምስል በተያያዘዉ መልኩ ዉድቅ ተደረገ። ወደ ሥራዬ ከውዝፍ ደመወዝ ጋር ተመለስኩ።

ከስንብቴ በፊት የጀመርኩትን በብርሃን ባንክ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የሠራተኛ ማህበር የማቋቋም ሐሳቡ በድጋሚ ገፋሁበት። ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን የብርሃን ባንክ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር ምስረታ በጥር 07/2015 ዓ.ም. ማቋቋም ቻልን። ሰመረልን። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሆኜም ተመረጥኩ።

የሠራተኛ ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላም ሌላ ከባድ ፈተና...

የብርሃን ባንክ ሠራተኞች ማህበር
ለባንኩና ለሠራተኛው የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ሠላም የሚተጋ የሠራተኛው እዉነተኛ ማህበር፤ የሠራተኛዉ የዘወትር ድምፅ !

ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.




Address

Addis Ababa

Telephone

+251920514005

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Berhan Bank Labor Union, የብርሃን ባንክ ሰራተኞች ማህበር posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Berhan Bank Labor Union, የብርሃን ባንክ ሰራተኞች ማህበር:

Shortcuts

Share